የአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት አራተኛ ዙር ግምገማ “አዎንታዊ እርምጃ” መታየቱን ገለጹ  

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ልዑካን ቡድን፤ የኢትዮጵያ የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) አራተኛ ዙር ግምገማ፤ በባለሙያዎች ደረጃ ከስምምነት ለመድረስ የሚያስችል “አዎንታዊ እርምጃ” ማሳየቱን አስታወቀ። በአራተኛው ዙር ግምገማ ላይ የሚደረገው ውይይት በመጪዎቹ ሳምንታት እንደሚቀጥል የልዑካን ቡድኑ መሪ አልቫሮ ፒሪስ ገልጸዋል። 

የአይ ኤም ኤፍ ልዑካን ቡድን ይህን የገለጸው፤ ከጥቅምት 20 እስከ ዛሬ ሐሙስ ህዳር 4፤ 2018 በአዲስ አበባ ጉብኝት ካደረገ በኋላ ባወጣው አጭር መግለጫ ነው። የልዑካን ቡድኑ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ጨምሮ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር “ውጤታማ ውይይቶች” ማድረጉን አስታውቋል።

ባለሙያዎቹ ከባንኮች እና የግል ኩባንያዎች ጋር ጭምር መገናኘታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። ውይይቶቹ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚበደርበት ስምምነት አፈጻጸምን የተመለከቱ ናቸው። 

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ይህንን የተራዘመ የብድር አቅርቦት ያጸደቀው በሐምሌ 2016 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በባለሙያዎች ያደረጋቸው ሶስት ግምገማዎችን መሰረት በማድረግ፤ 851.7 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ መንግስት ለቅቋል።

በኢትዮጵያ መንግስት እና በአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች መካከል በጥቅምት 2017 ዓ.ም ከተደረሰ የመጀመሪያ ግምገማ ስምምነት በኋላ፤ ኢትዮጵያ 340.7 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከድርጅቱ አግኝታለች። በህዳር 2017 ዓ.ም በተመሳሳይ ሁኔታ ከተካሄደው ሁለተኛ ግምገማ በኋላ ደግሞ፤ አይ ኤም ኤፍ 251 ሚሊዮን ዶላር ለቅቋል። 

መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አበዳሪ ተቋም እና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት፤ በተራዘመ የብድር አቅርቦት ሶስተኛ ዙር ግምገማ ላይ ከስምምነት የደረሱት በግንቦት 2017 ዓ.ም ነበር። ስምምነቱ በብድር አቅርቦቱ ለኢትዮጵያ ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን ውስጥ 260 ሚሊዮን ዶላር ለመንግስት እንዲለቀቅ አድርጓል። 

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረገው የአይ ኤም ኤፍ የልዑካን ቡድን መሪ፤ በተራዘመ የብድር አቅርቦት አራተኛ ዙር ግምገማ ላይ በባለሙያዎች ደረጃ ከስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸዋል። የልዑካን ቡድኑን ጉብኝት አስመልክቶ አይ ኤም ኤፍ በመጀመሪያ ያሰራጨው መግለጫ “ጥቂት ያልተፈቱ ጉዳዮች እንደሚቀሩ” ጠቅሶ ነበር። ሆኖም በስተኋላ ላይ ተስተካክሎ የተሰራጨው የድርጅቱ መግለጫ ይህንን ገለጻ አስቀርቶታል።    

ባለሙያዎቹ የጉብኝታቸውን የመጀመሪያ ግኝት መሰረት በማድረግ፤ ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ የሚቀርብ ሪፖርት ያዘጋጃሉ። ይህ ሪፖርት ለድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ከመቅረቡ በፊት፤ ከአይ ኤም ኤፍ አስተዳደር ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል። ሪፖርቱ በስራ አስፈጻሚው ቦርድ ውይይት ተደርጎበት ከጸደቀ፤ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ከፈቀደው 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ የተወሰነውን ይለቅቃል።

አይ ኤም ኤፍ ለአራት ዓመታት የሚቆየውን የተራዘመ የብድር አቅርቦት በሐምሌ 2016 ዓ.ም. ካጸደቀ ወዲህ፤ ለኢትዮጵያ መንግስት የለቀቀው የገንዘብ መጠን 1.871 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። የመጀመሪያው አንድ ቢሊዮን ዶላር የተለቀቀው፤ የኢትዮጵያ ውጭ ምንዛሬ ግብይት “በገበያ ላይ የተመሰረተ” እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)