በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ የሸቀጦች ዋጋ ባለፉት ጥቂት ቀናት በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሪ ማሳየቱን የከተማይቱ ነዋሪዎች ገለጹ። ባለፈው ሳምንት ከ12 እስከ 13 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ጤፍ፤ ትላንት በዋለው ገበያ 16 ሺህ ብር መግባቱን አንድ የከተማይቱ ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የመቐለ ከተማ ነዋሪው ይህን የተናገሩት፤ ደካማ የኢንተርኔት ግንኙነት ካለበት የትግራይ ክልል አካባቢ ሆነው ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ጋር ባደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ ነው። በአብዛኛው የትግራይ ክልል አካባቢዎች መንግስታዊው ኢትዮ ቴሌኮም ይሰጣቸው የነበሩት የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎቶች የተቋረጡት፤ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ መስከረም 14፤ 2019 ምሽት ላይ ነበር።
ሌላኛው የቴሌኮም አገልግሎቶች ሰጪ ድርጅት የሆነው የሳፋሪኮም ኔትወርክ ግን እስከ ትላንት አርብ እኩለ ቀን ድረስ በመቐለ ከተማ ይሰራ እንደነበር የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ አረጋግጧል። የሳፋሪኮም ኔትወርክ መስራቱን የተመለከቱ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ ትላንት ረፋዱን ኩባንያው ለሽያጭ ያቀረበውን ሲም ካርድ ለመግዛት ወረፋ ይዘው ታይተዋል።

የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት የሆነው ኤ ኤፍ ፒ በትላንትናው ዕለት ባሰራጨው ፎቶም፤ በርከት ያሉ ነዋሪዎች በመቐለ መሀል ከተማ በሚገኘው የሳፋሪኮም ዋና የሽያጭ ቅርንጫፍ ሲም ካርድ ለመግዛት ተሰልፈው እንደነበር አሳይቷል። ይሁን እንጂ የሳፋሪኮም የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎትም፤ ከትላንት ከሰዓት በኋላ “ሙሉ ለሙሉ” መቋረጡን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከነዋሪዎች ተረድታለች።
የኢትዮ ቴሌኮም እና የሳፋሪኮም የኢንተርኔት እና የስልክ “ኔትወርኮቻቸውን እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ” የሰጠው፤ የትግራይ ክልልን በአሁኑ ወቅት እያስተዳደረ ያለው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጭን ጨምሮ ስለጉዳዩ የሚያውቁ አራት ግለሰቦች እንደነገሩት “ሮይተርስ” በትላንትናው ዕለት ዘግቦ ነበር።
የመቐለ እና የሌሎች አካባቢ ነዋሪዎች፤ በዛሬው ዕለት ወደ ትግራይ ክልል አዋሳኝ ስፍራዎች በመሄድ ከዘመድ እና ጓደኞቻቸው ጋር በስልክ እና በኢንተርኔት ለመገናኘት ሙከራዎች እያደረጉ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተገንዝባለች። የክልሉ ነዋሪዎች በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ተቀስቅሶ ሁለት ዓመት በፈጀው የትግራይ ጦርነት ወቅትም፤ ይህንኑ ተመሳሳይ መፍትሔ ሲጠቀሙ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይህን መፍትሔ በመጠቀም ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር በዛሬው ዕለት አጭር ቆይታ ያደረጉት የመቐለ ከተማ ነዋሪ፤ በትላንትናው ዕለት በክልሉ ዋና ከተማ የነበረውን የሸቀጦች ዋጋ ዘርዝረዋል። እንደ እርሳቸው አባባል ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየው በምግብ ሸቀጦች ላይ ነው።
ሶስት ሺህ ብር ገደማ ጭማሪ ከታየበት ኩንታል ጤፍ ሌላ ፉርኖ ዱቄት እና ዘይት የዋጋ ማሻቀብ እንደታየባቸው የመቐለ ከተማ ነዋሪው አስረድተዋል። ባለፈው ሳምንት 2,500 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረው አምስት ሊትር የምግብ ዘይት፤ በቀናት ውስጥ በሊትር 700 ብር ያህል ጭማሪ እንደተደረገበት ነዋሪው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
“ሮይተርስ” የዜና ወኪል ባለፈው ሐሙስ ባሰራጨው ዘገባ፤ ወደ ጦርነት መመለስን የሰጉ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች የምግብ ሸቀጦችን ገዝተው እያከማቹ መሆኑን አስነብቦ ነበር። በመቐለ ከተማ በሚገኝ አንድ ሱቅ ውስጥ የሚሰራውን ሳሙኤል ገብረ ስላሴ የተባለ የ37 ዓመት ጎልማሳ በዚሁ ዕለት ያነጋገረው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት፤ በህብረተሰቡ ውስጥ “መሰረታዊ ሸቀጦች በድጋሚ ይቋረጣሉ የሚል ጥልቅ ፍርሃት አለ” ማለቱን ዘግቧል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የመቐለ ነዋሪ፤ በከተማይቱ ከሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ባሻገር “የአቅርቦት እጥረት” እንደሚስተዋል አመልክተዋል። በከተማይቱ ከአቅርቦት እጥረት እና ከገበያ መጥፋት ጋር የተያያዘው ሌላው ሸቀጥ፤ ለተሽከርካሪዎች የሚውለው ናፍጣ ነው።
እንደ ነዋሪው ገለጻ በመቐለ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች በአሁኑ ወቅት ናፍታ ማግኘት አልቻሉም። በትግራይ ባለፉት ዓመታት የነዳጅ ውጤቶች የሚገኙ በመደበኛ ማደያዎች ሳይሆን ህጋዊ ባልሆነው “ጥቁር ገበያ” ነው።
በዚህ ገበያ አማካኝነት ባለፉት ዓመታት አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 1,200 ብር ይሸጥ እንደነበር የገበያ ሁኔታውን በቅርበት የሚያውቁ ይናገራሉ። በትላንትናው ዕለት አንድ ሊትር ቤንዚን በመቐለ ሲሸጥ የነበረው ከ800 እስከ 900 ብር እንደነበር የከተማይቱ ነዋሪ ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































