ፌስታልን የሚተኩ ምርቶች እጥረት እና መወደድ ሸማቾች እና ነጋዴዎችን አስቸግሯል  

ገነት ተስፋሁን በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፊጋ አካባቢ በግለሰብ ቤት ተቀጥራ የምትሠራ ወጣት ናት። ለሳምንት ፍጆታ የሚውል አትክልት እንድትገዛ ባለፈው እሁድ ረፋድ ላይ በአካባቢው አደባባይ ዙሪያ ወደሚገኘው “የእሁድ ገበያ” ትላካለች። የእቃ መያዣ ሳትይዝ ከቤት የወጣችው ገነት፤ ከረጢት መሰል ነገር ወደ ወደሚሸጡ ነጋዴዎች ተጠግታ ዋጋውን ስትጠይቅ የተሰጣት ምላሽ ወደ መጣችበት እንድትመለስ አስገድዷታል። 

እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥማት በጥቂት ብሮች ታገኘው የነበረው ፌስታል በመታገዱ ምክንያት፤ በምትኩ በገበያ ላይ ያለው  በ“ስስ ማዳበሪያ” የተሠራ የእቃ መያዣ ነው። የእዚህን መሰል እቃ መያዣዎች አነስተኛ የመሸጫ ዋጋ 60 ብር መሆኑ ሲነገራት፤ ወደ ቤት ተመልሳ ይህንኑ ለአሠሪዎቿ ማሳወቅ ነበረባት። ምርጫ ያልነበራቸው አሠሪዎቿ ለእቃ መያዣ ተጨማሪ ገንዝብ ከሰጧት በኋላ ነበር ወደ ገበያ ተመልሳ አትክልት መሸመት የቻለችው። 

ቦሌ ወደ ሚገኘው ሰን ሲቲ ሱፐርማርኬት ከትላንት በስቲያ ሰኞ ያቀናው አብነት ሲሳይ፤ ፌስታል በመከልከሉ ምክንያት ለገዛው ቆሎ እና ውሃ በመያዣነት የቀረበለት አማራጭ ካርቶን ብቻ መሆኑ አላስደሰተውም። “የሽያጭ ባለሙያዎቹ እቃ መያዣ እንዳለኝ ከጠየቁኝ በኋላ እንዳልያዝኹ ስነግራቸው ካርቶን እንድጠቀም ጠይቀውኝ ነበር” የሚለው አብነት፤ ካርቶኑ ትልቅ እና ለመያዝ አመቺ ባለመሆኑ ከሱፐር ማርኬቱ የገዛውን ቆሎ እና ውሃ በእጁ ይዞ መውጣቱን መርጧል።

ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀም፣ ማዘዋወር እና ማምረት እንዳይቻል የሚከለክለው አዋጅ ከጥር 23፤ 2018 ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ እንዲህ አይነት ቅሬታዎች እና አለመመቸቶች በተጠቃሚዎች ዘንድ ሲነገሩ በተደጋጋሚ ይደመጣል። 

በግንቦት 2017 ዓ.ም. በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ የጸደቀው “የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድን” የሚመለከተው አዋጅ፤ ለ13 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን ነባር ሕግ የተካ ነው። አዲሱ አዋጅ ከተዘጋጀባቸው ዓላማዎች አንዱ፤ “ለአካባቢ ብክለት የሚዳርጉ” እና “አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ምርቶች” በሥነ ምህዳር ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት መከላከል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ሆኖም ሸማቾች እና ነጋዴዎች፣ በፕላስቲክ ተኪ ምርቶች እጥረት እንዲሁም በተኪ ምርቶቹ የዋጋ ከፍተኛ መሆን ምክንያት መቸገራቸውንም እየገለጹ ይገኛሉ። ከሰባት ዓመታት በላይ በችርቻሮ ንግድ ሥራ የተሰማራው ሙደሲር ጀማል ከእነዚህ አንዱ ነው። 

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አራብሳ አካባቢ ጨርቆስ ተብሎ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በአንዱ ህንጻ ስር በሚገኝ አነስተኛ ሱቁ ደንበኞቹን ያስተናግዳል። በሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች የተሞላው አነስተኛ ሱቅ፤ ምሽት ላይ ሳይቀር ደንበኞችን አያጣም።

