ኢትዮጵያ ከሱዳን ወደ ግዛቷ የገቡ የጦር መሳሪያዎችን በተመለከተ ማስረጃ እንደምታቀርብ ለተመድ የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ገለጸች

በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት የሚሳተፉ “የተወሰኑ ወገኖች” በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ ደህንነት ላይ ለሚፈጽሟቸው “ከባድ ጥሰቶች” በሁለትዮሽ የግንኙነት መንገዶች መፍትሔ ለማበጀት ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ኢትዮጵያ ለተመድ የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት አሳወቀች። ምክር ቤቱ ትላንት ባካሄደው ስብሰባ፤ “በኮንትሮባንድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሱዳን የጦር መሳሪያዎችን በተመለከተ በቂ ማስረጃ በተገቢው ጊዜ እንደሚቀርብ” ኢትዮጵያ ገልጻለች። 

ትላንት አርብ ጥቅምት 6፤ 2019 ምሽት በኒው ዮርክ የተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ሱዳን በመካሄድ ላይ በሚገኘው ጦርነት እና ባስከተላቸው ሰብአዊ ቀውሶች ላይ የመከረ ነው። በስብሰባው ከአስራ አምስቱ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አባላት በተጨማሪ በምክር ቤቱ አሰራር መሠረት የሱዳን፣ የኢትዮጵያ እና የግብጽ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያን በመወከል በስብሰባው ላይ የተካፈሉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ናቸው። ግሪክ በሰብሳቢነት በመራችው በዚህ ስብሰባ በተመድ የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ዋና ጸሀፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ ስለ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ አቅርበዋል።

ኃላፊዋ በማብራሪያቸው የሱዳን ህዝብ ከባድ ውጊያዎች፣ ሰብአዊ ቀውስ፣ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እና የመሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥን እንደተጋፈጠ አስረድተዋል። በተለይ ከኢትዮጵያ በሚዋሰነው ብሉ ናይል፣ ሰሜን ኮርዶፋን እና ደቡብ ኮርዶፋን ግዛቶችን ጨምሮ በመላው ሱዳን አሁንም ውጊያው እንደቀጠለ አስረድተዋል። 

ሮዝሜሪ ዲካርሎ በሱዳን ድንበሮች አካባቢ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ በዚሁ ስብሰባ ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የሱዳን ሁኔታ ቀድሞም በበርካታ ቀውሶች በታወከው ቀጠና፤ ከፍተኛ የአለመረጋጋት ተጋላጭነት ባለባቸው ጎረቤት ሀገራት ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህም ምክንያት ሁሉም ወገኖች የሱዳን ግጭት ድንበር ተሻግሮ ሊሰፋ የሚችልበትን ማንኛውም ድርጊት እንዲያስወግዱ አሳስበዋል። ሰፊ ቀጠናዊ ቀውስ እንዳይከሰት መከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው የጋራ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባም ለሀገራቱ ምክራቸውን ለግሰዋል።

ወደ አራተኛ ዓመቱ እየተንደረደረ ያለው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት፤ በአብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን በሚመራው የሱዳን የጦር ኃይሎች እና መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሲካሄድ የቆየ ነው።  በሱዳን ያለውን ጦርነት በማቀጣጠል እና ለረጅም ጊዜ እንዲቀጥል በማድረግ የቀጠናው እና የገልፍ ሀገራት “ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው” የሚል ውንጀላ ይቀርብባቸዋል።

በተመድ የሱዳን ቋሚ ተጠሪ የሆኑት አምባሳደር አል ሀሪትዝ ኢድሪስ መሐመድ ይህንኑ ውንጀላ በትላንቱ የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አንስተዋል። በዚሁ ስብሰባ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የድሮኖች ጥቃት፤ ጎረቤታሞቹን ኢትዮጵያ እና ሱዳንን ያካሰሰ ጉዳይ ነበር።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድሮኖችን በስፋት እየተጠቀመ እንደሚገኝ የገለጹት አምባሳደር አል ሀሪትዝ፤ ታጣቂ ቡድኑ የሚፈጽማቸው የአየር ላይ ጥቃቶች ከሚሊሺያው አቅም በላይ “የተወሳሰበ ዕቅድ” እንደሚጠይቁ አስረድተዋል። በውጭ አገር ባለሙያዎች እና ሰራተኞች የሚተዳደሩ የድሮን ማስወንጨፊያ እና ማከማቻዎች በመጠቀም ጥቃቶቹ፤ ከዕዝ ማዕከላት እንደሚፈጸሙም አብራርተዋል።

ታጣቂ ቡድኑ በኮርዶፋን፣ ብሉ ናይል፣ ዋይት ናይል እና ሪቨር ናይል ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ ከተሞች ላይ በፈጸማቸው ጥቃቶች፤ የነዳጅ ማደያዎች፣ የውሃ ማቅረቢያዎች እና ድልድዮችን ማውደሙን አምባሳደሩ ከስሰዋል። በፖርት ሱዳን የሚገኝ ወደብ፣ የነዳጅ እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች፣ ወታደራዊ የአየር ማረፊያ እና ፍላሚንጎ በተባለ ቦታ የሚገኝ ራዳር ጥቃት እንደተፈጸመባቸውም አል ሀሪትዝ አክለዋል።

