ለሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚቀርቡ የትግራይ ክልል አጀንዳዎች የሚሰባሰቡበትን መድረክ፤ በአዲስ አበባ ማካሄድ በአማራጭነት መያዙን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ። ኮሚሽኑ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተራዘመለት የስራ ዘመን ሊጠናቀቅ በመቃረቡ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የምክክር ጉባኤ “በፍጥነት” እንዲጀምር ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል።
ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ትላንት አርብ ጥር 29፤ 2018 የገመገመው የተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። የኮሚሽኑን የመንፈቅ ዓመት የስራ ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት፤ የተቋሙ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ናቸው።
ፕሮፌሰር መስፍን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አጀንዳዎችን እና ተወካዮችን የማስመረጡ ስራ ከትግራይ ክልል ውጪ ባሉ ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳድሮች ተጠናቅቋል። ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲሳተፉ ለማድረግ ኮሚሽኑ ያስቀመጠው እቅድ 93 በመቶ መሳካቱንም ዋና ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።
የእቅድ አፈጻጸሙ በቁጥር ደረጃ ከሚጠበቀው በላይ የተከናወነ ቢሆንም፤ የትግራይ ጉዳይ ግን በቁጥር ደረጃ ብቻ ሊታይ የሚገባው አለመሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን በትላንቱ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። ይህንን ታሳቢ በማድረግም የትግራይ ክልል ወደ ሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲመጣ፤ ላለፉት አራት ዓመታት ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
በትግራይ ክልል የምክክር መድረክ ለማካሄድ፤ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ከተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በተደጋጋሚ ውይይቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም ለማሳያነት አንስተዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ከነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ጊዜ ጀምሮ ምክክሩን ለማድረግ ሲከናወኑ የነበሩ ጥረቶች አሁንም መቀጠላቸውን ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ሆኖም ህወሓት ባለፈው ታህሳስ ወር በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት የምክክር መድረክ ማካሄድ “ቅንጦት ነው” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገልጸዋል። ህወሓት ለኮሚሽኑ የሰጠው ምላሽ ተስፋ እንደማያስቆርጣቸው ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በክልሉ የምክክር መድረክ ለማካሄድ እና አጀንዳ ለማሰባሰብ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አብራርተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም፤ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ታች ያለውን ማህበረሰብ ጨምሮ ሁሉንም ያሳተፈ ምክክር ማድረግ የሚቻለው “በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሆነ እናምናለን” ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ የአጀንዳ ማሰባሰቡን በክልሉ ማድረግ ካልተቻለ በአዲስ አበባ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
“አሁን ባለው ሁኔታ ትግራይ ላይ ምክክሩን ማስኬድ የምንችልበት ሁኔታ ‘በትክክል አለ ወይስ በፍጹም ተዘግቷል’ የሚለውን፤ በቀናት ውስጥ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደን ካገኘናቸው ከእሳቸው የምንሰመው ይሆናል። እርሳቸው ትግራይ ውስጥ የሚካሄድበት መንገድ ‘አስቸጋሪ ነው’ የሚሉን ከሆነ እና እዚያ ማድረግ ካልተቻለ ግን ሌሎች አማራጮችን እንከተላለን” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ መስፍን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ካሉት 11 ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዘገየ አስፋው በበኩላቸው “ህወሓት መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሞ ‘አልመጣም ቢል፤ እሱ እስከሚመጣ የኢትዮጵያ ህዝብ መያዣ መሆን የለበትም። ቀልብ ገዝቶ ከመጣ በሩ ክፍት ነው። ‘እሱን በመጠበቅ እንዘግይ’ የሚል አቋም የለም” ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተዋል።
