መረጃ በሚከለክሉ ኃላፊዎች ላይ በመረጃ ነጻነት ረቂቅ አዋጅ የተቀመጠው የቅጣት መጠን፤ ከ20 ሺህ ወደ 150 ሺህ ብር እና ከዚያ በላይ ከፍ እንዲል የኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ ምክር ቤት ጠየቀ። መረጃዎችን በሰነድ መስጠት ሳይቻል ሲቀር፤ ኃላፊዎች በቃለ መጠይቅ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲሰጡ የሚያስገድድ አንቀጽ በአዋጁ ላይ መስፈር እንዳለበትም ምክር ቤቱ አሳስቧል።
ምክር ቤቱ ይህን ጥያቄ ያቀረበው፤ የመረጃ ነጻነት የአዋጅ ረቂቅን በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 16፤ 2018 በአዲስ አበባ በተካሄደ ውይይት ላይ ነው። በፍትሕ ሚኒስቴር ስር ተዋቅሮ በነበረው የመገናኛ ብዙሃን የስራ ቡድን የተዘጋጀው እና በኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዳበረው የመረጃ ነጻነት የአዋጅ ረቂቅ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይላካል ተብሎ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ አዋጁን ከማጽደቁ በፊት፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተጠርተው የሕዝብ አስተያየት እንዲካተትበት እንደሚደረግም በዚህ ውይይት ላይ ተነስቷል። በዚሁ እሳቤ በተዘጋጀው በዛሬው የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በአዋጅ ረቂቁ ላይ መሻሻል ይገባቸዋል ባላቸው ጉዳዮች ላይ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቧል።

ተቋማት ወይም የተቋማት ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ “በ48 ሰዓት ውስጥ ምላሽ መስጠት አለባቸው” በሚል በአዋጁ ረቂቁ ላይ የተቀመጠው አንቀጽ በምክር ቤቱ እንዲሻሻል ከተጠየቁት ውስጥ ይገኝበታል። የመረጃ መስጪያ ገደቡ ለአስቸኳይ ጉዳዮች ሲሆን “ከዚያም ባጠረ ጊዜ እንዲሰጥ” የሚል ሀሳብ “ሊካተት ይገባል” ሲል ምክር ቤቱ የማሻሻያ ሃሳቡን ገልጿል።
መረጃዎችን በሰነድ መስጠት ሳይቻል ሲቀር፤ ኃላፊዎች በቃለ መጠይቅ ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲሰጡ የሚያስገድድ አንቀጽ በአዋጅ ረቂቁ ላይ “መስፈር እንዳለበትም” ምክር ቤቱ በዛሬው ውይይት ላይ አመልክቷል። የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመፍትሔ ሀሳቦችን ከመጠቆም ባለፈ መረጃ በማይሰጡ አካላት ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ስልጣን በረቂቅ አዋጁ ያልተሰጠው መሆኑ፤ ሌላኛው መሻሻል አለበት በሚል በመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት የተነሳ ሃሳብ ነው።
የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ መሰረት አታላይ፤ የምንሰጠው መረጃ “የህዝብን ጥቅም ይጎዳል” በሚል ምክንያት የበርካታ ተቋማት ኃላፊዎች “መረጃ አይሰጡም ወይም የመተባበር ፍላጎት የላቸውም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በተለያዩ ምክንያቶች መረጃዎችን ከሚዲያዎችም ሆነ ከሌሎች መረጃ ፈላጊዎች ሲጠየቁ የማይተባበሩ አካላት ላይ ቅጣት እንደሚጣል በረቂቅ አዋጁ ላይ መቀመጡን “በበጎ መልኩ እንደሚያዩት” ገልጸዋል።

ይሁንና ይህን በማያደርጉ አካላት ላይ እንዲጣልባቸው በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው የ20 ሺህ ብር ቅጣት “አነስተኛ” መሆኑን አንስተዋል። “እንደ ኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ ምክር ቤት ከሆነ ይህ ቅጣት በጣም ትንሽ ነው” ያሉት አቶ መሰረት፤ በገንዘብ ሊገመቱ የማይችሉ ሕዝብን እና ሀገርን የሚጠቅሙ መረጃዎችን የደበቀ፣ ሆን ብሎ ያጠፋ እና የደለዘን አካል 20 ሺህ ብር መቅጣት ማለት “ትክክል አይደለም” ሲሉ ይሞግታሉ።
ዝቅተኛው ቅጣት “150 ሺህ ብር ወይም ከዛ በላይ ሊሆን ይገባል” ሲሉ የገንዘብ መጠኑ በረቂቅ አዋጁ ከተቀመጠው ከሰባት እጥፍ በላይ እንዲጨምርም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። አንድ ኃላፊ መረጃ ባለመስጠቱ ምክንያት ከፍተኛ የሀገር እና የሕዝብ ሃብት ላይ ጉዳት ቢደርስ፤ የሚጣለው ቅጣት ተመጣጣኝ ላይሆን ስለሚችል የቅጣት መጠኑ “እንደ ጉዳቱ መጠን እየታየ የሚጣል ቢሆን” እንደሚደግፉት አቶ መሰረት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ ይህንን ጉዳይ ጨምሮ በረቂቅ አዋጁ ላይ ቢስተካከሉ ያሏቸውን ከ11 በላይ ነጥቦች በዛሬው የውይይት መድረክ ላይ አንስተዋል። እንደ አቶ መሰረት አስተያየት ከሆነ፤ የመረጃ ነጻነት አዋጁ በብዛት “ግልጽ ያልሆኑ እና አሻሚ” ሀሳቦችን ከመያዙ ባለፈ፤ መረጃዎች ለህዝብ እንዲደርሱ የሚያበረታታ ሳይሆን “ብዙ ክልከላዎችን” የያዘ ነው።

