የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከነገ በስቲያ በፓርላማ ንግግር ሊያደርጉ ነው

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከነገ በስቲያ ረቡዕ ታኅሣሥ 8፤ 2018 ዓ.ም ለፌዴሬሽን እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ንግግር ሊያደርጉ ነው። ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት የሚያካሄዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፤ ንግግር የሚያደርጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚገኙበት የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መድረክ ላይ ነው። 

የፌደሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ለአባላቱ በላከው “አስቸኳይ” መልዕክት፥ “የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መድረክ ንግግር እንደሚያደርጉ” አስታውቋል። ምክር ቤቱ በዚሁ መልዕክቱ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በከተማው ዙሪያ የሚኖሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ከነገ በስቲያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲገኙ አሳስቧል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ይሄው መልዕክት እንደደረሳቸው አረጋግጠዋል። የረቡዕውን የጋራ መድረክ በተመለከተ ለገዢው ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተመሳሳይ መልዕክት ቢላክም፤ የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮች ስለ ጉዳዩ በቀጥታ መረጃ እንዳልደረሳቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ለነገ በስቲያው ስብሰባ የተላለፈውን መልዕክት፤ የገዢው ፓርቲ አባል የሆኑ የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዳሳዩዋቸው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተመራጭ ገልጸዋል። እኚሁ አባል ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት ቅጽር ጊቢ ህንዳውያንን መመልከታቸውንም አክለዋል። 

ከነገ ማክሰኞ ታኅሣሥ 7፤ 2018 ጀምሮ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፤ በፓርላማ ተገኝተው የሚያሰሙት ንግግር ዋነኛ ትኩረት ምን እንደሆነ ለምክር ቤት አባላቱ የተባለ ነገር የለም። የህንዱ ኤንዲቲቪ ቴሌቪዥን ጣቢያ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የዲሞክራሲ እናት” ባሏት በሀገራቸው ህንድ ጉዞ ላይ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ሀሳባቸውን ለማካፈል “በጉጉት እንደሚጠባበቁ” መግለጻቸውን ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ የህንድ እና ኢትዮጵያ አጋርነት ለአለም አቀፉ የታዳጊ ሀገራት ትብብር የሚኖረውን እሴት በተመለከተ ሀሳባቸውን እንደሚያጋሩ መግለጻቸውም በዘገባው ተመልክቷል። የውጭ ሀገር መሪዎች በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለእንደራሴዎች ንግግር ሲያደርጉ መመልከት ብዙም የተለመደ አይደለም። 

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ከ10 ዓመት በፊት ካደረጉት ንግግር ወዲህ ለምክር ቤት አባላት በይፋ ንግግር ያሰማ የውጭ ሀገር መሪ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔያሚን ኔታኒያሁ ናቸው። ምንም እንኳን የሀገር መሪ ባይሆኑም በከፍተኛ ባለሥልጣን ደረጃ የተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው በቅርብ ጊዜ ንግግር ያደረጉት፤ የጅቡቲ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ዲሌታ መሀመድ ናቸው።

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ቆይታቸው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር “በዘርፈ ብዙ የኹለትዮሽ ግንኙነቶች ዙሪያ” በዝርዝር ውይይት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ኤንዲቲቪ ዘግቧል። የሁለቱ ሀገራት ጠቅላይ ሚኒስትሮች፤ ከሶስት ዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ አገራት ጉባኤ ጎን ለጎን ተገናኝተው መነጋገራቸው ይታወሳል።

በመስከረም 2016 ዓ.ም. የተካሄደው የብሪክስ ሀገራት ጉባኤ፤ ህንድ መስራች የሆነችበትን የብሪክስ ሀገራት ስብስብ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል የተጋበዘችበት ነበር። ሁለቱ መሪዎች በዚሁ ጉባኤ ወቅት ባደረጉት ውይይት፤ የሀገሮቻቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ለማሳደግ ተስማምተዋል። 

ሞዲ እና አብይ ከሶስት ሳምንት በፊት በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ ወቅትም ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በወቅቱ ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያደረጉትን ውይይት “ፍሬያማ” እና “ትርጉም ያለው” ሲሉ ገልጸውታል።

የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉብኝት ከመጀመራቸው አስቀድመው የተጓዙት ወደ መካከለኛ ምስራቋ ሀገር ዮርዳኖስ ነው። ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ሶስተኛዋ መዳረሻቸው ኦማን እንደሚያቀኑ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።     

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገራቸው ከመነሳታቸው በፊት በሰጡት መግለጫ፤ የሚጎበኟቸውን ሶስት ሀገራት ከአገራቸው ህንድ ጋራ “ለዘመናት የቆየ የስልጣኔ ግንኙነት እና በአሁኑ ወቅትም ሰፊ የኹለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው” እንደሆኑ መግለጻቸውን ኤንዲቲቪ ዘግቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)