የአሜሪካ ዜጎች “በማንኛውም ምክንያት” ወደ አማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ፤ የአሜሪካ ዜጎች “በማንኛውም ምክንያት” ወደ አማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። በኢትዮጵያ ወደሚገኙ አምስት ክልሎች ከሚደረጉ ማንኛውም ጉዞዎች እንዲርቁ ከዚህ ቀደም ለዜጎቿ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ የነበረችው ካናዳ፤ በዝርዝሩ ውስጥ የአፋር ክልል እንዲካተት አድርጋለች።

ካናዳ የአፋር ክልል የተካተተበትን አዲስ የጉዞ ማስጠንቀቂያ የሰጠችው በትላንትናው ነው። ጎረቤቷ አሜሪካ ዛሬ አርብ መስከረም 15፤ 2019 በኤምባሲዋ በኩል ባሰራጨችው የደህንነት ማንቂያ መልዕክት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ ክልሎች ስላሉ የጸጥታ ሁኔታዎች ለዜጎቿ አጭር ማብራሪያ ሰጥታለች። 

ኤምባሲው በዚሁ መልዕክቱ፤ በአማራ ክልል በላሊበላ ከተማ አቅራቢያ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የሚያመለክት መረጃ እንደደረሰው ገልጿል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትላንት ሐሙስ መስከረም 14 ጀምሮ ወደ ላሊበላ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን በመልዕክቱ የጠቀሰው ኤምባሲው፤ ወደ ከተማይቱ የሚደረጉ በረራዎች ዳግም መቼ እንደሚጀመሩ መረጃ እንደሌለው አመልክቷል።

የአሜሪካ ዜጎች ላሊበላን ጨምሮ ወደ አማራ ክልል ሌሎች አካባቢዎች ለማንኛውም ምክንያት እንዳይጓዙም ኤምባሲው መክሯል። ኤምባሲው ተመሳሳይ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ባስተላለፈበት በትግራይ ክልል፤ የኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነት መቋረጡን የሚያመለክቱ መረጃዎችን እንዳገኘም በመልዕክቱ ላይ አክሏል።

በትግራይ ክልል የኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነት የተቋረጠው ከትላንት ሐሙስ ምሽት አራት ሰዓት ገደማ ጀምሮ እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የክልሉ ነዋሪዎች አረጋግጠዋል። መንግስታዊውን ኢትዮ ቴሌኮም እና የግል ኩባንያ የሆነውን ሳፋሪኮም የኢንተርኔት እና የስልክ “ኔትወርኮቻቸውን እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ” የሰጠው፤ የትግራይ ክልልን በአሁኑ ወቅት እያስተዳደረ ያለው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጭ ጨምሮ ስለጉዳዩ የሚያውቁ አራት ግለሰቦች እንደነገሩት “ሮይተርስ” ዘግቧል። 

የአሜሪካ ኤምባሲ በዛሬ ማስጠንቀቂያው፤ አሜሪካውያን የደህንነት ችግር ሳይደርስባቸው በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ከሚገኙ አካባቢዎች “ለቅቀው” መውጣት የሚችሉ ከሆነ ይህንኑ እንዲያደርጉ መክሯል። ይህንን ማድረግ የማይችሉ የሀገሪቱ ዜጎች ደግሞ “ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ” ድረስ በመጠለያዎች ውስጥ እንዲቆዩ እና የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች የሚያስተላልፏቸውን መረጃዎች እንዲከታተሉ ኤምባሲው አሳስቧል።

እንደ አሜሪካ ሁሉ ካናዳም ዜጎቿ ወደ አፋር ክልል የሚደረግ ማንኛውንም ጉዞ እንዳያደርጉ በትላንትናው ዕለት መልዕክት አስተላልፋለች። ካናዳ ከዚህ ቀደም ባወጣችው የጉዞ ማስጠንቀቂያ፤ ዜጎቿ ወደ አማራ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ክልሎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ወደሚገኙ ስድስት ዞኖች ከሚደረጉ ማንኛውም ጉዞዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ ማሳሰቢያ ሰጥታ ነበር። 

ካናዳ ማስጠንቀቂያውን የሰጠችው፤ በኢትዮጵያ አሉ ያለቻቸውን “አለመረጋጋት፣ ብጥብጥ፣ የትጥቅ ግጭት፣ ወንጀል እና የነዳጅ እጥረት” በምክንያትነት በመጥቀስ ነው። ሀገሪቱ ለዜጎቿ ባስተላለፈችው በዚሁ መልዕክቷ፤ “በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ይበልጥ ሊባባስ እንደሚችል” አመልክታ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)