በጦርነት ስጋት ከትግራይ ክልል ወጣቶች እየሸሹ ነው

የመቐለ ከተማ ነዋሪው እዮብ* እና ቤተሰቦቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመለከቷቸውና የሚሰሟቸው ወሬዎች፤ በልባቸው ውስጥ አንድ “ትልቅ ስጋት” ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጓል። “ዳግም ጦርነት ሊጀመር ይችላል” የሚለው ስጋት በቤታቸው ውስጥ ጥላውን አጥልቷል።

ስጋታቸውን ይበልጥ ያገነነው፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወላጅ አባታቸው ለሕክምና ክትትል ወደ አዲስ አበባ ካቀኑ በኋላ ለመመለስ በሚሰናዱበት ወቅት ያጋጠማቸው ነገር ነው። በወቅቱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተላከ አጭር የጽሑፍ መልዕክት፤ አባታቸውን ይዞ ወደ መቐለ የሚመጣው በረራ መሰረዙን የገለጸ ነበር።

የአየር በረራው መሰረዝ የጉዞ ቀናትን ከማስተጓጎል ባለፈ፤ አባት ከሶስት ዓመት በፊት የነበረው ጦርነት “ልጆቼን ይበላብኛል” በሚል በጭንቀት ያሳለፏቸውን አስከፊ ቀናት መልሶ አምጥቶባቸዋል። ለቀናት የተቋረጠው በረራ መጀመሩ በተሰማ ማግስት፤ አባት አዲስ አበባ ላይ አንድም ቀን ሳያድሩ ቤተሰቦቻቸው ወደ አሉበት ከተማ አቀኑ።

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

ካንዣበበው የጦርነት ደመና ልጆቻቸውን ለማስመለጥ ለምክክር እንኳ ጊዜ ማባካን ያልፈለጉት አባት፤ በመቐለ ከተማ ያሉትን ሰብስበው ሳይዘገዩ ትኬት እንዲቆርጡ ትዕዛዝ ሰጡ። “መቼ ከእዚያ እንደምንወጣ አናውቅም እንጂ፤ እዚያ እንደማንቆይ እናውቅ ነበር” ይላል እዮብ የዚያን ዕለት የአባቱን ሁኔታ ሲያስታውስ።

የእነ እዮብ አባት ስጋት “ልጆቼ ለውትድርና ሊወሰዱብኝ ይችላሉ” የሚል ነው። እናም የአባታቸውን ትዕዛዝ በመቀበል እዮብን ጨምሮ ሶስት ወንድማማቾች፤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 5፤ 2018 ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ የአየር ትኬት ለመቁረጥ ወሰኑ።

ወንድማማቾቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሞባይል መተግበሪያን ሲከፍቱ የተመለከቱት ግን ይበልጥ ስለ ጦርነቱ ስጋት እንዲገባቸው ያደረገ ነበር። ወደ አዲስ አበባ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የሚደረጉ በረራዎች መሙላታቸውን ከሞባይል መተግበሪያው የተረዱት ወንድማማቾቹ፤ ከየካቲት 10 ጀምሮ ወንበር ባገኙባቸው በተለያዩ ቀናት በሚነሱ በረራዎች ለመጓዝ ትኬት ለመቁረጥ ተገደዱ። 

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

እድሜያቸው ከ26 እስከ 29 ከሚሆኑት ወንድማማቾች፤ ወደ አዲስ አበባ የመጓዝ ዕድልን በማግኘት የመጀመሪያው የሆነው ታናሽ የሆነው እዮብ ነው። ለባለፈው ማክሰኞ የካቲት 10 በተገኘ ትኬት፤ ከአውሮፕላን ላይ ተሳፍሮም እንኳ ስጋቱ አልቀቀውም። ስጋቱ ከመቐለ ከተማ ከመውጣታቸው በፊት “ጦርነት ቢነሳስ?” የሚል ነበር።

