በትጥቅ ትግል እና በእስር ላይ ያሉ የአማራ ክልል ተወላጆችን በምክክር ሂደት ለማሳተፍ የጀመረውን ጥረት እንደሚቀጥል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

በተለያዩ ምክንያቶች ጫካ ገብተው ትጥቅ ትግል እያካሄዱ የሚገኙ፣ እስር ቤት ያሉ እንዲሁም ሀገራቸውን ለቅቀው የተሰደዱ የአማራ ክልል ተወላጆች፤ በሀገራዊ ምክክር እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ለመፍጠር የጀመረውን ጥረት “አጠናክሮ እንደሚቀጥል” የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ጥረቱን ከግብ ለማድረግ “የተለየ ትኩረትም ሰጥቶ” እንደሚሰራ ገልጿል።  

ይህ የተገለጸው ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 2፤ 2017 በባህርዳር ከተማ በተጀመረው፤ የአማራ ክልል የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ነው። በስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ክልል አስተባባሪ ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደሚካኤል፤ በክልሉ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ምክክር መደረጉን በተመለከተ የሚቀርቡባቸውን ትችቶች አንስተዋል። 

“የአማራ ክልል ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የክልሉ ተወላጆች በእስር ቤት እያሉ፣ ተሰድደው ባለበት እንዲሁም ለትግል ጫካ በገቡበት ሁኔታ፤ ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ምክክር ማድረጉን የሚኮንኑ እንዳሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንሰማለን። መረጃዎችም ደርሰውናል” ያሉት አቶ መላኩ፤ ኮሚሽኑ በዚህ ረገድ ያለውን አቋም ለተሳታፊዎች አስረድተዋል። 

“መታወቅ ያለበት ቁም ነገር፤ መላው የአማራ ህዝብ የአማራ ክልል ጉዳይ የሚያገባው መሆኑን ነው። ሰሞኑን በተደረገው የማህበረሰብ ወኪሎች ምክክርም ይህንኑ ማረጋገጥ ተችሏል። [ተወካዮቹ] ‘የሁሉም የክልል ህዝብ ጥያቄ ናቸው’ የተባሉ ጉዳዮችን አንስተው፣ አስመዝገበው ተመልሰዋል” ብለዋል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ ምክክር የሚያደርጉ ባለድርሻ አካላትም፤ ይህንኑ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “ባለድርሻ አካላት” ሲል የሚጠራቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት ተቋማት ተወካዮችን እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ነው። እነዚህ ተወካዮች ከ270 የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በመሆን በመጪው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ የአማራ ክልል አጀንዳዎችን በቀጣዮቹ ቀናት ያጠናቅራሉ።

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ምክክር “እጅግ ከፍተኛ ክንውን የተመዘገበበት” ነው ያሉት ኮሚሽነር መላኩ፤ ሆኖም ሂደቱ “ለየት ያለ አጀንዳ አለን፤ ልንሰማ ይገባል” የሚሉትን ሁሉ ኮሚሽኑ እንደሚያስተናግድ ገልጸዋል። “ወደ ኮሚሽኑ መጥተው አጀንዳቸውን ለመስጠት የሚፈልጉትን ለመቀበል፤ ኮሚሽኑ ምንጊዜም ዝግጁ እና በሩ ክፍት መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ” ሲሉም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተዋል።   

“የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንዱን ጥሎ፣ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚሄድበት አሰራር የሌለው መሆኑ ታውቆ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የእዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል አድርጎ ተግባሩን እንደሚያከናውን በዚህ አጋጣሚ በድጋሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ” ሲሉም አቶ መላኩ በሂደቱ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ጥሪ አድርገዋል።

በትጥቅ ትግል፣ በእስር እና በስደት የሚገኙ የአማራ ክልል ተወላጆች “ሀሳባቸውን የሚሰጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት”፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “ቁርጠኛ አቋም ያለው” መሆኑንም ኮሚሽነር መላኩ በድጋሚ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። እነዚህ ዜጎች በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ኮሚሽኑ “የተለየ ትኩረት” ሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል። 

“በአጠቃላይ አማራ ክልልን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ በትጥቅ ትግል፣ በእስር እና በስደት የሚገኙ ዜጎች፤ ብቸኛ እና በጣም አዋጪ በሆነው የምክክር ሂደት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል ኮሚሽነር መላኩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)