ከትግራይ ክልል ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበት መርሃ ግብር በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። በመርሃ ግብሩ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ላይ 400 ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮሚሽኑ ገልጿል።
ከተሳታፊዎቹ ውስጥ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች እንደሚገኙበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናግረዋል። ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን በክልሉ ለማካሄድ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ህወሓት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ አመልክተዋል።
ኮሚሽነሩ ከአንድ ወር በፊት ከፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በነበራቸው ስብሰባ፤ “በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሀገራዊ ምክክር ማካሄድ ቅንጦት ነው” የሚል ምላሽ ከህወሓት እንደሰጣቸው ተናግረው ነበር። ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬው መግለጫቸው “የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አሁንም በሩን ዘግቶብናል ብለን አንጠብቅም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የትግራይ አጀንዳ ማሰባሰብ መድረክም በአዲስ አበባ ለማካሄድ ቢወስንም፤ ቀጣይ ስራዎችን ለማከናወን በክልሉ ውስጥ ተንቀሳቅሶ መስራቱን እንደሚቀጥል አክለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎቹን ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች አከናውኖ አጠናቅቋል።
ከመጪው ሳምንት ረቡዕ መጋቢት 23 እስከ አርብ መጋቢት 25 ድረስ በአዲስ አበባ በሚካሄደው መድረክ፤ የትግራይ ተወላጆች በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የምክክር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የሚያቀርቡ ይሆናል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በሀገር አቀፍ ጉባኤ ላይ የሚወክሏቸውን ተወካዮችም ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































