በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለውድድር የሚቀርቡ ዕጩዎችን ለመመዝገብ የተዘጋጀው የዲጂታል ስርዓት፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን “ከፉክክር ሜዳው በማውጣት ህዝብን አማራጭ አሳጥቶ ለመግዛት የታሰበ የፖለቲካ ሴራ ነው” የሚል ነቀፋ ቀረበበት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ የምርጫ ሂደቱን “ለመጉዳት” በመስሪያ ቤቱ “ሆን ተብሎ የሚደረግ ተግባር የለም” ሲል አስተባብሏል።
ዛሬ አርብ ጥር 15፤ 2018 ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በዲጂታል ሥርዓቱ እና በምርጫ ቦርድ የዕጩዎች ምዝገባ መስፈርቶች ላይ ተቃውሞ ያቀረቡት ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ የፓርቲዎች ስብስብ ናቸው። ከፓርቲዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ይገኙበታል።
ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር ኢትዮጵያ)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ)፣ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄም (አማራዊ ግዮናዊ) የዛሬው መግለጫ አካል ናቸው። ኢሕአፓ እና መኢአድ አባል የሆኑበት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት (ለኢትዮጵያ) የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብም በጋራ መግለጫው ተካትቷል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በዚሁ መግለጫቸው “ግልጽነት በጎደለው” እና “በተድበሰበሰ የምዝገባ አሠራርና ሂደት”፤ በመጪው ግንቦት መጨረሻ የሚካሄደው ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ “አሳታፊ፣ ሃቀኛ፣ ተዓማኒ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊሆን አይችልም” ሲሉም አቋማቸውን አስታውቀዋል። ሀገር አቀፉ ምርጫ ሊካሄድ ወራት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት፤ በዕጩዎች ምዝገባ ጅማሮ ላይ “ሰላማዊውን የፖለቲካ ምህዳር እያጨለሙ ያሉ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመውናል” ብለዋል ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በተግዳሮነት ከጠቀሷቸው ጉዳዩች አንዱ የዕጩዎች እና የመራጮች ዲጂታል ምዝገባ ስርዓትን ነው። ምርጫ ቦርድ ምዝገባውን ለማካሄድ የሚያስችል መተግበሪያ ማበልጸጉን “በጥቅል መልኩ” ለፖለቲካ ፓርቲዎች አወያይቶ እንደነበር ፓርቲዎቹ በዛሬው መግለጫቸው አስታውሰዋል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ “በቂ የቴክኒካል እውቀት የሌላቸው” መሆናቸውን በመግለጫቸው ያነሱት ተቃዋሚዎቹ፤ ቦርዱ ስላበለጸገው መተግበሪያ አዳምጠው ከመውጣት ባለፈ “ፈትሸው ማጽደቅ የሚያስችል ሁኔታ እንዳልነበረ ሊሰመር ይገባል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። ምርጫ ቦርድ ዕጩዎች እና መራጮች በዲጂታል አማራጭ መመዝገብ የሚችሉበት መተግበሪያ እና የድረ ገጽ አማራጭ ማዘጋጀቱን የገለጸው ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
ቦርዱ የዲጂታል ምዝገባ ስርዓቱን ይፋ ባደረገበት በዚህ ስነ-ሥርዓት ላይ የዲጂታል አማራጮቹ በስድስት የሀገሪቱ ቋንቋዎች ምዝገባ ለማከናወን እንዲችሉ ተደርገው መዘጋጀታቸውን ገልጿል። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ባወጣው ይፋዊ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ በዚሁ የዲጂታል ሥርዓት የዕጩዎች ምዝገባ የሚካሄደው ከጥር 1 እስከ የካቲት 1 ነው።
