በፌደራል ደረጃ ካሉ የባለድርሻ አካላት ሀገራዊ የምክክር አጀንዳዎችን የማሰባሰቢያ መድረክ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሊካሄድ ነው 

በቤርሳቤህ ገብረ

በፌደራል ደረጃ ባሉ የባለድርሻ አካላት የሚደረገው የሀገራዊ ምክክር እና የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በዚህ መድረክ ላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ተወካዮችን ጨምሮ 38 የባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሏል።

ባለፈው ታህሳስ ወር የስራ ዘመኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የተራዘመለት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ሲያሰባስብ ቆይቷል። ከ10 ክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተሰበሰቡ የምክክር አጀንዳዎችን ከወራት በፊት የተረከበው ኮሚሽኑ፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት የዘገየውን የአማራ ክልል ተመሳሳይ ክንውን ባለፈው ወር መጀመሪያ ላይ አጠናቅቋል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከሁለት ሳምንት በፊት ባሰራጨው መረጃ፤ የፌደራል ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ለማካሄድ እየተሰናዳ መሆኑን ገልጾ ነበር። ይህን መድረክ ለማካሄድ እየተደረገ ባለው ዝግጅት፤ በፌደራል ደረጃ ለሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት፣ የመንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ ጥሪ እንደተደረገላቸው ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በአዲስ አበባው የሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ፤ ከእነዚህ የባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ከ900 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ፤ ተሳታፊዎቹ የተመካከሩባቸውን አጀንዳዎች አጠናቅረው ለኮሚሽኑ እንደሚያስረክቡ እና በመጪው ሀገራዊ ጉባኤ ላይ የሚወክሏቸውን ወኪሎች እንደሚመርጡ ሂሩት አስረድተዋል። 

ከዚህ መድረክ መጠናቀቅ በኋላ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ እስካሁን ምክክር ባልተካሄደበት የትግራይ ክልል ተሳታፊዎችን የመለየት እንዲሁም የምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት እንደሚያከናውን ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል። በክልሉ ለሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ሂደት የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ሂሩት፤ የእዚህ አካል የሆነ ውይይት ከዩኒቨርስቲ መምህራን እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር መደረጉን አመልክተዋል።  

በቀጣይ በዳያስፖራ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ እንዲቀርቡላቸው የሚፈልጓቸው አጃንዳዎችን በበይነ መረብ አማካኝነት የማሰባሰብ ሂደትም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በቀሩት 10 ወራት ውስጥ የቀሩ ስራዎችን ያጠናቅቃል ወይ?” በሚል ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፤ “አንድ የምናውቀው ነገር በእርግጠኛነት ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ እናደርጋለን። Exact science አይደለም። ‘ሰው በስንት ጊዜ ውስጥ ተግባብቶ ውሳኔ ላይ ይደርሳል’ የሚባለውን በግምት ነው ያደረግነው። የበለጠ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፤ ያነሰም ሊፈጅ ይችላል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)