ከትምህርት ዘመን መጀመር በፊት የክፍያ መጠናቸውን በማያሳውቁ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ 500 ሺህ ብር ቅጣት የሚጥል መመሪያ ተዘጋጀ

በወር ወይም በተርም የሚያስከፍሉትን የትምህርት ክፍያ፤ የትምህርት ዘመኑ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ከተማሪ ወላጆች እና አሳዳጊዎች ጋር በመወያየት፣ በግልጽ በማያሳውቁ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ 500 ሺህ ብር ቅጣት እንዲጣልባቸው የሚደነግግ ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ። ትምህርት ቤቶች የክፍያ አፈጻጸሞችን በትምህርት ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳዎች እና ድህረ ገጾች ላይ በግልጽ ካላሳወቁ፤ 100 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልባቸውም በረቂቅ መመሪያው ላይ ተደነግጓል። 

“ነጻና የግዴታ ትምህርት አተገባበር” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ መመሪያ የተዘጋጀው በትምህርት ሚኒስቴር ነው። የትምህርት ማህበረሰብ እና ባለድርሻ አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት ዛሬ ሐሙስ ህዳር 4፤ 2018 ዓ.ም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይፋ የተደረገው ይህ ረቂቅ መመሪያ፤ በስድስት ክፍሎች እና በ35 አንቀጾች የተከፋፈለ ነው።

በመመሪያው ከተካተቱ ክፍሎች አንዱ “የግል ትምህርት ቤት የትምህርት ክፍያዎችን” የሚመለከት ነው። በዚህ ክፍል የትምህርት ክፍያዎች ፍትሃዊነት እና ተመጣጣኝነት፣ የክፍያ አወሳሰን፣ የክፍያ ዘዴዎች፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲሁም የተከለከሉ ክፍያዎች ምንነትን የሚዘረዝሩ ድንጋጌዎች ተካትተዋል።

“ግልጽነትን” የሚመለከተው የመመሪያው ድንጋጌ፤ ሁለም የግል ትምህርት ቤቶች በወር ወይም በተርም የሚከፈለውን የተማሪዎች  የትምህርት ክፍያ እና መመዝገቢያ “በይፋ መግለጽ” እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ትምህርት ቤቶቹ ይህን ማድረግ የሚጠበቅባቸው “የትምህርት ዘመኑ ከመጀመሩ” በፊት እንደሆነም በድንጋጌው ላይ ሰፍሯል። 

የግል ትምህርት ቤቶቹ የክልል ወይም የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች በሚያወጣቸው መመሪያዎች ላይ ተመስርቶ የሚዘጋጀውን የትምህርት ክፍያ እና መመዘገቢያ በይፋ ከመግለጻቸው በፊት፤ “ከወላጅ ወይም ከአሳዳጊ ጋር መወያየት” እንደሚገባቸውም በረቂቅ መመሪያው ላይ ተመልክቷል። ማንኛውንም ትምህርት ቤት ይሄንን ጥሶ ቢገኝ እስከ 200 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልበት በመመሪያው ተደንግጓል። 

ይሄን ጥሰት ለሁለተኛ ጊዜ የሚደግም ትምህርት ቤት፤ ከሚጣልበት የ500 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ የማስተማር ፈቃዱ በጊዜያዊነት እስከ አንድ ዓመት ይታገዳል። ሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች በመመሪያው መሰረት የክፍያ አፈጻጸሞችን በትምህርት ቤቱ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች እና ድህረ ገጾች ላይ በግልጽ የማሳወቅ ግዴታም ተጥሎባቸዋል።

የክፍያ አፈጻጸሞችን አለማሳወቅ እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደሚያስቀጣ የገለጸው ረቂቅ መመሪያው፤ ጥሰቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተደገመ እንደሆነ ቅጣቱ ወደ 400 ሺህ ብር ከፍ እንደሚልም አስገንዝቧል። የግል ትምህርት ቤቶች ዘመኑ የደረሰበትን “ተለዋዋጭ” እና “ተደራሽ” የክፍያ አማራጮች እንዲያቀርቡም መመሪያው ያስገድዳል።

ትምህርት ቤቶቹ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች ከሚያወጧቸው የክፍያ መመሪያዎች ውጪ፤ “ያልተፈቀደ ክፍያ” ማስከፈል እንደማይችሉም በረቂቅ መመሪያው ላይ ተቀምጧል። “የተማሪ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ያልተወያዩበት እና ያልተስማሙበት፤ የትምህርት ክፍያ እና መመዝገቢያ “ተፈጻሚ መሆን የለበትም” ሲልም መመሪያው ደንግጓል። 

ከመመሪያ ውጭ ለተማሪዎች የትምህርት ክፍያ እና መመዝገቢያ የተሰበሰበ ገንዘብ ካለ፤ ለተማሪ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች “ተመላሽ” እንዲሆን ይኸው ረቂቅ መመሪያ ያዝዛል። የትምህርት ወይም የመመዝገቢያ ክፍያዎችን በተመለከተ የተማሪ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ቅሬታ ካላቸው፤ የትምህርት ስራውን ለሚያስፈጽመው አካል “በጹሁፍ” ማቅረብ እንዳለባቸው መመሪያው ያስገነዝባል።

በዚህ አሰራር ያልተፈቱ ቅሬታዎች ካሉ በሚመለከተው የትምህርት ቢሮ ወይም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቀርበው “ሊታዩ እንደሚችሉ” በረቂቅ መመሪያው ተመልክቷል። ያልተፈቱ ቅሬታዎች ወይም አለመግባባቶች “በ15 የስራ ቀናት ውስጥ” መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚገባም መመሪያው ቀነ ገደብ አስቀምጧል። 

እነዚህን ድንጋጌዎች የያዘውን መመሪያ፤ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች በክልል እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው በረቂቅ መመሪያው ላይ ተመልክቷል። ይሁንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ደንብ በካቢኔው ያጸደቀው የትምህርት ሚኒስቴር መመሪያውን ይፋ ከማድረጉ አምስት ወራት በፊት ነው።

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ ባጸደቀው ደንብ መሰረት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለ2018 የትምህርት ዘመን እስከ 65 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል። በደንቡ ከተወሰነው የትምህርት አገልግሎት እና የመመዝገቢያ ክፍያ ውጪ “በማንኛውም ሁኔታ” ጭማሪ አድርጎ የተገኘ የትምህርት ተቋም፤ “ያለ አግባብ” በአብላጫ የሰበሰበውን ገንዘብ “ተመላሽ” እንደሚያደርግ የከተማይቱ ደንብ ይደነግጋል። 

ይህን የመከታተል ስልጣን የተሰጠው ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ነው። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጭማሪ አድርጎ ስለተገኘ ትምህርት ቤት በደንቡ የሰፈረውን ድንጋጌ የተላለፉ ትምህርት ቤቶች ላይ 50 ሺህ ብር አስተዳደራዊ ቅጣት የመጣል ኃላፊነት ተሰጥቶታል። 

ይኸው መስሪያ ቤት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ባወጣው መግለጫ፤ ትምህርት ቤቶች የሚያደርጉት የትምህርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ “በደንቡ በተገለጸው ጣሪያ” መሰረት መሆን እንዳለበት ገልጾ ይህንን በተመለከተም ወላጆችን በመጥራት ማወያየት እንደሚገባቸው አሳስቦ ነበር። በትምህርት ቤቶች እና በወላጆች መካከል በሚደረግ ምክክር የክፍያ ጭማሪ መጠን እንደሚወሰንም በዚሁ መግለጫው ማስገንዘቡ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)