በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተመረጡ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባላት፤ ጨፌ ኦሮሚያን በአፈ ጉባኤነት እንዲመሩ አቶ አብዱልሰላም ዋሪዮን መረጡ። የምክር ቤቱ አባላት በምክትል አፈ ጉባኤነት ለአምስት አመት እንዲያገለግሉ የመረጡት ወ/ሮ ዘምዘም ሻሎን ነው።
ጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ ምርጫ ያካሄደው፤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 18፤ 2019 በአዳማ ከተማ እያካሄደ ባለው መስራች ጉባኤው ነው። ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ ምርጫ ከተካሄደባቸው 11 ክልሎች ውስጥ ቀዳሚ በመሆን የምስረታ ጉባኤውን ያካሄደው ጨፌ ኦሮሚያ፤ 537 መቀመጫዎች አሉት።
ምርጫ ከተደረገባቸው 523 መቀመጫዎች ውስጥ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ 99 በመቶውን አሸንፏል። በክልሉ ለነበረው ምርጫ 45 ተወዳዳሪዎችን አቅርቦ የነበረው፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አንድ መቀመጫ ማግኘት ችሏል።

ቀሪዎቹ የጨፌ ኦሮሚያ መቀመጫዎች የተያዙት በአራት የግል ተወዳዳሪ ተመራጮች ነው። እነዚህን የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኙ ተመራጮች፤ በጨፌ ኦሮሚያ ምስረታ ጉባኤ የመጀመሪያ የሆነውን ተግባራቸውን ዛሬ ጠዋት አከናውነዋል።
በዚህም መሰረት የቦረና ዞን ዋን አስተዳዳሪ የነበሩትን አቶ አብዱልሰላም ዋሪዮን፤ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤትን በአፈ ጉባኤነት እንዲመሩ በአብላጫ ድምጽ መርጠዋል። በአመራር የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው አቶ አብዱልሰላም፤ ላለፉት 15 ዓመታት ከወረዳ እስከ ዞን ባሉ የተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ማገልገላቸው ተገልጿል።
በወረዳ ጽህፈት ቤት ደረጃ ለሁለት ዓመት፣ በዞን ፓርቲ አደረጃጀት ለአራት ዓመት፣ በቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪነት እና የዞኑ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊነት የሰሩት አቶ አብዱልሰላም፤ የ42 ዓመት ጎልማሳ ናቸው። አዲሱ አፈ ጉባኤ ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ በግል ድርጅቶች በመስራት “ልምድ አካብተዋል” ተብሏል።
ተሰናባቿ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን ለቦታው የተመረጡት፤ በመስከረም 2014 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው የጨፌ ኦሮሚያ መስራች ጉባኤ ላይ እንደነበር። ላለፉት አምስት ዓመታት በጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤነት ኃላፊነታቸው ላይ የቆዩት ሰዓዳ፤ የምስራቅ ሐረርጌ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ።
የእርሳቸው ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ኤልያስ ኡመታ ናቸው። በዛሬው ጉባኤ አቶ ኤልያስን እንዲተኩ የተመረጡት፤ የአርሲ ዞን የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ዘምዘም ሻሎ ናቸው። ወ/ሮ ዘምዘም ከ15 ዓመት በላይ የአመራር እና የስራ ልምድ እንዳላቸው ከሹመታቸው በፊት በቀረበው አጭር ታሪካቸው ላይ ተጠቅሷል።

የጨፌ ኦሮሚያን ከዚህ ቀደም በአፈ ጉባኤነት ከመሩ ግለሰቦች ውስጥ አቶ ለማ መገርሳ፣ ደሚቱ ሀምቢሳ፣ ሎሚ በዶ ይጠቀሳሉ። አቶ ለማ ከጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤነት ኃላፊነታቸው በኋላ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት እና የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ወ/ሮ ደሚቱ ከአፈ ጉባኤነት በኋላ የሴቶች እና ህጻናት፣ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። በሚያዝያ 2013 ዓ.ም በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት የቀድሞዋ አፈ ጉባኤ፤ እስካለፈው ነሐሴ ወር ድረስ በዚሁ የኃላፊነት ቦታቸው ላይ ቆይተዋል።
ከ2011 እስከ 2014 ጨፌ ኦሮሚያን በአፈ ጉባኤነት ያገለገሉት ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ የተሰናባቹ የስድስተኛው የፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]


