ዛሬ መግለጫ ያወጡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን በዲጂታል ሥርዓቱ ውስጥ የተቀመጡ ግዴታዎች ዕጩዎችን ለማስመዝገብ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ዕጩዎች ሲመዘገቡ ማሟላት አለባቸው ተብለው ከተጠቀሱት ግዴታዎች መካከል “የልደት የምስክር ወረቀት” መያዝ አንዱ መሆኑን በመግለጫቸው ያነሱት ፓርቲዎቹ፤ ይህን የምስክር ወረቀት መያዝ “ከከተሞች ውጭ ፈጽሞ ያልተለመደ” በመሆኑ በዚህ ረገድ ችግር እንዳጋጠማቸው አመልክተዋል።
“የልደት የምስክር ወረቀት” ማቅረብ ያልቻለ ዕጩ፤ ግለሰቡ ሲወለድ የነበረ “የዓይን እማኝ ማቅረብ እንዳለበት” በምዝገባ ፎርሙ ላይ መቀመጡን ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል። ሆስፒታል ውስጥ እንኳን ለተወለዱ ዕጩ የምርጫ ተወዳዳሪዎች፤ “ያዋለዱ ባለሙያዎችን ለምስክርነት ማግኘት አይቻልም” ያሉት ፓርቲዎቹ ይህ በአማራጭነት መቀመጡን ተችተዋል።

ከቅሬታ አቅራቢ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ኃይማኖት፤ በዲጂታሉ አማራጭ አንድ ዕጩ መታወቂያው ከተመዘገበበት አካባቢ ውጭ ባለ የምርጫ ክልል ለተወዳዳሪነት የመመዝገብ ዕድል እንደሌለው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መታወቂያ ካወጡበት ክፍለ ከተማ ውጪ ለመወዳደር በዕጩነት ሲመዘገቡ የገጠማቸውንም በማሳያነት በመጥቀስ አሰራሩ ችግር እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
አቶ አብርሃም በመጀመሪያ ለመወዳደር አስበው የነበረው በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ እንደነበር ጠቁመዋል። ሆኖም የእርሳቸው ፓርቲ አባል በሆነበት የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ስብስብ ውስጥ የሚገኝ የሌላ ፓርቲ ዕጩ በክፍለ ከተማው በሚገኝ የምርጫ ክልል ስለሚወዳደር፤ የራሳቸውን የመወዳደሪያ ስፍራ ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ማዘዋወራቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው የዲጂታል አማራጭ ከተመዘገቡ በኋላ መታወቂያቸው የቦሌ ክፍለ ከተማ በመሆኑ ውድቅ እንደተደረገባቸው የኢሕአፓው ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይህ አካሄድ በተለያየ ምክንያት ተዘዋውረው ኑሮአቸውን በሚገፉ እና በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በሚኖሩ ዕጩዎች ላይ “የጎላ ተጽዕኖ” እንደሚኖረው ስጋታቸውን አጋርተዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ማስተባበርያ ክፍል ኃላፊ ቀነኒ እንሰርሙ፤ ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ውጭ ያሉት መስፈርቶች ከዚህ ቀደም በተካሄደው “ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይም የነበሩ ናቸው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምላሽ ሰጥተዋል። በምርጫ አዋጁ ላይ ለዕጩዎች ከተቀመጡ መስፈርቶች አንዱ የሰነድ ማረጋገጫ እንደሆነ የጠቀሱት ቀነኒ፤ ይህም ቢሆን በልደት ሰርተፍኬት እና በመታወቂያ ላይ ብቻ የተመሰረተ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