“ብዙ ሰው አላመነም”

በማግስቱ ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው የእዮብ ወንድምም፤ እርሱን ጨምሮ በአውሮፕላን ውስጥ አብረውት የነበሩት ተጓዦች በረራው እስኪደርስ ጭንቀት ይነበብባቸው እንደነበር ይገልጻል። አብዛኞቹ አውሮፕላኑ እስኪነሳ እየጠበቁ በነበረበት ወቅት፤ “በረራ ቢቋረጥስ?” የሚል ስጋት ሰቅዞ ይዟቸው እንደነበር ያስረዳል። አውሮፕላኑ መቐለን ለቅቆ እንደሚወጣ “ብዙ ሰው አላመነም” ነበር ሲል ያክላል።  

እስከሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ድረስ ያሉት በረራዎች መሙላታቸውን የተረዱት የእነ እዮብ ጓደኞች በበኩላቸው፤ እስከዚያው ከመጠበቅ በአውቶብስ ለመጓዝ ወስነዋል። ሆኖም የአውቶብስ ትኬት ለማግኘት ሲያጠያይቁ የጠበቃቸው እጥፍ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ነበር። አማራጭ ያልነበራቸው አምስት የእዮብ ጓደኞች፤ ከመደበኛው የአውቶቡስ ታሪፍ እጥፍ ስድስት ሺህ ብር ከፍለው በ“ሃይሩፍ” ሚኒባስ የሌሊት ጉዞ ለማድረግ ተገድደዋል።   

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

እዮብ አንደኛው ወንድሙ እና ጓደኞቹ ወደ አዲስ አበባ በሰላም በመግባታቸው ደስተኛ ቢሆንም፤ ከነገ በስቲያ እሁድ በአውሮፕላን ለመምጣት እየተዘጋጀ ያለውን ታላቅ ወንድማቸውን እስኪቀበሉት ግን አሁንም ስጋት እንደተጫነው ነው። በሁለት ቀናት ውስጥ ተከታትለው አዲስ አበባ የገቡት እዮብ እና ወንድሙ፤ አሁን ያሉት ዘመድ ጋር ተጠግተው ነው።

ወንድማማቾቹ በከተማይቱ እስከመቼ እንደሚቆዩ እርግጠኛ ባይሆኑም፤ የኪራይ ቤት በመፈለግ ላይ ናቸው። “እስከ መቼ ዘመድ ጋር ትቀመጫለሽ? ሰው ቢታገስሽና ባይሰለችሽ እንኳን ለሦስት ቀን ወይም ለአንድ ሳምንት ብቻ ነው” ይላል እዮብ መኖሪያ ቤት ማፈላለግ ስለጀመሩበት ምክንያት ሲያስረዳ። 

የቤት ኪራይ ዋጋ በየዕለቱ በሚንርባት አዲስ አበባ፤ ካላቸው ውስን ገንዘብ ጋር የሚመጣጠን መጠለያ ማግኘት ሌላ ፈተና ሆኖባቸዋል። ወንድማማቾቹ በዘመድ ጭምር ቤት ሲያፈላልጉ ቆይተው ከቀናት ፍለጋ በኋላ በወር 16 ሺህ ብር የሚከፈልባት “ስቱዲዮ” ከከተማው ጥግ ካሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንደሚኒየሞች) መካከል በአንዱ አግኝተዋል።

ሆኖም ይህ ክፍያ የተለየ የገቢ ምንጭ ለሌላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወጣቶች የሚቀመስ አይደለም። ይህም ሆኖ ወንድማማቾቹ ዳግም የጦርነት ስጋት ካንዣበበበት ክልል ርቀው፣ እምብዛም መግቢያ መውጪያዋን በማያውቋት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ሆነው፣ ከቀናት በኋላ የሚመጣውን ታላቅ ወንድማቸውን እየተጠባበቁ ነው።