“በችርቻሮ ንግድ ሥራ ቆይታዬ የእቃ መያዣ እንደልብ ነበር። አሳስቦኝ አያውቅም። ከሰሞኑ የቸገረ ነገር ገጥሞኛል” ይላል ሙደሲር። በአንድ በኩል ከደንበኞቹ “እቃ መያዣ ስጠን” በሚሉ በሌላ በኩል ደግሞ አማራጭ የእቃ መያዣዎች ዋጋ በመወደዱ መፈተኑን ይገልጻል።

ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ፌስታሎችን መጠቀም ከተከለከለበት ጊዜ ጀምሮ በግራ መጋባት ውስጥ መሆኑን የሚናገረው ሙደሲር፤ እቃ መያዣዎችን በነጻ ሲያቀርብላቸው ለነበሩ ደንበኞቹ አሁን ከመርካቶ ገበያ በ40 ብር የገዛውን አማራጭ እቃ መያዣ በሽያጭ ማቅረብ ጀምሯል።

ደንበኞቹም ባልተለመደ መልኩ እቃ ከገዙት በኋላ መያዣውን በሽያጭ ሲያቀርብላቸው እንደሚበሳጩበት እና አልፎ አልፎ እንደሚገላምጡትም ተናግሯል። ወቀሳው በዛ ሲልበት፤ ብዙ እቃ ለሚገዙ ደንበኞቹ መሸት ሲል አልፎ አልፎ በፌስታል እንደሚያስተናግዳቸው አብራርቷል።

የኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰሚራ ሸረፋ፤ አዋጁ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ “ሸማቾች ምቾታቸው እየተጓደለባቸው መሆኑን እየነገሩን ነው” ሲሉ ከባለሱቁ ሙደሲር ጋር የተመሳሳለ ሀሳባቸውን ያጋራሉ። ከጨርቅ እና ማዳበሪያ የተሠሩ አማራጭ የእቃ መያዣዎችን ለሸማቾች ከ30 እስከ 150 ብር ድረስ በሽያጭ በማቅረብ ላይ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።

በአዲስ አበባ 13 ቅርንጫፎች ያሉት ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት፤ አማራጭ የእቃ መያዣ በገበያ ላይ ማግኘት ባለመቻሉ እንደ እርሱ ሁሉ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ባለው ኤም.ፒ.ፒ ፋብሪካ እቃ መያዣ ማስመረት ጀምሯል። ይሁንና የፋብሪካው የማምረት አቅም በቀን 1 ሺህ ብቻ መሆኑ በቀን በአማካይ 10 ሺህ ደንበኞችን ለሚያስተናግደው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት ሙሉ ፍላጎቱን ለማሟላት አልቻለም።

በዚህም ምክንያት ሱፐርማርኬቱ የእቃ መያዣ ምርቶችን ከውጭ ለመፈለግ መገደዱን ዋና ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል። “የፌስታል ጉዳይ የሸማቾችን የመግዛት ፍላጎት ቀንሷል” ያሉት ሰሚራ፤ ድርጅቱ ከሽያጭ የሚያገኘው ገቢም መቀነሱን አስታውቀዋል። ሆኖም የቅናሽ መጠኑን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ቦሌ የሚገኘው ስፕሪንግ ሱፐር ማርኬት ፌስታልን የሚተኩ አማራጭ እቃ መያዣዎችን ለደንበኞቹ እስካሁን ማቅረብ አልቻለም። የሱፐር ማርኬቱ ሥራ አስኪያጅ ትዕግስት ሀብተማርያም፤ “ከሁለት ሳምንት በፊት ከአምራቾች ጋር አማራጭ እቃ መያዣ እንዲያቀርቡልን የተነጋገርን ቢሆንም እስካሁን አላቀረቡልንም። በዚያ ላይ ከዚህ በፊት 30 ብር ሲሸጡ የነበሩ እቃ መያዣዎች አሁን ላይ 80 ብር እየተሸጡ ነው” ሲሉ በገበያ ላይ ያለው ምርትም ቢሆን መወደዱን አስረድተዋል።

ክፍተቱን ለመሙላት ምን እተደረገ ነው?