በብሉ ናይል ግዛት እና በሮሳይረስ ግድብ የኃይል ማመንጫ ላይ ያነጣጠሩ የድሮን ጥቃቶች፤ “ከጎረቤት ሀገራት የተፈጸሙ ናቸው” ሲሉ የሱዳኑ አምባሳደር ወንጅለዋል። የሱዳኑ አምባሳደር በዚሁ ውንጀላቸው፤ በግንቦት ወር በሱዳን ግዛት ውስጥ ኾር አል-ደባብ በተባለ ቦታ የኢትዮጵያ ድሮን መመታቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

 አል ሀሪትዝ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ በሚገኝ ቦታ እንደተመታ የገለጹት ይኸው ድሮን፤ “የተለያዩ ቦታዎችን እና መንገዶችን ፎቶግራፍ ሲያነሳ ነበር” ሲሉ ከስሰዋል። ከእዚህ ሰው አልባ አውሮፕላን በተጨማሪ የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ የተሻገሩ ሶስት አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖችን በብሉ ናይል ግዛት ውስጥ መትቶ እንደጣለ ሲናገሩም ተደምጠዋል።

ድርጊቱ ተፈጽሞበታል የተባለው የብሉ ናይል ግዛት፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር የሚዋሰን ነው። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ አካባቢ በሚነሱ ድሮኖች፤ የመሐመድ ሐምዳን ደጋሎ ታጣቂ ቡድን በነዋሪዎች እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም አምባሳደር አል ሀሪትዝ ተጨማሪ ውንጀላ ለጸጥታው ምክር ቤት አቅርበዋል። 

በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ውንጀላዎቹን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገዋል። “የሱዳን ተወካይ በሀገሬ ላይ መሰረተ ቢስ ክስ ለመሰንዘር መወሰናቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው” ሲሉም አምባሳደር ተስፋዬ በትላንቱ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለው “ጥልቅ ወዳጅነት ተገቢውን ክብር በመስጠት”፤ ሱዳን የምታቀርበውን ክስ በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን በሚቀርቡ ዘገባዎች ላይ አስተያየት ከመስጠት እንደተቆጠበ አምባሳደር ተስፋዬ አስረድተዋል። በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የሚሳተፉ “የተወሰኑ ወገኖች” በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት እና ብሔራዊ ደህንነት ላይ “ከባድ ጥሰቶች” እየፈጸሙ መሆኑንም አምባሳደሩ አስታውቀዋል። 

ለዚህም ችግር ቢሆን በሁለትዮሽ የግንኙነት መንገዶች መፍትሔ ለማበጀት መንግስታቸው ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አምባሳደር ተስፋዬ ለጸጥታው ምክር ቤት ገልጸዋል። በሁለቱ ሀገራት የጋር የድንበር አካባቢዎች እየባሰ የመጣው የጸጥታ እጦት፤ መላ ቀጠናውን የበለጠ ሊያናጋ እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።

በክፍለ አህጉሩ የሚገኙ ሀገራት፤ የጎረቤቶቻቸውን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶችን ለመፈጸም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማረጋገጥ እንዳለባቸውም አሳስበዋል። አምባሳደር ተስፋዬ “የአፍሪካ ቀንድን የማተራመስ ፖሊሲያቸውን ለማስፈጸም በሱዳን ያለውን ግጭት ለመጠቀም የሚፈልጉ ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን” ሲሉም ለጸጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ለዚህ በማጣቀሻነት ያነሱት፤ የድሮን የጦር ሰፈርን በመጠቀም ጭምር በእርስ በእርስ ጦርነቱ በግልጽ እና በንቃት የሚሳተፍ የሱዳን ጎረቤት መኖሩን የሚጠቁሙ ዘገባዎችን ነው። ከዚሁ ጎረቤት ሀገር በአየር እና በከባድ መሳሪያ በሱዳን ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት፤ ሰላማዊ ሰዎች እና ባህላዊ የወርቅ አውጪዎች መገደላቸውን አንስተዋል። 

“የአፍሪካ ቀንድን የማተራመስ ፖሊሲያቸውን ለማስፈጸም በሱዳን ያለውን ግጭት ለመጠቀም የሚፈልጉ ወገኖች እንዳሉ እናውቃለን”

አምባሳደር ተስፋዬ ጥቃት ፈጻሚውን ሀገር በስም ባይጠቅሱም፤ ቢያንስ 72 ወርቅ አውጪዎች ለተገደሉበት ያለፈው ሳምንት ጥቃት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተጠያቂ ያደረጉት ግብጽን እንደሆነ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። መቀመጫውን በካርቱም ያደረገ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን፤ በሱዳን ግዛት ውስጥ ባለ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት “የግብጽ ተዋጊ ጀቶች ናቸው” ብሏል።

“የሱዳናውያን ህይወት ዋጋ ቢስ መሆን የለበትም” ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፤ በሰላማዊ ሰዎች እና በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በምንም አይነት የጸጥታ አመክንዮ ተቀባይነት እንደማይኖረው ለጸጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል። የሱዳን ቀውስ በራሳቸው በሱዳናውያን ባለቤትነት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚያወሳስቡ ድርጊቶችን ኢትዮጵያ እንደምታወግዝም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽን ያሳተፈው የትላንትናው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ፤ የተወሰነው ክፍል በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ ነበር። የስብሰባው የማጠቃለያ ክፍል በዝግ የተከናወነ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

We are hiring!