“ወጣቱ በብዛት እየወጣ ነው”

በረከት* ከመቐለ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከመጣ አንድ ሳምንት ሆኖታል። በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እና የፖለቲካ ሽኩቻ “በጣም ስለሚያስፈራ እሱን በመሸሽ ነው የመጣሁት” ይላል በረከት ወደ አዲስ አበባ የመጣበትን ምክንያት ሲያስረዳ። ከዚህ ቀደም የነበረው ጦርነት ባስከተለው “ችግር ላይ ሌላ ችግር ተደራርቦ ማየት ስለማንፈልግ፤ የበፊቱንም ስለምናውቅ ነው [የሸሸነው]” ሲል ምክንያቱን ያጠናክራል።

ከሶስት ዓመት በፊት በነበረው ጦርነት ብዙ ነገሩን ያጣው በረከት፤ የተትረፈረፈም ባይሆን ራሱን የሚያኖርበት የንግድ ስራ ነበረው። “አንድ ቦታ ላይ ስትኖር የሰላም አየር ከሌለ ብትሰራም satisfaction የለውም። ስለዚህ ያለህ አማራጭ ሰላም ያለበት ቦታ ሄደህ፣ በሙያህ እንኳን ባትሰራ ለምን የጉልበት ስራ አይሆንም [ትኖራለህ]። ‘የፈለገው ይምጣ። ሰላም ካለ ችግር የለውም። ያገኘሁትን እሰራለሁ’ በሚል ነው በሽሽት የመጣሁት” የሚለው በረከት በአዲስ አበባ ከተማ ስራ እየፈለገ እንደሆነ ገልጿል።

ከመቐለ ከተማ የቻለ ቤተሰቡን ጨምር ይዞ ሲወጣ ሌላው ልጆቹን እያስወጣ እንደሚገኝ የሚገልጸው በረከት፤ “አማራጭ የሌለው ሰው ብቻ ነው እየቀረ ያለው” ሲል ነዋሪው ከጦርነት ለመሸሽ ያሉትን ሁሉ አማራጮች እየተጠቀመ እንደሆነ ይናገራል። “ወጣቱ በብዛት እየወጣ ነው” ሲልም የዓይን እማኝነቱን ሰጥቷል።

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

በረከት እንደሚለው ወጣቱ ከክልሉ ወጥቶ የሚሸሽበት ዋናው ምክንያት፤ ጦርነት ከተጀመረ “አፍሰው ለጦርነት ይማግዱናል” ብሎ ስለሚሰጋ ነው። “ቤተሰብ ትንንሽ ልጆችን ጭምር የዚያ ሰለባ እንዳይሆኑ በሚል ስጋት እያስወጣ ነው። ቅድም ራሱ ልጆቿን እንዳለ ወደዚህ እየላከች እንደሆነ ልትነግረኝ የደወለችልኝ ልጅ አለች። ኤለመንተሪ ነው የሚማሩት። ‘እኛ የሚገጥመንን ነገር face እናደርጋለን። ልጆቼን ግን እየላክኹ ነው’ እያለችን ነበር” በማለት ስለለው ስጋት ያብራራል።

ከመቐለ በአውቶቡስ የመጣው በረከት፤ የትራንስፖርት ነገር አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግሯል። መደበኛው የአውቶቡስ ታሪፍ ሶስት ሺህ ብር ገደማ ቢሆንም በዚህ ዋጋ ትኬት ማግኘት ግን “ብዙም የማይታሰብ ነው” ይላል። እርሱ ትኬት ለሚሸጡት “የሻይ ቡና” ሰጥቶ፤ በታሪፍ ትኬት ማግኘቱን እንደ እድለኛነት ቆጥሮታል።