“ህወሓት መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆሞ ‘አልመጣም ቢል፤ እሱ እስከሚመጣ የኢትዮጵያ ህዝብ መያዣ መሆን የለበትም። ቀልብ ገዝቶ ከመጣ በሩ ክፍት ነው። ‘እሱን በመጠበቅ እንዘግይ’ የሚል አቋም የለም”
አቶ ዘገየ ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤውን በቶሎ እንዲካሄድ ከፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ለተሰጠው ማሳሳቢያም ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተራዘመለት የስራ ዘመን ሊጠናቀቅ 19 ቀናት ብቻ መቅረቱን የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረኩ በፍጥነት እንዲያካሄድ በትላንቱ ስብሰባ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ለዓመታት የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሟን ያስታወሱት አቶ ዘገየ፤ “በጥድፊያ” “ውሽልሽል” የምክክር መድረክ እንድታዘጋጅ ከተደረገች “በታሪክ ተወቃሽ እንሆናለን” ሲሉ ተደምጠዋል።እየተካሄደ ያለው የምክክር ጥረት “ሁሉን አሳታፊ እና ሰፊ ሆኖ እያለ”፤ “በችኮላ ፍሬቢስ እንዳናደርገው” ሲሉም ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
“ይሄንን በታላቅ ተስፋ ህዝብ እየጠበቀው ያለን ነገር ጊዜ አሳጥረን፣ ውሽልሽል የሆነ ነገር ብናቀርብ፤ ህዝብም፣ መንግስትም፣ እኛን አምነው ከጎናችን የቆሙ የውጭ ዜጎችም ሁሉ ሊታዘቡን ይችላሉ። እኔ እምለው ምንድን ነው? አታቻኩሉን። ኢትዮጵያ ያለ ምክክር ለስንት ዓመት ኖራለች። ለአንድ ዓመት ብትኖር የሚመጣባት መዓት የለም” ሲሉ ኮሚሽነር ዘገየ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር በበኩላቸው ለሚመሩት ተቋም የተሰጠው ጊዜ የካቲት 17፤ 2018 የሚያበቃ ቢሆንም፤ “ተጨማሪ ጊዜ” እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል። ለሶስት ዓመት የቆይታ ጊዜ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ስራዎቹን በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ባለማጠናቀቁ ምክንያት የስራ ዘመኑ ለአንድ ዓመት መራዘሙ ይታወሳል።
ተቋሙ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር “ስኬታማ እንዲሆን ጊዜ ያስፈልጋል” ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን አጽንኦት ሰጥተዋል። ሀገር አቀፍ የምክክር መድረኩ መዘግየቱን በተመለከተ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ያነሷቸውን ጥያቄዎች እንደሚቀበሉት ነገር ግን “አሳታፊ እና አካታች የምክክር መድረክ ማድረግ አስፈላጊው ጉዳይ ነው” ሲሉ ሂደቱ ጊዜ የወሰደበትን ምክንያት አስረድተዋል።
በቀጣይ “ጊዜ ይፈልጋሉ” ከተባሉ የኮሚሽኑ ስራዎች መካከል፤ ለተቋሙ የቀረቡ አጀንዳዎችን “መልክ መልክ ማስያዝ” እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ምክክር የሚያቀላጥፉ አስተባባሪዎችን ማሰልጠን የሚሉት ይገኙበታል። በሀገር አቀፍ ምክክሩ እየተካሄደ ችግሮች ቢከሰቱ እንዴት እንደሚፈቱ፣ በምክክሩ ወቅት ከስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን የሚያስፈጽም አካል ጉዳይ፣ ጫፍ እና ጫፍ የወጡ ሀሳቦችን ማስታረቅ የሚቻልባቸውን መፍትሄዎች እንዴት መፈለግ ይቻላል የሚሉትም ከቀሪ ስራዎች መካከል ተጠቅሰዋል።

የትላንቱን የፓርላማ ስብሰባ ማጠቃለያ አስተያየት ያስደመጡት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በእስካሁን ቆይታው ለሌሎች ሀገራት ልምድ የሚሆን ስራዎችን መስራቱን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ሲቋቋም ግለሰቦች ሳይቀር እንዲሳተፉ በሚፈቅድ መልኩ መሆኑ እና አሳታፊ ውይይቶችን ማድረጉ “ህዝቡ ተስፋ እንዲኖረው አድርጓል” ሲሉም አሞግሰዋል።
ይሁንና “መፍትሔ ይመጣል” እያሉ በተስፋ የሚጠብቁ አካላት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ቶሎ ካልተደረገ “ተስፋ ወደመቁረጥ” ሊገቡ እንደሚችሉ ገልጸዋል። ብዙ ሀገራት የጀመሯቸው የምክክር መድረኮች ያልተሳኩት “መስቀለኛ ነገር እየገጠማቸው” እና “ምክክሮችን በቶሎ ባለመጀመራቸው” መሆኑን የጠቀሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው ምክክር ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መግባት ያለበት ጊዜ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
የሽግግር ፍትህን ጨምሮ ሌሎች ቀጣይ ስራዎችም “የምክክር መድረኩን መጀመር ይጠብቃሉ” ያሉት አቶ እውነቱ፤ የተወካዮች ምክር ቤት ሀገራዊ ምክክሩን “በዚህ ጊዜ ውስጥ ጀምሩ” ከሚል ኮሚሽኑ “ይህን ያህል ጊዜ ይሰጠን” ብሎ ቢያቀርብ የተሻለ እንደሚሆንም አመልክተዋል። ሆኖም በትግራይ የምክክር መድረክ የሚጀመርባቸውን መንገዶች በተመለከተ፤ ኮሚሽኑ እስከ የካቲት 17፤ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ ምልክቶችን ማሳየት እንደሚጠበቅበት አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































