በትግራይ ክልል ላለው ወቅታዊ ሁኔታ፤ የፌደራል መንግስት “አስፈላጊውን ድጋፍ” እንዲያደርግ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አሳሰበ    

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ “በጸጥታ ኃይሎች ስም” እየተንቀሳቀሱ ባሉ አካላት፤ “የፕሪቶሪያ ውል ሲፈርስ እና የትግራይ ህዝብ ወደ ዳግም ጥፋት ሲገባ ዝም ተብሎ መታየት የለበትም” አለ። የፌደራል መንግስት እነዚህ አካላት የትግራይ ህዝብንም ሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማይወክሉ መሆኑን ተገንዝቦ “አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት” ብሏል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ያለው በትግራይ ክልል ያለውን “ወቅታዊ ሁኔታ” በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 3፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። አስተዳደሩ በዚሁ መግለጫው፤ በጥር ወር አጋማሽ ከተደረገው የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች ስብሰባ ወዲህ የተከሰቱ ጉዳዮችን ዘርዝሯል። 

አስተዳደሩ “ወንጀለኛ” ከሚለው ቡድን ጋር “ወግነዋል” ያላቸው የሰሜን ምስራቅ እና ደቡብ ግንባር ሰራዊት አዛዦች፤ “ህገ ወጥ ተግባራትን” ከሰሞኑ ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጿል። እነዚህ “ህገ ወጥ ድርጊቶች” እና “አደገኛ አካሄዶች” እንዲቆሙ፤ ለትግራይ ሰራዊት ዋና አዛዥ ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ “የጥፋት ተግባራቱ” ወደ “ከፋ ሁኔታ” መሸጋገራቸውን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ይህን ተከትሎም “በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መቀጠላቸውን” ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስታውቋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ከማለቱ አስቀድሞ መግለጫ ያወጣው የደቡብ ምስራቅ ዞን አስተዳደር፤ ትላንት ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በዓዲ ጉዶም ከተማ ነዋሪዎች ላይ “በተከፈተ ተኩስ”፤ አራት ሰዎች በከባዱ ሲቆስሉ “በርካቶች” ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቆ ነበር። 

የዞኑ አስተዳደር በዚሁ መግለጫው፤ በትላንትናው ዕለት ከዓዲ ጉዶም ከተማ እና ከሳምረ ወረዳ ዘጠኝ አመራሮች ወዳልታወቀ ቦታ ታፍነው መወሰዳቸውንም ገልጿል። ከዞኑ አስተዳደር በኋላ የወጣው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫም፤ በትግራይ “ከላይ እስከ ታች መንግስት ለማፍረስ የሚደረጉ ተግባራት በከፋ ደረጃ ተጠናክረው ቀጥለዋል” ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።

“የትግራይ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦች የኋላ ቀሩን ቡድን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ መንግስት እንዲፈርስ እና የፕሪቶሪያ ውል እንዲጣስ በማድረግ፤ የትግራይ ህዝብን ወደ ዳግማዊ ጥፋት እያስገቡት ነው” ሲልም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በመግለጫው ወንጅሏል። “የፕሪቶሪያ ውል ሲፈርስ እና የትግራይ ህዝብ ወደ ዳግም ጥፋት ሲገባ ዝም ተብሎ መታየት የለበትም” ሲል ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለፌደራል መንግስት መልዕክት አስተላልፏል። 

በትግራይ ክልል “በጸጥታ ኃይሎች ስም የሚንቀሳቀሱ” አካላት “የአንድ ኋላ ቀር” እና “ወንጀለኛ ቡድን” ተላላኪ መሆናቸውን የፌደራል መንግስት መገንዘብ እንዳለበት ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። እነዚህ ኃይሎች “የትግራይ ህዝብንም ሆነ ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማይወክሉ መሆናቸውንም” የፌደራል መንግስት ሊረዳ እንደሚገባም አመልክቷል።

የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን አሳሳቢ የጸጥታ ሁኔታ በመረዳት “አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለበት” ሲልም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው አሳስቧል። እነዚህ አካላት “ወንጀሎቻቸውን ለመከላከል“ ”የፕሪቶሪያ ውልን እያፈረሱ ነው” ሲል የከሰሰው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ የዓለም ማህበረሰብም በተመሳሳይ ሁኔታ “አስፈላጊውን ጫና” እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። 

“ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን የትግራይ ህዝብ ሊወጣበት ወደማይችል ሌላ ዙር ጥፋት እንደሚገባ መላው ህዝባችን ሊገነዝብ ይገባል” ሲል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመግለጫው ማጠቃለያ አስጠንቅቋል። በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ሶስት ከፍተኛ የሰራዊት አዛዦችን ማገዳቸውን ተከትሎ ከፍ ወዳለ ውጥረት ተሸጋግሯል። 

ይህንን የአቶ ጌታቸው ረዳን እርምጃ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ጎራ በየፊናቸው ተቃውመውታል። የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የአቶ ጌታቸው እርምጃ “የተቋሙን አሰራር ያልተከተለ”፣ “ያልሰቀለውን የሚያወርድ” እና “የተናጠል እርምጃ” በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቆ ነበር። 

የሰራዊት አዛዦቹ እግድ “ወንጀልንና ወንጀለኞችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ወደ ኋላ የሚመልስ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲቆም” የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በዚሁ መግለጫው ጠይቋል። በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ጎራ በበኩሉ የሶስቱን ሰራዊት አዛዦች እግድ “ብሔራዊ ክህደት” እና “አሻጥር” ሲል ጠርቶታል።

በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት ከትላንት በስቲያ ለሊት ባወጣው መግለጫ፤ “በዚህ ወሳኝ ወቅት የሰራዊት ግንባር አዛዦችን ‘አግጄያለሁ’ ማለት ሆን ተብሎ ተጋላጭነት እንዲጨምር ለማድረግ፣ የትግራይ ህዝብን ሉዓላዊነት እና ደህንነትን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ለማድረግ ያለመ ክህደት ነው” ሲል የአቶ ጌታቸውን እርምጃ ነቅፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]