አንድ ዕጩ የሚወዳደርበት የምርጫ ክልል፤ ውልደቱ በአካባቢው ከሆነ አሊያም አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ በምርጫ ክልሉ በመኖር ወይም ሁለትና ከዚያ በላይ ለሆነ ዓመት በስፍራው በመስራት የሚወሰን እንደሆነ ኃላፊዋ የምርጫ ህጉን በማጣቀስ አብራርተዋል። ይህ በልደት ሰርተፍኬት፣ በፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ፣ በመኖሪያ እና በስራ መታወቂያ የሚረጋገጥ በመሆኑ ዕጩው የተቻለውን አማራጭ አቅርቦ መመዝገብ እንደሚችል ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ለምርጫ የሚወዳደር ግለሰብ የቀድሞ የዕጩነት ሰርተፍኬት አያይዞ መመዝገብ እንደሚችልም ጠቁመዋል። የሰነድ ማስረጃዎች ተደራሽ ሊሆኑባቸው በማይችሉ ገጠራማ አካባቢዎች ላይ ደግሞ አንድ ዕጩ በምርጫ ክልሉ የተወለደ ወይም አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የኖረ እና ለሁለት ዓመታት የሰራ ስለመሆኑ ሶስት ምስክሮችን በማቅረብ መመዝገብ እንደሚችል ኃላፊዋ አስረድተዋል።

በዛሬው የፓርቲዎቹ መግለጫ የተነሳው ሌላው ቅሬታ “የቤት ፕላን ማቅረብ ለምዝገባ ግዴታ ነው” የሚል ነው። የቤት ተከራዮች የቤቱን ፕላን (ካርታ) ከአከራዮቻቸው የማግኘት ዕድል እንደሌላቸው የገለጹት ፓርቲዎቹ፤ ይህን መስፈርት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማሳካት ደግሞ “የሚታሰብ” እንዳልሆነ አመልክተዋል።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚመዘገቡ ዕጩዎችን የምዝገባ ሂደት የሚመሩት ቀነኒ በበኩላቸው ለምርጫ ተወዳዳሪዎች “የቤት ካርታ አልተጠየቀም” በማለት አስተባብለዋል። እያንዳንዱ ዕጩ “የኢሜይል አድራሻ ማስገባት ግዴታው መሆኑ” በመስፈርትነት መቀመጡን በማንሳት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ላቀረቡት ትችት ደግሞ፤ ቦርዱ ፓርቲዎች ያጋጠማቸውን ተግዳሮት በመረዳቱ “ኢሜይል አስገዳጅ መሆኑ ቀርቷል” ብለዋል።
ሰባቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዛሬው መግለጫቸው፤ ኢሜይልን አስገዳጅ የሚያደርገው እና አንድን የኢሜይል አድራሻ ለሁለትና ከዚያ በላይ ዕጩዎች በጋራ መጠቀምን የሚገድበው ህግ “ሊሰረዝ” እንደሚገባ አሳስበው ነበር። ፓርቲዎቹ በዚሁ መግለጫቸው፤ የአካል ጉዳተኞች “ከሁለት ሆስፒታሎች ማስረጃ እንዲያቀርቡ” ግዴታ መቀመጡንም አንስተዋል።

ይህ መስፈርት በቂ ሆስፒታሎች የሌሉበትን የሀገሪቱን ገጠር አካባቢዎች ያላገናዘበ ከመሆኑ ባለፈ፤ የአካል ጉዳት “የሚዳሰስ እና የሚታይ ሆኖ ሳለ እንደ ውስጥ ደዌ ማስረጃ መጠየቁ በራሱ ትክክል አይደለም” ሲሉ ፓርቲዎቹ ተቃውመዋል። የአካል ጉዳተኞችን በሚመለከት የተቀመጠው መስፈርት፤ ቦርዱ ፓርቲዎች ባስመዘገቡት የአካል ጉዳተኞች መጠን ልክ ለሚያደርገው ድጋፍ “በማስረጃ ላይ መመስረት ስላለበት” እንደሆነ ቀነኒ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
የማስረጃ ሰነዶቹ ከመንግስት የህክምና ተቋም እና ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት መቅረብ እንዳለባቸው በህግ መደንገጉንም ጠቅሰዋል። የዛሬውን መግለጫ በጋራ ያወጡት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፤ ለዕጩዎች ከተቀመጡ አስገዳጅ መስፈርቶች ሌላ በዲጂታል ስርዓቱ ምዝገባ ለማከናወን በሚሞክሩበት ወቅት ያጋጠማቸውን ችግሮች ዘርዝረዋል።
