በቤርሳቤህ ገብረ
በኢትዮጵያ ያሉ ምሁራን በሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ ያላቸው ተሳትፎ፤ ሊኖራቸው ከሚገባው “አስተዋጽኦ” አንጻር ሲታይ “አነስተኛ ነው” ሲሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ተናገሩ። አብዛኞቹ ምሁራን ከሂደቱ “ራሳቸውን የማግለል” አሊያም ሁኔታውን “በዝምታ የመመልከት” አካሄዶችን የመከተል “አዝማሚያዎች” እንደሚታይባቸውም ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ይህን የገለጹት፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደት ምሁራን የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ዛሬ ቅዳሜ ግንቦት 9፤ 2017 በተካሄደ የውይይት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። በአዲስ አበባው ሃይሌ ግራንድ ሪዞርት በተካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ላይ ከአማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተመረጡ 90 ምሁራን ተሳትፈዋል።
ይህን መርሃ ግብር በንግግር የከፈቱት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት፤ በሌሎች ሀገራት የተከናወኑ ሀገራዊ ምክክሮች “ውጤታማ እንዲሆኑ” ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ “የምሁራኖቻቸው አስተዋጽኦ” እንደሆነ አስገንዝበዋል። በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ባለው ሀገራዊ ምክክር ተመሳሳይ ውጤት እንዲመዘገብ፤ “የምሁራን አበርክቶት” እና “የጉዳዩ ባለቤት መሆን” “ከፍተኛ ሚና” እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ በሆነ ጉዳዮች ላይ “አለመግባባቶች” “ጎልተው ከሚታዩባቸው” ወገኖች መካከል ምሁራን “ተጠቃሽ” መሆናቸውን ሂሩት በንግግራቸው አንስተዋል። “ምሁራን ሀገርን በሃሳብ የሚመሩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደመሆናቸው መጠን የሃሳብ ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶች መስተዋላቸው የሚገርም ላይሆን ይችላል” ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ ይህን ለመፍታት “ያደረጉት ጥረት” እና “ያስገኙት ውጤት” “በአግባቡ መጠናት እና መገምገም ያለበት ይመስለኛል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሀገራዊ ምክክር ምሁራን “ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርጉባቸው” ከሚገባቸው “ታሪካዊ አጋጣሚዎች” መካከል “አንዱ እና ዋነኛው ነው” ያሉት ሂሩት፤ ምሁራን በሂደቱ “እንዲካተቱ” እና “እንዲሳተፉ” ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “የተለያዩ ጥረቶችን” እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ምሁራን ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው መድረኮች አጀንዳዎችን በመስጠት እና በሞደሬተርነት እየተሳተፉ መሆኑን የጠቆሙት ሂሩት፤ በኮሚሽኑ ምክር ቤት የአማካሪ ኮሚቴ አባል በመሆን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
ሆኖም እነዚህ አበርክቶዎች፤ ምሁራን በምክክር ሂደቱ ሊኖራቸው ከሚገባው ተሳትፎ እና ሊያበረክቱ ከሚችሉት አስተዋጽኦ አኳያ ሲመዘን “አነስተኛ ነው” የሚል እምነት በኮሚሽኑ ዘንድ እንዳለ ሂሩት ገልጸዋል። “የኢትዮጵያ ምሁራን በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን ሲያገልሉ ወይም ሁኔታውን በዝምታ ሲመለከቱ መታዘብ የተለመደ ነው። በሀገራዊ ምክክሩ ላይም ተመሳሳይ አዝማሚያዎችን እያየን ነው” ሲሉም ዋና ኮሚሽነሯ ተችተዋል።
“የኢትዮጵያ ምሁራን በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ራሳቸውን ሲያገልሉ ወይም ሁኔታውን በዝምታ ሲመለከቱ መታዘብ የተለመደ ነው። በሀገራዊ ምክክሩ ላይም ተመሳሳይ አዝማሚያዎችን እያየን ነው”
–
ምሁራን ሀገራዊ ምክክርን “በተለየ መልኩ ማየት አለባቸው” የሚል አቋም ኮሚሽኑ እንዳለው የጠቀሱት ሂሩት፤ ጉዳዩ “በአመለካከት ልዩነቶች ሳይጋረዱ” “ያለስስት አስተዋጽኦ ሊያበረክቱለት የሚገባ” እንደሆነም አሳስበዋል። ምሁራን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ሲባል “ሂደቱን መደገፍ ብቻ” እንዳልሆነ ያስገነዘቡት ሂሩት፤ “ከመስመር የወጡ ጉዳዮች ሲኖሩ በምክንያት የተደገፈ ምሁራዊ ትችት ማቅረብንም ይጨምራል” ሲሉ አብራርተዋል።
“በመደገፍም ይሁን በመቃወም የምሁራን ድምጽ ሊሰማበት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ዝምታ መንገሱ ግን ጠቃሚ አማራጭ ነው የሚል እምነት የለንም” ሲሉ ሂሩት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን አቋም አስታውቀዋል። ኮሚሽኑ የዛሬውን መርሃ ግብር ያዘጋጀውም፤ የምሁራኑ አስተዋጽኦ በሚቻለው እና በሚገባው ልክ እንዳይሆን ያሉ ተግዳሮቶችን ለይቶ የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማመንጨት በማሰብ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ከተሳተፉ ምሁራን አንዱ የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ፤ ምሁራኑ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲጫወቱ የሚፈለገውን አዎንታዊ ሚና “በአግባቡ የሚያግዝ እና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መንግስት አለን ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው ለዚህ ጉዳይ የሚሆን የምሁራን ኔትወርክ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በቀጣይ የሀገራዊ ምክክር የምሁራን ፎረም እንዲመሰረትም ሀሳብ ቀርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)