የሀዋሳ ከተማ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ ከንቲባ ሊሾምላት ነው 

የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት በአንድ ወር ገደማ ለሁለተኛ ጊዜ በጠራው አስቸኳይ ጉባኤ፤ የከተማይቱን አዲስ ከንቲባ ሹመት እንደሚያጸድቅ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ምክር ቤቱ በነገው ዕለት በሚያካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው ሹመታቸው የሚጸድቅላቸው፤ ከአምስት ዓመት በፊት የከተማይቱ ከንቲባ የነበሩት አቶ ጥራቱ በየነ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

የከተማይቱ ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 2፤ 2018 ለአባላቱ ባስተላለፈው ጥሪ፤ በነገው ዕለት አስቸኳይ ጉባኤ እንደሚካሄድ አረጋግጧል። ምክር ቤት በዚሁ ጥሪው፤ አባላቱ ነገ ጠዋት በሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት በሚገኘው አዳራሽ እንዲገኙ ቢያሳስብም የጉባኤውን አጀንዳ ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ በተመሳሳይ መልኩ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ ከተማይቱን በከንቲባነት እንዲመሩ የተሾሙትን የአቶ ተክሌ ጆንባን ሹመት አጽድቆ ነበር። የሲዳማ ክልል የእንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ተክሌ፤ በዚህ የኃላፊነት ቦታቸው ላይ አንድ ወር ያህል ጊዜ እንኳ ሳይቆዩ ወደ ፌደራል ተቋም ተዘዋውረዋል መባሉ የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። 

ለዚህ መነሻ የሆነው፤ አቶ ተክሌ ከጥቅምት 21፤ 2018 ጀምሮ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በማህበራዊ ሚዲያዎች መሰራጨቱ ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አርማ እና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ፊርማ የያዘው ይህ ደብዳቤ፤ በአድራሻቸው እንዳልደረሳቸው አቶ ተክሌ ባለፈው እሁድ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀው ነበር። 

የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ለአቶ ተክሌ የተጻፈ እና በእጃቸው የሚሰጥ ደብዳቤ ለመስሪያ ቤቱ መድረሱን አረጋግጠዋል። የሲዳማ ክልል ምንጮች በበኩላቸው አቶ ተክሌ ካለፈው አርብ ጀምሮ በስራ ገበታቸው ላይ እንዳልተገኙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ተሰናባቹ ከንቲባ አቶ ተክሌ ለሶስት ሳምንታት የቆዩበትን የሀዋሳ ከተማን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት ከአቶ መኩሪያ መርሻዬ ነበር። አቶ መኩሪያ ለሁለት ዓመት ከአንድ ወር በከንቲባነት ወደቆዩበት ሀዋሳ ከተማ ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ በሲዳማ ክልል የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በአመራርነት የሰሩ ሲሆን የበንሳ ዳዬ ከተማንም በከንቲባነት መርተዋል። 

ሲዳማ የፌዴሬሽኑ 10ኛ ክልል ከሆነች በኋላ ለሀዋሳ ከተማ የተሾሙ ሶስተኛው ከንቲንባ የነበሩት አቶ መኩሪያ፤ ወደ ኃላፊነት የመጡት እንዳሁኑ በተመሳሳይ መልኩ በተጠራ አስቸኳይ ጉባኤ ነበር። በነሐሴ 2015 ዓ.ም አጋማሽ ከተካሄደው ከዚህ አስቸኳይ ጉባኤ ቀናት አስቀድሞ፤ የሀዋሳ ከተማን ለሶስት ዓመት ገደማ በከንቲባነት ያስተዳደሩት አቶ ጸጋዬ ቱኬ በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” ተገምግመው ከስልጣናቸው እንዲነሱ ተደርገዋል። 

አቶ ጸጋዬ ከስልጣናቸውን ከተነሱ በኋላ በፍርድ ቤት ተደራራቢ ክሶች ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውን በእስር ቤት ሆነው ሲከታተሉ ቆይተዋል። የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ከቀርቡባቸው ሁለት ክሶች በየካቲት 2017 ዓ.ም. በነጻ እንዲሰናበቱ ተፈርዶላቸዋል። 

በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተመሰረቱባቸው ክሶች ጥፋተኛ በመባላቸው ምክንያት በእስር ላይ የቆዩት አቶ ጸጋዬ፤ በ13 አመት ጽኑ እስራት እና በ21 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ በመጋቢት 2017 ዓ.ም. ውሳኔ ተላልፎባቸው ነበር። ለአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር በእስር ካሳለፉ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በሲዳማ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከእስር የተፈቱት አቶ ጸጋዬ፤ ለእስር ወዳደረጋቸው የኃላፊነት ቦታ የመጡት አቶ ጥራቱ በየነን ተክተው ነው። 

አቶ ጥራቱ ከነሐሴ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ገደማ በከንቲባነት የሰሩበትን የሀዋሳ ከተማን የለቀቁት፤ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2013 ምርጫ በኋላ ካቢኔውን መልሶ ሲያዋቅር፤ አቶ ጥራቱን በዚሁ የኃላፊነት ቦታቸው ላይ እንዲቀጥሉ አድርጎ ነበር።

አቶ ጥራቱ የምክትል ከንቲባ ማዕረጋቸውን እንደያዙ ከአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅነት ወደ የከተማይቱ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊነት የተዛወሩት በህዳር 2016 ዓ.ም. ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእርሳቸው የኃላፊነት ቦታ ላይ ሌላኛውን የሲዳማ ክልል ፖለቲከኛ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስን መሾሙን ያስታወቀው ጥቅምት 21፤ 2018 ነበር። 

በማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ሚሊዮን፤ ከአቶ ጥራቱ ጋር የስራ ርክክብ ያደረጉት በትላንትናው ዕለት ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሸኛኘት የተደረገላቸው አቶ ጥራቱ፤ በዛሬው ዕለት ከሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጋር የሀዋሳ ከተማን ሁለተኛ ምዕራፍ የከተማ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጉብኝተዋል። ጉብኝቱ የተካሄደው “ከአዲሱ የሀዋሳ ከተማ አመራር ጋር” እንደሆነ የሲዳማ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ቢሮ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)