የአዋጅ ረቂቁ በአብዛኛው ለመረጃ ሰጪው አካል “የተለጠጠ ስልጣን” የሰጠ መሆኑንም አቶ መሰረት ተችተዋል። በረቂቅ ደረጃ ያለው አዋጅ፤ ብዙሃን መገናኛዎችን ጨምሮ መረጃ ለሚፈልጉ የምርምር ተቋማት፣ ግለሰቦች እና ሌሎች አካላት ከዚህ በፊቱ የተሻለ መረጃ እንዲያገኙ የሚፈቅድ “አለመሆኑንም” ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ መሰረት ሁሉ የዛሬው ውይይት ተሳታፊዎችም፤ በመረጃ ነጻነት የአዋጅ ረቂቅ ላይ ቢጨመሩ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል። የአሐዱ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ፤ የመንግስት ተቋማት መረጃዎችን ሲጠየቁ እና ጋዜጣዊ መግለጫዎችን ሲያዘጋጁ የግል እና የመንግስት ሚዲያዎች በሚል በመክፈል “የሚፈልጉትን ብቻ መርጠው” የመጥራት አዝማሚያ እየጨመረ መሆኑን በውይይቱ ላይ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መረጃን የመንፈግ ባህል እያደገ መምጣቱን የገለጹት አቶ ጥበቡ፤ “የግል ሚዲያዎች አልተጠራችሁም፤ የጠራነው እነ እከሌን ነው” የሚለው የተቋማት ድርጊት፤ ጋዜጠኞች ዘገባዎችን በነጻነት እንዳይሰሩ እያደረገ በመሆኑ እንዲስተካከል ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽንን ተወካይ አቶ አብዮት ይግዛው በበኩላቸው ሚዲያዎች የሚፈልጓቸውን አስቸኳይ መረጃዎችን ሲጠይቁ “የሕዝብ ጥቅምን ይጎዳል” በሚል ሰበብ እየተከለከሉ እንደሆነ ገልጸዋል።

በረቂቅ ሕጉ ላይ፣ አንድ ኃላፊ መረጃ “በ48 ሰዓት ውስጥ እንዲሰጥ” ተብሎ መደንገጉ አሁንም የተቋማት ኃላፊዎች ይህን ሰበብ በማድረግ “አስቸኳይ መረጃዎችን እንዳይሰጡ እድል የሚሰጥ ነው” ሲሉም ተወካዩ ተችተዋል። አቶ አብዮት የመረጃ ነጻነት ረቂቅ አዋጁ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመጽደቁ በፊት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተጠርተው ተጨማሪ ውይይት እንዲያካሂዱ “ሊደረግ ይገባል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች ማኅበርን ወክለው በመድረኩ ላይ መገኘታቸውን የተናገሩት አቶ ዘመነ ዮሀንስ በበኩላቸው፤ ተቋማት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲጠሩ ቦታዎቹ ለአካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች ምቹ መሆን አለመሆናቸውን ትኩረት እንደማይሰጡ በማንሳት ተችተዋል። ተቋማት በአካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች መረጃ ሲጠየቁም አመቺ በሆነ መንገድ ለመስጠት ዝግጁ እንዳልሆኑ የገለጹት አቶ ዘመነ፤ እነዚህን ሁኔታዎችን ለማሻሻል የሚረዳ አንቀጽ በረቂቅ አዋጁ ላይ በግልጽ እንዲሰፍርላቸው ጠይቀዋል።
የመረጃ ነጻነት የአዋጅ ረቂቁን ማሻሻያዎችን በማከል ያዳበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፤ በውይይት መድረኩ ላይ የተነሱትን አስተያየቶች በግብዓትነት እንደሚወስዳቸው ገልጿል። በተቋሙ ምክትል ዕንባ ጠባቂ የሆኑት ዶ/ር የኔነህ ስመኝ፤ በአዋጁ ረቂቁ ላይ ቢስተካከሉ ተብለው ከተነሱ አስተያየቶች መካከል “አሻሚ የቋንቋ አቀማመጦችን” ጨምሮ በሌሎች ነጥቦች ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በተለይም “መረጃዎችን መከልከል የሚቻለው መቼ ነው?” በሚለው ላይ የተነሱ አስተያየቶችን በመቀበል ግልጽ ማሻሻያ ሀሳቦች “እንደሚካተቱ” በማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። ያለ ምንም ምክንያት መረጃ የከለከለ አካል እስከ “እስራት የደረሰ ቅጣት እንዲጣልበት” የሚጠይቅ ሃሳብ በረቂቅ ሕጉ ላይ ለማካተት ታስቦ እንደነበር የተናገሩት ምክትል ዕንባ ጠባቂው፤ በኋላ ላይ መረጃ የሚሰጡት የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች በመሆናቸው እና “የተፈጻሚነት ወሰኑ ጥያቄ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል” በሚል ሳይካተት መቅረቱን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































