የኦሮሚያ ክልልን ለሰባት ዓመታት የመሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ለክልሉ ፕሬዝዳንትነት በድጋሚ ተመረጡ

የኦሮሚያ ክልልን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ለሁለት ዓመት ተኩል፣ በሙሉ የፕሬዝዳንትነት ስልጣን ላለፉት አምስት ዓመታት የመሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ክልሉን እንዲያስተዳድሩ በድጋሚ ተመረጡ። አቶ ሽመልስ የተመረጡት በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት መስራች ጉባኤ በተገኙ 509 የጨፌ ኦሮሚያ አባላት ናቸው።

ዛሬ ሰኞ መስከረም 18፤ 2019 በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ያለው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) መስራች ጉባኤ፤ የአቶ ሽመልስን የክልል መሪነት ያጸደቀው በጭብጨባ ነው። እንደ አቶ ሽመልስ ሁሉ ያለ ምንም ተቀናቃኝ የቀረቡትን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ ሹመት ሲጸድቅ ድምጽ ቢሰጥም፤ የክልሉ ፕሬዝዳንት ምርጫ ግን በዚህ አካሄድ አላለፈም።

ከአቶ ሽመልስ ዳግም ምርጫ አስቀድሞ፤ የክልሉን ፕሬዝዳንት የትምህርት እና የስራ ልምድ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። ይህንኑ አጭር ገለጻ ለጨፌ ኦሮሚያ ተመራጮች ያቀረቡት፤ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ናቸው።

የ40 ዓመቱ አቶ ሽመልስ በፍልስፍና እና በሰብአዊ መብት ሁለት የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው ለምክር ቤቱ ያስረዱት አቶ ከፍያለው፤ ላለፉት ሰባት ዓመታት “ቀን እና ለሊት ሳይሉ” ክልሉን ሲያገለግሉ መቆየታቸውን አመልክተዋል። አቶ ሽመልስ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንትነት በድጋሚ የቀረቡት “ለማንኛውም ችግር ሳይበገሩ በግንባር ቀደምነት የአመራር ሚናቸውን በመወጣታቸው” እንደሆነ የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብራርተዋል።

ይህንን ምስክርነት ለአቶ ሽመልስ የሰጡት አቶ ከፍያለው፤ ከደቂቃዎች በኋላ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት እና በጨፌ ኦሮሚያ የመንግስት ተወካይ ሆነ ተመርጠዋል። አቶ ከፍያለውን በብቸኝነት ለኃላፊነት ቦታዎቹ በዕጩነት ያቀረቧቸው፤ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው።

የ50 ዓመቱ አቶ ከፍያለው በፌደራል እና በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ማገልገላቸው በአቶ ሽመልስ ተጠቅሷል። አዲሱ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ በፌደራል ደረጃ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ምክትል ዳይሬክተር እንዲሁም የሲቪል ስርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ሰርተዋል።

በመከላከያ ሰራዊት በአባልነት እና በአመራርነት ማገልገላቸው የተነገረላቸው አቶ ከፍያለው፤ በኦሮሚያ ደረጃ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽን እና የጸጥታ ቢሮን በኃላፊነት መርተዋል። አዲሱ ተሿሚ፤ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ማዕረግ የሰላም እና የፍትህ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል።

አቶ ከፍያለው ላለፉት አምስት ዓመታት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ አወሉ አብዲን የሚተኩ ይሆናል። አቶ አወሉ ከዚህ ሹመታቸው አስቀድሞ በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]