አዲሱ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በከተማይቱ ያሉ የሰላም እና ጸጥታ ተቋማትን “ማጠናከር” አንዱ የትኩረት አቅጣጫቸው መሆኑን ገለጹ

በዛሬው ዕለት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ሹመታቸው የጸደቀላቸው አቶ ጥራቱ በየነ፤ በከተማይቱ ያሉ የሰላም እና ጸጥታ ተቋማትን “ማጠናከር” እንዲሁም አረንጓዴ ቦታዎች እና መሰረተ ልማትን “ማስፋፋት” የትኩረት አቅጣጫቸው እንደሆነ ገለጹ። አዲሱ ከንቲባ ሳምንቱን ሙሉ ለ24 ሰዓት ስራዎችን የማከናወን ባህልን ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምጣት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚፈልጉም አስታውቀዋል። 

አቶ ጥራቱ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ሆነው የተሾሙት፤ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 3፤ 2018 በተካሄደ የከተማይቱ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ነው። የአዲሱ ከንቲባ ሹመት እንዲጸድቅ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት፤ የሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ናቸው።

ምክር ቤቱ ለሁለተኛ ጊዜ የሀዋሳ ከተማን በከንቲባነት ለመምራት በዕጩነት የቀረበሉትን የአቶ ጥራቱን ሹመት ያጸደቀው በሙሉ ድምጽ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል። በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር የነበረው የሲዳማ ዞን ራሱን ችሎ ክልል ሆኖ ሲደራጅ፤ አቶ ጥራቱ የሀዋሳ ከንቲባ ነበሩ። 

አቶ ጥራቱ የአሁኑን የከንቲባነት ኃላፊነትን የተረከቡት፤ ከአንድ ወር ላነሰ ጊዜ በዚሁ ቦታ ላይ የቆዩትን አቶ ተክሌ ጆንባን በመተካት ነው። አዲሱ ከንቲባ ሹመታቸው መጽደቁን ተከትሎ ለምክር ቤቱ አባላት ባደረጉት ንግግር፤ የሀዋሳ ከተማን በሀገር አቀፍ እና በአህጉር ደረጃ “ተመራጭ የመኖሪያ፣ የቱሪዝም እና የኮንፍረንስ ከተማ ለማድረግ” “ከፍ ያለ ራዕይ” መሰነቃቸውን ተናግረዋል።

ከንቲባው በዚሁ ንግግራቸው፤ በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ “የሰላም እና ጸጥታ ተቋማትን ማጠናከር”፣ “አረንጓዴ ቦታዎች እና መሰረተ ልማትን ማስፋፋት” የትኩረት አቅጣጫቸው መሆናቸውን ለምክር ቤቱ አባላት አሳውቀዋል። በሀዋሳ ከተማ የአረንጓዴ ቦታዎች እና መሰረተ ልማቶች የሚስፋፉት፤ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እና የከተማ ኘላንን መሰረት በማድረግ መሆኑንም አቶ ጥራቱ ገልጸዋል።

ይህ የከንቲባው እቅድ የቆሻሻ አያያዝና ዘላቂ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ፣ የታቦር ተራራን በማልማት እና የሐዋሳ ሀይቅን ከብክለት የመከላከል ተግባራትን ያካተተ መሆኑን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አመልክቷል። አቶ ጥራቱ ለአንድ ዓመት ገደማ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት እነዚህን ተግባራት ሲያከናውኑ እንደነበር “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የሲዳማ ክልል እና የሀዋሳ ከተማ የቀድሞ አመራሮች አስረድተዋል።

አቶ ጥራቱ ከሚታወሱባቸው ተግባራት መካከል በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ በጎርፍ የሚጠቁ አካባቢዎች የውሃ ፍሳሽ መስመር እንዲገነባላቸው እና በከተማይቱ ፕላን ያልነበራቸው አካባቢዎች እንዲሰራላቸው ማድረጋቸው ተጠቃሽ መሆናቸውን አንድ የቀድሞው የክልሉ አመራር ተናግረዋል። በከተማው ዳቶ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ የብዙ ነዋሪዎች የመንገድ ችግር ለመፍታት የመሰረት ድንጋይ በእርሳቸው ጊዜ መጣሉን ያስታወሱት እኚሁ የቀድሞ አመራር፤ እርሳቸው ከንቲባነታቸውን ከለቀቁ በኋላ ግን ፕሮጀክቱ መቆሙን አብራርተዋል።

አዲሱ ተሿሚ በከንቲባነት ዘመናቸው፤ በከተማው የአረንጓዴ ልማት እንዲሰራ ማድረጋቸው እና የተለያዩ ቤተ እምነቶች ለማስፋፊያ የጠየቋቸው የመሬት ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ ምላሽ በመስጠት የሚታወቁ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል። የታቦር ተራራን ለማልማት በፕሮጀክት ደረጃ እቅድ የተያዘው፤ በእርሳቸው የአመራርነት ጊዜ እንደነበርም አክለዋል።

በአቶ ጥራቱ የስልጣን ዘመን በከንቲባ ጽህፈት ቤት የሰሩ ሌላ አመራር በበኩላቸው አቶ ጥራቱ በሀዋሳ ከተማ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉ ማድረጋቸውን በስኬትነት ያነሳሉ። በተወሰኑ የከተማይቱ ክፍለ ከተሞች ከመሬት ጋር የተያያዘ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታታቸውን ጠንካራ ጎናቸው እንደነበር ይገልጻሉ።

አዲሱ ከንቲባ ዛሬ ከሰዓት ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እና ከክፍለ ከተማ አመራሮች ጋር በነበራቸው የትውውቅ መድረክ ላይም የመልካም አስተዳደርን ጉዳይ አንስተዋል። የከተማው አመራሮች የሚቀርቡላቸውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ “በቁርጠኝነት መስራት” እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን የከተማይቱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አስታውቋል።

በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የኮሪደር እና ሌሎች የፕሮጀክት ስራዎችን ለማከናወን 24/7 የተሰኘውን የስራ ባህል ወደ ከተማይቱ በማምጣት፤ ስራዎችን በጋራ መስራት እንደሚገባ ለከተማዋ አመራሮች ማሳሰባቸውም ተገልጿል። አቶ ጥራቱ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቢሮ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት፤ በከተማይቱ ከተካሄዱ የኮሪደር ልማቶች የአንደኛውን ክፍል የማስተባበር ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ይህንኑ አሰራራ ተግባራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)