በተስፋለም ወልደየስ
እስከ ዛሬ ድረስ ባለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት፤ ከ200 ሺህ ሰዎች በላይ መሳተፋቸውን ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር አምባዬ ኦጋቶ ተናገሩ። ኮሚሽኑ ከ1,746 በላይ የሆኑ “የጥቃቅን ቡድኖች” የምክክር አጀንዳዎችን መሰነዱንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ዶ/ር አምባዬ ይህን ያስታወቁት፤ ዛሬ አርብ ግንቦት 22፤ 2017 በአዲስ አበባው ሚሊኒየም አዳራሽ በተጀመረው የፌደራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ ባቀረቡት ገለጻ ነው። ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መርሃ ግብር፤ የተለያዩ የፌደራል ተቋማትን፣ ማህበራትን እና አካላትን የወከሉ 900 የሚጠጉ ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በፌደራል ደረጃ በሚካሄደው በዚህ የምክክር ሂደት ከሚሳተፉት መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት፤ “ተጽዕኖ ፈጣሪ” የተባሉ ግለሰቦች ናቸው። በኮሚሽኑ ግብዣ በምክክር አጀንዳ ልየታ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የእነዚህ ግለሰቦች ብዛት 220 እንደሆነ ከተቋሙ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የሃይማኖት እንዲሁም የሲቪል እና የዲሞክራሲ ተቋማት፤ ከመንግስት ተወካዮች እኩል 160 ተሳታፊዎችን አዋጥተዋል። በፌደራል ደረጃ ያሉ ማህበራት እና ተቋማት በ113 ግለሰቦች ሲወከሉ፣ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች እና ማህበራት 96 ግለሰቦችን በምክክሩ ላይ አሳትፈዋል።
ከሀገር አቀፍ እና ከክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ተውጣጥተው በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ እየተሳተፉ ያሉ ፖለቲከኞች 85 ናቸው። በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ካሉ እና ከቀድሞው የመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ተመርጠው፤ በዚህ መርሃ ግብር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የጸጥታ አስከባሪ አካላት 45 እንደሆኑ የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።
እነዚህ ተሳታፊዎች በየመጡበት ተቋም ስር በመሆን ባመጧቸው አጀንዳዎች ላይ ዛሬ ከሰዓቱን ምክክር ሲያደርጉ ውለዋል። ተሳታፊዎቹ በነገው ዕለት በሰባት ቡድኖች በመከፈል አጀንዳዎቻቸውን አደራጅተው፤ ለፌደራል ባለድርሻ አካላት አጀንዳ አሰባሳቢ ጉባኤ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ በክልሎች እንደተደረገው ሁሉ የፌደራል ባለድርሻ አካላት “የተጠቃለለ አጀንዳ” ሁሉም ተሳታፊዎች በተገኙበት በንባብ ይደመጣል። ይህ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተጠቃለለ አጀንዳዎቹን ይረከባል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ባካሄዳቸው 13 ተመሳሳይ መድረኮች የተሰበሰቡ “የጥቃቅን ቡድኖች” የአጀንዳ ሰነዶች ብዛት ከ1,746 በላይ መሆኑን ኮሚሽነር ዶ/ር አምባዬ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተናግረዋል። በክልሎች፣ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከሚገኙ የማህብረሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡ የአጀንዳ ሰነዶች ብዛት 164 መሆኑንም አስረድተዋል።
በ11 ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ካሉ ባለድርሻ አካላት፤ 65 የአጀንዳ ሰነዶችን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማስረከባቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ኮሚሽኑ 13 የክልል እና የከተማ አስተዳደር የተጠቃለሉ የአጀንዳ ሰነዶችን ለምክክር መሰብሰቡንም አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የምክክር ጉባኤ “አጀንዳ የመቅረጽ ሂደት መጀመሩን” ዶ/ር አምባዬ ጠቁመዋል። ጉባኤውን የሚያመቻቹ ግለሰቦችን ወደ መመልመል ሂደት መገባቱንም አክለዋል።
“በተጨማሪም ዋናው ሀገራዊ ምክክር ‘ምን መምሰል አለበት?’ የሚል ኤክሳርሳይሶችን እየሰራን እንገኛለን…ኢትዮጵያውያን በሚቀረጹ አጀንዳዎች ላይ ከተወያዩ [በኋላ]፤ ‘ውሳኔዎች እንዴት ነው የሚሰጡት?’ የሚለውን ግልጽ በሆነ መንገድ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት መስራት ስላለብን፤ ያንን እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤን ከማካሄዱ አስቀድሞ በትግራይ ክልል እና በተመረጡ የዳያስፖራ አካባቢዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቶች ማካሄድ ይጠበቅበታል። እስካሁን ባለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከ200 ሺህ በላይ መሳተፋቸውን በዛሬው መርሃ ግብር ላይ የተናገሩት ዶ/ር አምባዬ፤ ለሂደቱ ወኪሎቻቸው የመረጡ ወረዳዎች ብዛት 1,234 መሆናቸውን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)