የየፓርቲው የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ዕጩዎችን በሚመዘግቡበት ጊዜ “የኔትዎርክ ችግር” ደጋግሞ እያቋረጣቸው መሆኑን በመግለጫቸው የጠቆሙት ተቃዋሚዎቹ፤ ለምዝገባው በተሰጠው “የ3 ደቂቃ ጊዜ” ውስጥ ተናብበው የፋይዳ መታወቂያ ትስስሩን ማሳካት “እጅግ አዳጋች” መሆኑን አመልክተዋል። በዲጂታል ስርዓቱ ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት የእርሳቸው እና የሌሎችም ፓርቲዎች ዕጩዎች ምዝገባ ለማከናወን መቸገራቸው የገለጹት የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት፤ “ምርጫ ቦርድ ሲስተሙን ሊፈትሸው እንደሚገባ” አሳስበዋል።
ኢሕአፓ የተካተተበት “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” የተሰኘው የፓርቲዎች ስብስብ 1,275 ዕጩዎችን ለምርጫ ቦርድ ቢያቀርብም፤ “በሲስተም ችግር” ምክንያት ባለፉት 15 ቀናት በዲጂታል ሥርዓቱ ማስመዘገብ የቻለው መቶ ገደማዎቹን ብቻ መሆኑን አቶ አብርሃም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለምርጫ ቦርድ የቀረቡ ዕጩዎችን በዲጂታል ሥርዓት ማስመዝገብ ግዴታ መሆኑን የጠቆሙት የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት፤ በቀጣዩ ሁለት ሳምንት የቀሩትን ዕጩዎች ሁሉ ማስመዝገብ ፈታኝ እንደሚሆን አስገንዘበዋል።
“የ3 ደቂቃ ጊዜ” የተቀመጠው የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያን ለማረጋጥ ብቻ መሆኑን ያመለከቱት የዕጩዎች ምዝገባ ሂደት መሪዋ ቀነኒ፤ የምዝገባው አጠቃላይ ሂደት ግን የሰዓት ገደብ እንዳልተቀመጠለት በመግለጽ ቅሬታ ላቀረቡት ፓርቲዎች ምላሽ ሰጥተዋል። አንድ ዕጩ ከብሔራዊ መታወቂያ ተቋም የሚላከውን የአንድ ጊዜ የይለፍ ቁጥር በ3 ደቂቃ ውስጥ ካልስገባ፤ በድጋሚ የሚያስገባበት ዕድል እንዳለውም ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
በምርጫ ቦርድ የዲጂታል የምዝገባ ሥርዓት፤ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ያለፓርቲያቸው ዕውቅና በእጃቸው ባለው ስልክ ገብተው “ራሳቸውን ከዕጩነት እንዲሠርዙ” የሚያስችል አማራጭ መካተቱ ሌላው በተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅሬታ የቀረበበት ጉዳይ ነው። ይህ አሰራር “ገዢው ፓርቲ እና ካድሬዎቹ” “በሀብት እና ጥቅማ ጥቅም” አሊያም “በሥልጣን፣ በእሥራት እና በማስፈራራት” እጩዎች ራሳቸውን እንዲሰርዙ ለማድረግ “ሆን ተብሎ” የተደረገ መሆኑን በመጥቀስ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ተችተዋል።

የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓቱ “የሀገሪቱን አቅም እና የህዝቡን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ብቃት ያላገናዘበ” መሆኑን በተጨማሪነት የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፤ “መንግሥት ብቻውን የደረሰበትን ቴክኖሎጂካል ሲስተም ለመስፈርትነት መጠቀም አግባብነት የለውም” ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው አስፍረዋል። ይህ አካሄድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን “ከፉክክር ሜዳው በማውጣት” ህዝብን አማራጭ ለማሳጣት ታስቦ የተዘጋጀ” እንደሆነም ፓርቲዎቹ አቋማቸውን በመግለጫቸው አንጸባርቀዋል።
በምርጫ ቦርድ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ማስተባበርያ ክፍል ኃላፊዋ፤ በመስሪያ ቤታቸው በኩል የምርጫ ሂደቱን “ለመጉዳት ሆን ተብሎ የሚደረግ ተግባር የለም” ሲሉ ትችቱን ተከላክለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲኖራቸው ለቦርዱ ማቅረብ እንደሚችሉም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