“ትኬት አለቀ ትባላለህ። ነገር ግን ውጭ ላይ ነው ትኬት የሚሸጠው። በየመንገዱ አለ፤ ግን ውድ ነው። አንተም ያው ቶሎ መውጣት አለብኝ ብለህ ስለምታስብ መስዋዕትነት ትከፍላለህ። መደበኛው 3,010 ብር ነው። ውጭ ላይ 5 ሺህ፣ 8 ሺህ፣ ከ15 እስከ 30 ሺህ ይሸጣል። በብዛት ትንንሽ መኪኖች ናቸው እስከ 30 ሺህ የሚጠይቁህ። ሁኔታውን እያዩ ይጠቀሙብሃል። ከእኔ ጋር የመጡ፤ 8 ሺህ እና 15 ሺህ የቆረጡ አሉ” ሲል በረከት በጉዞው የታዘበውን ያጋራል።

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

“ትምህርት ጭምር አቋርጠው ነው እየወጡ ያሉት”

ነዋሪነቱ በመቐለ ከተማ የሆነ ጋዜጠኛ፤ በትግራይ ክልል “ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ነው” የሚለውን ስጋት ተከትሎ “ሰዎች በብዛት እየወጡ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። ከክልሉ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ የአየርም፣ የየብስም ትራንስፖርት አማራጮች “በጣም ቢዚ ናቸው” ያለው ጋዜጠኛው፤ “በአውሮፕላንም፣ በባስም ብዙ ሰው እየወጣ ነው” ሲል ያለውን ሁኔታ ያስረዳል።

ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቃላቸውን እንደሰጡት የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ሁሉ፤ ጦርነትን በመስጋት ከትግራይ ክልን በብዛት እየወጡ ያሉት ወጣቶች ስለመሆናቸው ይናገራል። በፍጥነት መውጣት የሚፈልጉ ወጣቶች፤ በክልሉ የአውሮፕላን ትኬት ለማግኘት ቀናትን ላለመጠበቅ ሲሉ “ወደ አፋር ክልል ሰመራ በመኪና ሄደው ከዚያ በአውሮፕላን ይጓዛሉ” ይላል ጋዜጠኛው።

አውቶብስም እንደልብ እንደማይገኝ እና ትኬት ቆርጦ ለመሄድ ቀናትን ሊያስጠብቅ እንደሚችል የሚናገረው ጋዜጠኛው፤ በዚህ ምክንያት በመለስተኛ ተሽከርካሪዎች አቆራርጠው ወደ አፋር የሚገቡ ወጣቶች እንዳሉ ይገልጻል። ወጣቶቹ “ትምህርትም ጭምር አቋርጠው ነው እየወጡ ያሉት” ሲልም የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጭምር ከክልሉ እየሸሹ መሆኑን ያብራራል።

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

ዩኒቨርሲቲ የሚማር ወንድም እንዳለው የሚገልጸው ጋዜጠኛው፤ ቤተሰባቸው ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ እንዲሄድ እየወተወቱት እንደሆነ በግል የገጠመውን አካፍሏል። “ትንሽ ሁኔታውን እንየው እና ካልሆነ ይሄዳል ብዬ ነው ያረጋጋኋቸው” ሲልም ቤተሰቡ በጭንቀት ላይ እንደሆነ ያክላል።

በትግራይ ክልል ስላለው የጦርነት ስጋት ጋዜጠኛው ሲያስረዳ “የኢትዮጵያ ሰራዊት ተጠግቷል። በትግራይ በኩልም ዝግጅቶች አሉ። በቀበሌም ሰው እያዘጋጁ ነው። በየቀበሌው ‘ለጦርነት ተዘጋጁ’ ተብሎ ተነግሯል” ብሏል። 

ከመቐለ ውጭ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

ለደህንነቱ በመስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የተምቤን ነዋሪ፤ “ለወትሮው በወጣቶች እንቅስቃሴ ትታወቅ የነበረችው” የአቢ አዲ ከተማ ከሰሞኑ መቀዝቀዟን ይናገራል። “በአሁኑ ወቅት በመዝናኛ ቤቶች እና በቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ወጣቶችን ማየት አይቻልም” የሚለው ነዋሪው፤ ወጣቶች ከአካባቢው እየወጡ ስለመሆናቸው ይገልጻል። 