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ትላንት ማክሰኞ የካቲት 10፤ 2018 ውይይት ጠርቶ ነበር። በውይይቱ ላይ በቀላሉ የሚበሰብሱ እቃ መያዣዎችን የሚያመርቱ አምራቾች እና ድርጅቶች እንዲሁም የፌደራል የአካባቢ ጥበቃ ባለልጣን ተወካዮች ተገኝተዋል።

“ላይነር” የወረቀት ውጤቶች ማምረቻን ወክሎ በመድረኩ የተገኘው ቢኒያም የሺጥላ፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የወረቀት ህትመት ውስጥ ቆይቷል። ድርጅታቸው አሁንም ካርቶኖችን ጨምሮ የተለያዩ የወረቀት እቃ መያዣዎችን በማምረት ላይ መሆኑን የገለጸው ቢኒያም፤ በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ የፕላስቲክ እቃ መያዣዎችን ፍላጎት በአንድ ጊዜ መተካት እንደማይቻል ይናገራል።

የተተኪ ምርቶች ዋጋ መጨመርንም በቀላሉ ማስቆም እንደሚከብድ ቢኒያም ያስረዳል። “ከትላልቅ አምራች ፋብሪካዎች ጋር በመቀናጀት ካልሆነ በስተቀር ሰዎች በየቤታቸው እና በአነስተኛ ቦታዎች በሚያመርቱት የፕላስቲክ ከረጢት ምትክ የሆኑ ምርቶች ፍላጎቱን መሸፈን አይቻልም” ሲልም ሀሳቡን አካፍሏል።

”ፍሌክሲብል ፓኬጂንግ” የተብባለው ድርጅትን ወክሎ በትላንቱ ስብሰባ የተገኘው አቶ ሽመልስ ሹሚ በበኩሉ፤ ለአንድ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ የፕላስቲክ ምርቶችን መጠቀምን የሚከለክል ሕግ ከማውጣት በዘለለ መንግሥት ተኪ ምርት አምራቾችን “ሳይደግፍ” መቆየቱን ተችቷል።

“እኛን ጨምሮ አብዛኞቻችን ተኪ ምርት አምራቾች፤ አነስተኛ የማምረት አቅም ያላቸው፣ የገንዘብ፣ የማምረቻ ቦታ እና የግብዓት እጥረት ያለብን ነን” ያለው ሽመልስ፤ ሕዝቡ ለአማራጭ እቃ መያዣ ዋጋ መናር የተዳረገው በቂ ዝግጅት ባለመደረጉ መሆኑንም ገልጿል።

“አፍሮ ዘምቢል ፓኬጂንግ” ከተሰኘ ማምረቻ መምጣቷን የተናገረችው ሌላኛዋ ተሳታፊ ቲያ በላይ፤ ከ2013 ጀምሮ ተኪ የመያዣ ምርቶችን በማዘጋጀት ላይ መሰማራቷን ገልጻለች። ዘርፉ በዘላቂነት እንዲጠናከርና አምራቾች ወደዚህ ሥራ እንዲገቡ ማበረታታት እና ፋብሪካዎች ከመተከላቸው በፊት የጥራት ማስጠበቂያ መስፈርቶችን መዘርጋት እንደሚገባ አሳስባለች።

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ፤ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚተኩ ምርቶችን በማምረት ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች ያለባቸውን የመሥሪያ ቦታ፣ የገንዘብ እና የማሽነሪ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ተቋማቸው አብሯቸው እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል። 

አምራቾች እንደ ስኬት ባንክ፣ ልማት ባንክ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ካሉ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ ምክረ ሐሳብ የሰነዘሩት ሥራ አስኪያጁ በተጨማሪም ተደራጅተው በማኅበር ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ መክረዋል።

በፌደራሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የከተማ ቆሻሻ አያያዝ ክትትል ዴስክ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ዓለሙ በበኩላቸው፤ “ባለፉት ዓመታት የፕላስቲክ ከረጢቶች እያሉ ተኪ ምርቶችን ወደ ገበያ እንዲመጡ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል” ብለዋል። ምንም እንኳን በቂ ዝግጅት ባይደረግም፤ “ለሰው እና አካባቢ ጤና ሲባል የፕላስቲክ ከረጢቶችን ሙሉ ለሙሉ ማገድ የግድ አስፈላጊ” ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል።

ተኪ የእቃ መያዣዎችን በማምረት ላይ ለሚገኙ አምራቾች የግብር፣ የገንዘብ፣ የማምረቻ እና ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ እና ማበረታቻዎችን ለማቅረብ ተቋማቸው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ጋር በመወያየት ላይ መሆኑን ኃላፊው ከአምራቾች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)