የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ለቀጣዩ ምርጫ በዕጩነት ካዘጋጃቸው ተወዳዳሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ ከአንድ ቀን እስር በኋላ ተፈቱ። አቶ የሺዋስ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 4፤ 2018 ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ ተፈትተው በስልክ እንዳነጋገሯቸው የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በተለያዩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ለረዥም ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው አቶ የሺዋስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ ትላንት ማክሰኞ ከቀኑ 8 ሰዓት ገደማ እንደነበር የኢሕአፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይስሀቅ ወልዳይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ገልጸዋል። አቶ የሺዋስ የተያዙት ከመኖሪያ ቤታቸው ውጭ ባለ ስፍራ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል።
ፖሊስ ፖለቲከኛውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ወደሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዳቸው ማረጋገጣቸውን ጉዳዩን ሲከታተሉ የቆዩት አቶ ይስሀቅ ተናግረዋል። ኢሕአፓ ዛሬ ረፋድ ላይ ባወጣው አጭር መግለጫ፤ በቅርቡ ፓርቲውን በተቀላቀሉት በአቶ የሺዋስ ላይ የተወሰደውን የእስር እርምጃ ተችቷል።

የአቶ የሺዋስ እስር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ዜጎች ላይ “በመንግስት እየደረሰ ያለውን አፈና” ከሚያሳዩ “ተቆጥረው የማያልቁ ድርጊቶች” ውስጥ አንዱ እንደሆነ ፓርቲው በመግለጫው ላይ አስፍሯል። የእስር እርምጃው መጪው ምርጫ “ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል” ከተባለው “በተቃራኒ እንደሚሆን አመላካች ነው” ሲል ኢህአፓ ኮንኗል።
ለአንድ ቀን በእስር ላይ የቆዩት አቶ የሺዋስ፤ ኢሕአፓ አባል የሆነበትን “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘ የፓርቲዎች ቅንጅት በመወከል በዘንድሮው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ነበሩ። አቶ የሺዋስ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ የምርጫ ክልል ሊወዳደሩ መታጨታቸውን እና ለዚህም በምዝገባ ሂደት ላይ መሆናቸውን የኢሕአፓው ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ የሺዋስ በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ሳይነገራቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ዛሬ ከሰዓት መለቀቃቸውን ተናግረዋል። “ሲታሰሩም ሲፈቱም ያለምክንያት ነው” ያሉት አቶ አብርሃም፤ ይህ አይነቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞችን “የማሰር እና የማዋከብ” ድርጊት በምርጫው ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።

በመጪው ግንቦት መጨረሻ የሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወራት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት፤ ከኢሕአፓ በተጨማሪ ሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አባሎቻቸው መታሰራቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲ ይጠቀሳሉ።
የኢዜማ የፓርላማ አባል የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በርታ ይህንኑ ጉዳይ ባለፈው ሳምንት በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ አንስተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት በዚህ የፓርላማ ስብሰባ ላይ፤ የህግ ሂደቱን ባልተከተለ ሁኔታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላቶች በዘፈቀደ እስር፣ ማዋከብና ማንገላታት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ዶ/ር አብርሃም ተናግረዋል።
ከታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል የኢዜማ አባላት ጭምር እንደሚገኙበት የፓርላማ አባሉ በዚሁ ስብሰባ ላይ ጠቅሰዋል። በስብሰባው ላይ ምርጫን በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የአሁኑ ምርጫ ካለፈው የተሻለ እንደሚሆን ማረጋገጫ ለመስጠት ሞክረው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አንዳንዶች ሰግታችኋል፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ መልሴ በውጤት እንየው ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። እርሳቸው ይህን በተናገሩ በሳምንቱ፤ ኢዜማን ከምስረታው ጀምሮ በሊቀመንበርነት ሲመሩ ቆይተው በስተኋላ ላይ ራሳቸውን ከፓርቲው ያገለሉት አቶ የሺዋስ መታሰራቸው ይፋ ተደርጓል።
አቶ የሺዋስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውሉ የትላንቱ የመጀመሪያቸው አይደለም። ፖለቲከኛው ከእዚህ እስራቸው አስቀድሞ በቁጥጥር ስር ውለው የነበረው፤ “ሁከት በመቀስቀስ” ወንጀል ተጠርጥረው ነበር። አቶ የሺዋስ ከአንድ ሳምንት እስር በኋላ የተፈቱት የመታወቂያ ዋስ በማስያዝ እንደነበር ይታወሳል።
በግንቦት 2016 ዓ.ም. የተከናወነው የአቶ የሺዋስ እስር፤ በዚያው ዓመት ህዳር ወር ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ ከነበረ ሰላማዊ ሰልፍ ጋር በተያያዘ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። “የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ” በሚል መሪ ቃል ለህዳር 30፤ 2016 ተጠርቶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ ከነበሩት እና በስተኋላ ላይ ከታሰሩ ፖለቲከኞች ውስጥ አቶ የሺዋስ ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























