በጋምቤላ ከተማ ከምሽት እስከ ንጋት የሚዘልቅ የሰዓት እላፊ ተጣለ  

በጋምቤላ ከተማ ከዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 4፤ 2019 ጀምሮ ከምሽት 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ “ላልተወሰነ ጊዜ” የሚቆይ የሰዓት እላፊ ተጣለ። “ለጸጥታ ስራ” ሲባል እንደተጣለ በተገለጸው በዚሁ የሰዓት ገደብ ውስጥ በከተማይቱ የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ “በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን” የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ይህን እርምጃ የወሰደው፤ በጋምቤላ ከተማ ትላንት ማክሰኞ ምሽት በተፈጸመ ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። ኮሚሽኑ ጥቃቱ የተፈጸመው “ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት” መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ቢያስታውቅም፤ በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

ከትላንትናው ጥቃት በኋላ በጋምቤላ ከተማ “የጸጥታ መደፍረስ” ማጋጠሙን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በዛሬው መግለጫው አረጋግጧል። በማክሰኞ ምሽት ክስተት ሳቢያ “በቁጣ እና ስሜታዊነት” በመነሳሳት ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እና በንብረት ላይም ጉዳት እንዳይደርስ፤ የከተማው ነዋሪ ለጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ኮሚሽኑ በመግለጫው አሳስቧል።

በከተማይቱ “ለጸጥታ ስራ” በህጋዊ መንገድ ፈቃድ ከተሰጣቸው የጸጥታ አካላት ውጪ፤ ማንኛውም አካል የጦር መሳሪያ ይዞ በከተማዋ ውስጥ መንቀሳቀስ “በጥብቅ የተከለከለ” መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል። ኮሚሽኑ ለሚያከናውነው “የጸጥታ ስራ ስኬት ሲባል”፤ ከዛሬ ረቡዕ ጥቅምት ምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ የሚቆይ የሰዓት እላፊ መጣሉን ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።

“ላልተወሰነ ጊዜ” እንደሚቆይ በተገለጸው በዚህ የሰዓት ገደብ ውስጥ በጋምቤላ ከተማ የሰዎች እና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ “በጥብቅ” መከልከሉንም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል። እገዳውን ተላልፎ በሚገኝ አካል ላይ ኮሚሽኑ በህግ መሰረት “አስፈላጊውን እርምጃ” እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

ተደጋጋሚ ግጭቶች በሚከሰቱበት የጋምቤላ ክልል፤ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎች እና የሰዓት እላፊ ገደቦች በየጊዜው ሲጣሉ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት በጋምቤላ ከተማ እና በአካባቢው የደረሱ ጥቃቶችን ተከትሎ በህዳር እና ታህሳስ ወራት የሰዓት እላፊ ገደቦች ተጥለው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]

We are hiring!