የ68 ዓመቱ የቀድሞው የፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሐቪስቶ፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በይበልጥ የሚታወቁት በትግራይ ጦርነት ወቅት ይሰጧቸው በነበሩ ቀጥተኛ እና አነጋጋሪ አስተያየቶች ነበር። በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ወራት የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዩ ልዑክ የነበሩት ሐቪስቶ፤ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በተደጋጋሚ በመገናኘት ለግጭቱ መፍትሔ ለማበጀት ሲጥሩ ከርመዋል።
በዚሁ ኃላፊነታቸው ወቅት የትግራይ ክልልን የመጎብኘት ዕድል አግኝተው የነበሩት ሐቪስቶ፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው ስምምነት ሲፈረምም ሂደቱን በቅርበት ተከታትለዋል። ሐቪስቶ ከፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ከተሰናበቱ ከሶስት ዓመት በኋላም ይህንኑ ማድረጉን አልተውም።
አንጋፋው ዲፕሎማት ከሁለት ቀናት በፊት በፊንላንድ ዋና ከተማ ሂልሲንኪ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር አጠር ያለ ቆይታ ባደረጉበት ወቅትም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ሐቪስቶ በትግራይ ክልል ላለው ቀውስ “ሰላማዊ እልባት” ይገኛል የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም፤ በሱዳን ያለው ጦርነት በጎረቤት ሀገራት ላይ “አለመረጋጋትን መቀስቀሱ” እና “ከድንበር የተሻገረው” ተጽዕኖው ያሳስባቸዋል።
ሐቪስቶ የሱዳን ጉዳይ የሚያስከትለውን ጣጣ በአጽንኦት ለማንሳት ምክንያት አላቸው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖችን እንዲያሸማግሉ የግል ልዑካቸው አድርገው ከሶስት ወር በፊት የሾሟቸው ሐቪስቶን ነው። ሐቪስቶ በሱዳን ጦርነት ተሳታፊ ከሆኑ ኃይሎች፣ ከቀጠናው ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅርበት በመስራት በሀገሪቱ የሲቪል አስተዳደር እንዲመሰረት ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
“የሱዳን ጉዳይ ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዳይዛመት መፍትሔ መፈለግ ያሻል። የሱዳን ቀውስ በዚሁ ከቀጠለ ለመላው ቀጠና፣ ለቻድ፣ ለደቡብ ሱዳን፣ ለኢትዮጵያ፣ ለሊቢያ ሳይቀር መዘዝ ይኖረዋል” ሲሉ ሐቪስቶ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እነዚህ ሀገራት ድንበር አቋርጠው በፈለሱ የሱዳን ስደተኞች አማካኝነት አሁንም ቢሆን እየተጎዱ መሆኑንም አክለዋል።
“የኢኮኖሚ ልማቱ እየተጎዳ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ሌሎች ተጽዕኖዎች አሉ። በተለይም በሰብአዊ እና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች፤ ጎረቤት ሀገራት ለሱዳን ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኙ መስራታቸው አስፈላጊ ነው” ሲሉ የመንግስታቱ ድርጅት የሱዳን ልዑክ አሳስበዋል።

የሱዳን ጎረቤቶች ለአገሪቱ ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) የጦር መሳሪያ ማቅረብን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ በማድረግ ጦርነቱን እያባባሱ እንደሚገኙ የዓለም አቀፍ ተቋማት ትንታኔዎች እና የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይፋ አድርገዋል። በሌተናል ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሀን የሚታዘዘው የሱዳን ጦር ሰራዊት እና በመሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ውጊያ የጀመሩት በሚያዝያ 2016 ዓ.ም. ነበር።
ለድፍን ሶስት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ባስከተለው ረሃብ እና በተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር፤ የሱዳን ጦርነት በዓለም ትልቁ ሰብአዊ ቀውስ ለመሆን እንደበቃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በተደጋጋሚ ሲያሳስብ ቆይቷል። ድርጅቱ ከሱዳን ሕዝብ 19.5 ሚሊዮን የሚሆነው የምግብ እጥረት ቀውስ እንደገጠመው በተያዘው ግንቦት ወር አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































