ኢትዮ ቴሌኮም በ2019 በጀት ዓመት ገቢውን 295 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ 

ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮው በጀት ዓመት 295 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አስታወቀ። ተቋሙ በ2019 በጀት ዓመት የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 96.2 ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ አለው። 

መንግስታዊው የቴሌኮም አቅራቢ ኩባንያ ይህን የገለጸው፤ ለሶስት ዓመት ከያዘው ስትራቴጂ ውስጥ በዘንድሮው በጀት ዓመት ሊያከናውናቸው ያቀዳቸውን አበይት ተግባራት ለማስተዋወቅ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ኩባንያው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የሶስት ዓመት ስትራቴጂ “ቀጣዩ አድማስ፣ ዲጂታል እና ክዚያም ባሻገር” የሚል ስያሜ አለው።

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የሚመሩት ተቋም በገቢ፣ በትርፍ ድርሻ እና በደንበኞች ቁጥር አንጻር የያዛቸውን እቅዶች አብራርተዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም በ2019 በጀት ዓመት ገቢውን 295 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን በዚሁ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ይህ እቅድ ኩባንያው ባለፈው ሰኔ ወር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካስመዘገበው ገቢ በ36.7 በመቶ እድገት ያለው ነው። ተቋሙ በሐምሌ ወር አጋማሽ በሰጠው መግለጫ፤ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 215.82 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን እና 92.9 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቆ ነበር።

ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮው በጀት ዓመት ለማሳካት ካቀደው ገቢ ውስጥ ከሞባይል ዳታ እና ኢንተርኔት የሚገኘው 34.6 በመቶውን ድርሻ ይይዛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፍሬሕይወት ተናግረዋል። ኩባንያው በ2019 በጀት ዓመት የሞባይል ዳታ እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በ16.5 በመቶ ለማሳደግ ማቀዱንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጨምረው ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት “ንቁ” የሞባይል ዳታ ተጠቃሚዎች ብዛት ወደ 51.53 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ተቋሙ ባለፈው ሐምሌ ወር አጋማሽ በሰጠው መግለጫ ላይ አስታውቆ ነበር። በዚሁ መግለጫ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ጠቅላላ ደንበኞች ቁጥር 90.12 ሚሊዮን መድረሱ ይፋ ተደርጓል።

ይህን የደንበኞች ቁጥር በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት ወደ 96.2 ሚሊዮን ለማሳደግ መታቀዱን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ በዛሬው መግለጫ ላይ አመልክተዋል። ከዚህም ውስጥ የሞባይል ድምጽ ተጠቃሚዎችን በ6.2 በመቶ ለማሳደግ ተቋሙ እቅድ ይዟል።  የሞባይል ድምጽ ተጠቃሚዎች ብዛት በ2018 በጀት ዓመት 66.95 ሚሊዮን መድረሱን ኩባንያው አስታውቋል።

ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ያሉትን የቴሌ ብር የሞባይል ግብይት አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ11.7 በማሳደግ 67.69 ሚሊዮን ለማሳደግ ማቀዱም በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። በ2018 በጀት ዓመት የተጠቃሚዎቹ ብዛት 60.6 ሚሊዮን በደረሰው “ቴሌ ብር” የተፈጸመው የግብይት መጠን 4.19 ትሪሊዮን ብር ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)