ስለመጪው ምርጫ ሂደትም ሆነ የጊዜ ሰሌዳን የተመለከተ ውይይት ከመደረጉ አስቀድሞ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሰባት መሰረታዊ ቅደመ ሁኔታዎች ላይ “አፋጣኝ” እና “ተጨባጭ” እርምጃዎችን እንዲወስድ ዘጠኝ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ የፓርቲዎች ስብስብ ጠየቁ። መንግስት እና ገዢው ፓርቲ ቅድመ ሁኔታዎቹን በማሟላት፤ ለሁሉም ወገኖች “ነጻ እና ፍትሃዊ የሆነ” የውድድር ምህዳር እንዲፈጥሩ ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጠኙ ፓርቲዎች እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድነት መድረክ (መድረክ) የተሰኘው የፓርቲዎች ስብስብ ጥሪውን ያቀረቡት “በኢትዮጵያ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠርን” በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 3፤ 2018 በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው። ፓርቲዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፤ ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እያደረገ ያለውን “እንቅስቃሴ” በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ምርጫ ቦርድ ሂደቱን እያከናወነ ያለው በህግ ከተሰጠው ተግባር እና ኃላፊነት አንጻር መሆኑን እንደሚገነዘቡም ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል። ሆኖም ቦርዱ የጀመረው እንቅስቃሴ ለምርጫ “አስቻይ ሁኔታዎች” መኖራቸው “ባልተረጋገጠበት” እየተደረጉ ያለ በመሆኑ፤ “ጥረቱ ሁሉ ትርጉም አልባ መሆኑን በግልጽ መናገር እንፈልጋለን” ሲሉም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አስፍረዋል።
ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማከናወን ያቀደው በመጪው ግንቦት 24፤ 2018 ነው። ቦርዱ የድምጽ መስጫ ዕለትን እና ሌሎችንም የምርጫ ሂደቶች የዘረዘረ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ አዘጋጅቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሌሎችም አካላት ጋር ምክክር ቢያደርግም እስካሁን በይፋ አላጸደቀውም።
ዘጠኙ ፓርቲዎች በዛሬው መግለጫቸው የ2018 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ባለፈው ጊዜያት ከተካሄዱት “የተለየ” እና “አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት” የሚያስችል እንዲሆን፤ ምቹ ሁኔታ መፍጠር “አማራጭ” ሳይሆን “ቅድመ ሁኔታ መሆኑን” አጽንኦት ሰጥተዋል። ፓርቲዎቹ “የማይታለፉ” እና “መሰረታዊ” በሚል በመግለጫቸው ላይ በዘረዘሯቸው ቅደመ ሁኔታዎች ላይም የኢትዮጵያ መንግስት “አፋጣኝ” እና “ተጨባጭ” እርምጃዎችን እንዲወስድም አጥብቀው ጠይቀዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ “ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ መካሄድ ወሳኝ ናቸው” በሚል በቅድመ ሁኔታነት እንዲሟሉ ከጠየቋቸው ጉዳዮች ውስጥ በቀዳሚነት ያስቀመጡት “ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ድርድር” ነው። “መንግስት ከሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በእውነተኛ የዲሞክራሲያዊ ሽግግር የጋራ ፍኖተ-ካርታ ላይ ለመስማማት የሚያስችል አፋጣኝ እና ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት መጀመር አለበት” ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ አቋማቸውን አስታውቀዋል።
“መንግስት ከሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በእውነተኛ የዲሞክራሲያዊ ሽግግር የጋራ ፍኖተ-ካርታ ላይ ለመስማማት የሚያስችል አፋጣኝ እና ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት መጀመር አለበት”
– ዘጠኝ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች
መጪው ምርጫ ከመካሄዱ በፊት፤ በስደት እና በትጥቅ ትግል የሚገኙትን ጨምሮ በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችና ባለድርሻ አካላት መካከል ሁሉን አቀፍ ውይይት በማድረግ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር” እና “ዕርቅ ማውረድ” አስፈላጊ መሆኑንም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ አስፍረዋል።
ፓርቲዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፤ “በግፍ ታስረው የሚገኙ” ያሏቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላት እና “የፖለቲካ እስረኞችን” መንግስት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ “በአፋጣኝ” መልቀቅ እንዳለበትም አሳስበዋል። በተቃዋሚዎች ላይ ይደርሳል ያሉት “ማዋከብ” እና “ማስፈራራት” “ሙሉ በሙሉ መቆም” እንዳለበትም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አመልክተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ እና “በህገ-ወጥ መንገድ” ተዘግተዋል ያሏቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢሮዎች እንዲከፈቱም ጠይቀዋል። “አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኞቹ የፓርቲ አመራሮችና አባላት በእስር ላይ በሚገኙበትና ቢሮዎቻቸው በተዘጉበት ሁኔታ በምርጫ መሳተፍ እጅግ ፈታኝ ብቻ ሳይሆን፤ ከአጃቢነት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውምና መስተካከል እንዳለበት ይታመናል” ሲሉ ፓርቲዎቹ በመግለጫው አስፍረዋል።

“የግጭቶች መቆም እና የጸጥታ ዋስትና” ሌላው በፓርቲዎቹ በቅድመ ሁኔታነት የተቀመጠ ጉዳይ ነው። በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋር እና በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ “አውዳሚ ጦርነቶች” እና “ግጭቶች” “እየተስፋፉ እና እየከፉ ነው” ሲሉ በመግለጫቸው ያመለከቱት ፓርቲዎቹ፤ “ይህ እውነታ በአፋጣኝ፣ በቋሚነትና በሚረጋገጥ መልኩ መቆም አለበት” ብለዋል።
ሰላም እና ጸጥታ ለማንኛውም አስተማማኝ ምርጫ መሰረት መሆናቸውን የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፤ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና ዕጩዎቻቸው በመላ ሀገሪቱ “በነጻነት እና በደህንነት መንቀሳቀስ” እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። እንደ ፓለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ መራጮች፣ ገለልተኛ ታዛቢዎች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃን በነጻነት እና ደህንነታቸው በተጠበቀበት ሁኔታ መንቀሳቀሳቸው “ለምርጫው ተዓማኒነት፣ ተቀባይነትና ዲሞክራሲያዊነት ወሳኝ” መሆናቸውን አብራርተዋል።
ዘጠኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በቁልፍ የዲሞክራሲ ተቋማት እና ህጎች ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ፣ የመንግስት መዋቅሮች ገለልተኝነት እንዲረጋገጥ፣ የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር እንዲሁም የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች በሂደቱ እንዲሳተፉ “አስፈላጊ ሁኔታዎች” እንዲሟሉ በመግለጫቸው ጠይቀዋል። “እነዚህ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የሚደረግ ማንኛውም ምርጫ የህዝብን ፍላጎት ከመግለጽ ይልቅ የይስሙላ ዲሞክራሲ ማሳያ እንደሚሆን እናምናለን” ሲሉም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።

በመግለጫው ማጠቃለያ ስማቸው ከሰፈረ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ)፣ የዐረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት (ዐረና ትግራይ) እና የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) እና የመላው ሲዳማ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ (መሲሕዴአፓ) ይገኙበታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ፣ ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር ኢትዮጵያ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲም (ባልደራስ) መግለጫውን በጋራ ካወጡ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























