በትግራይ እና አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ “የትጥቅ ግጭት” አድርጎ እንደሚወስደው ኢሰመኮ ገለጸ

Screenshot

በትግራይ ክልል እና በአዋሳኝ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለውን ውጊያ፤ ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተቋም የሚጠራው “ጦርነት” በሚለው ስያሜ ሳይሆን “የትጥቅ ግጭት” በሚለው ብየና እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ተናገሩ። የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን በተመለከተ ኮሚሽኑ “መረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ” መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ይህን የገለጹት፤ ዓመታዊውን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ዛሬ አርብ መስከረም 29፤ 2019 ይፋ ባደረጉበት ወቅት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። አቶ ብርሃኑ በዚሁ መግለጫቸው፤ በትግራይ ክልል ባሉ ግጭቶች እየተሳተፉ ያሉ አካላት “ ‘የጦርነት ተዋጊዎች ናቸው’ የሚል ነገር እስካሁን አልደረስንበትም” ብለዋል። 

“በቀደም ያወጣነው መግለጫ ላይ [እንደገለጽነው]፤ በትግራይ እና አዋሳኝ በሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች፣ በትግራይ እና አዋሳኝ በሆኑ በአፋር የክልል አካባቢዎች ያለው ሁኔታን የትጥቅ ግጭት አድርገን ነው የምንወስደው” ሲሉም ዋና ኮሚሽነሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኢሰመኮ የዛሬ ሁለት ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ በትግራይ እና በአማራ እንዲሁም በትግራይ እና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ ስፍራዎች “ከጊዜ ወደ ጊዜ” ሲባባስ የቆየው “ውጥረት”፤ የ“ትጥቅ ግጭት” መቀስቀሱን አስታውቆ ነበር።

 “እነዚህ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በትጥቅ ግጭት የተጎዱ እና በበቂ ሁኔታ ያላገገሙ በመሆናቸው፤ የትጥቅ ግጭት ዳግም መከሰቱ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ሁኔታ ላይ ተደራራቢ ጉዳትን ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲልም ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። “በእነዚህ ግጭቶች ውስጥ ሲቪሎች ኢላማ ተደርገዋል ወይ?” የሚለው የኮሚሽኑ ዋና ትኩረት እንደሆነ አቶ ብርሃኑ በዛሬው መግለጫ ላይ አስገንዝበዋል።

“የሲቪሎች ማለት የግጭቱ ወይም የጦርነቱ ተሳታፊ ያልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ሲደርስ እና ሲቪሊያን ተቋማት ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ያን ተከትለን መግለጫ የምናወጣበት፣ የምናወግዘው ነገር ካለ የምናወግዝበት፣ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ካሉም እንዲሻሻሉ ምክረ ሃሳብ የምናቀርብበት አሰራር ነው ያለን” ያሉት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር፤ “ከዚያ ውጪ ያለውን ‘ይሄ ነው፣ እንዲህ ነው፣ ማን ከማን ጋር’ የሚለውን መረጃ ስጡን የሚባለው፤ መረጃ ልንሰጥ አንችልም” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል።

የኤርትራን ጉዳይ በሚመለከት ኮሚሽኑ “መረጃ በማሰባሰብ ላይ” መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ ግጭቱ ወደ ጦርነት “አድጓል ወይስ አላደገም?” የሚለውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ምንጮችን እንዲሁም ተቋማቸው ያሉትን “የዲጂታል ማረጋገጫ ስርዓቶች” ተጠቅሞ “በማጣራት ላይ” መሆኑን አብራርተዋል። ባለፉት ቀናት የወጡ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች፤ የኤርትራ ወታደሮች ድንበር በማቋረጥ አዲግራት ከተማን አልፈው እስከ ዕዳጋ ሐሙስ ድረስ ዘልቀው እንደነበር የዓይን እማኞችን በመጥቀስ ይፋ አድርገው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

We are hiring!