የኢትዮጵያን ህገ መንግስታዊ ስርዓት ለመለወጥ የሚደረጉ “ማንኛውንም ሙከራዎች” እንደማትቀበል የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ገለጸች  

በኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን “በኃይል ወይም በትጥቅ እንቅስቃሴ” ለመለወጥ የሚደረጉ “ማንኛውንም ሙከራዎች” ውድቅ እንደምታደርግ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አስታወቀች። ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በቅርቡ አብረውት ትብብር የመሰረቱት ታጣቂ ቡድኖች “በቅርቡ ፈጽመዋቸዋል” ያለቻቸውን ጥቃቶችንም ሀገሪቱ በጥብቅ አውግዛለች። 

ሀገሪቱ ውግዘቱን ያስተላለፈችው፤ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ ትላንት አርብ መስከረም 15፤ 2019 ባወጣችው መግለጫ ነው። ህወሓት በትግራይ ክልል አየር ማረፊያዎችን መቆጣጠሩን እንዲሁም በአፋር እና አማራ ክልሎች ወታደራዊ ግጭት መባባሱን የጠቀሰው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፤ እነዚህ ድርጊቶች የኢትዮጵያን “አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና መረጋጋት” አደጋ ላይ የሚጥሉ እንደሆኑም አስገንዝቧል።

መግለጫው የጠቀሳቸው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻካቦት ቢን ናህያን አል ናህያን፤ ሀገራቸው “ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ግዛታዊ አንድነት፣ ደህንነት እና መረጋጋት” ያላትን ጽኑ ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል። ሚኒስትር ዴኤታው፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ ያላትን “ምሉዕ አጋርነት” መግለጻቸውም ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት “በአስቸኳይ እንዲቆም” እና “የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ” ጥሪ ያቀረቡት ሼህ ሻካቦት፤ “ውይይት እና ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ የመፍቻ መንገድ” ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታው “የሲቪል ዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እና ተጨማሪ ግጭቶች እንዳይከሰቱ መከላከል” ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ሼህ ሻካቦት “ለፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ተገዢ መሆን” እንደሚገባም በመግለጫቸው አሳስበዋል። በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካዊቷ ፕሪቶሪያ ከተማ የተፈረመው ይህ ስምምነት፤ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመ ነበር።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን የሚደረጉ “ማንኛውንም ጥረቶች” እንደምትደግፍ በትላንቱ መግለጫዋ ላይ አስታውቃለች። የኢትዮጵያን ደህንነት እና መረጋጋት ማስጠበቅ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ደህንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን መግታት አስፈላጊ መሆኑንም የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አስገንዝቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)