ፎቶ፦ ከድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን የተወሰደ

የአካባቢው ወጣቶች “አቅም ያለው ወደ አረብ ሀገር ሌላው አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ መሀል ሀገር በመፈናቀል ላይ ናቸው” ይላል ነዋሪው። የወጣቶቹ ፍልሰት ከሚሰማው እና ካለው ሁኔታ በመነሳት “ጦርነት አይቀሬ ነው” በሚል ድምዳሜ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስረዳል። 

በተመሳሳይ ስጋት ሁለት ወንድሞቹ አዲግራት ከተማን ለቅቀው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን፤ ነዋሪነቱን በመዲናይቱ ያደረገ የከተማይቱ ተወላጅ ይናገራል። በደህንነት ስጋት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ይኸው የአዲግራት ተወላጅ ወንድሞቹን ከሁለት ወራት በፊት ወደ አዲስ አበባ ያስመጣው፤ “የህወሓት ሰዎች እድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎችን ለውትድርና በግዳጅ መመልመል በመጀመራቸው ነው” ይላል።  

በቅጥር ስራ የሚከፈለው ወርሀዊ ደመወዝ እንኳን ወንድሞቹን ጨምሮ ለራሱም በቂ ባይሆንም፤ “ወንድሞቼ የሚጋፈጡት ፈተና ከችግሬ አይበልጥም” በማለት ካመጣቸው ወንድሞቹ ጋር “እንደ ምንም አብቃቅተው” እየኖሩ መሆኑን ተናግሯል። የኤርትራ ወታደሮች “አዲግራት ከተማን አልፈው ወደ መሀል ትግራይ በመግባት ላይ እንደሆኑ” በስፍራው ካሉ ቤተሰቦቹ መስማቱን የሚገልጸው ይኸው ግለሰብ “ነዋሪው ጭንቀት ላይ ነው” ሲል የትውልድ ቦታውን ሁኔታ ያስረዳል።

ፎቶ፦ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል

የኤርትራ ወታደሮች በቅርቡ ወደ ተምቤን አካባቢ እንደገቡ የሚገልጹ መረጃዎችን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበለት የአቢ አዲው ነዋሪ በበኩሉ፤ እርሱም ይህንኑ መስማቱን ገልጿል። ከነመለዮአቸው የሚንቀሳቀሱ የኤርትራ ወታደሮችን እስካሁን እንዳልተመለከተ የሚናገረው ነዋሪው፤ ሆኖም “ሲቪል ለብሰው በከተማዋ ውስጥ እና ዙሪያዋ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ” ብሏል።

የኤርትራ ወታደሮች ስለመሆናቸው እንዴት እርግጠኛ እንደሆነ ለተነሳለት ጥያቄ “በአነጋገራቸው እና በጫማቸው” እንደሚለዩ ያስረዳል። “ሲቪል የለበሱ የኤርትራ ወታደሮች” በብዛት የታዩት፤ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የካቲት 4 እና ቅዳሜ የካቲት 7 በነበረው ገበያ ለሸመታ በወጡበት አጋጣሚ እንደሆነም አብራርቷል።

በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት እና የጦርነት ስጋትን ሸሽተው የሚወጡ ነዋሪዎችን በተመለከተ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ እና ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይህንኑ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበለት ጥያቄ፤ በትግራይ ክልል ስላለው የጦርነት ስጋት እና የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አስተያየት ለመስጠት “ዝግጁ እንዳልሆነ” ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ * በዚህ ዘገባ የጠቅሰናቸው ነዋሪዎችን ሙሉ ስም ያልተጠቀምነው፤ በግለሰቦቹ ጥያቄ መሰረት መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን]