ዋዜማ ሬዲዮ “ፍቃዱን” የመለሰው በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በተሰጠው “ትዕዛዝ” መሆኑን ገለጸ

በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እገዳ የታጠለበት ዋዜማ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን፤ የተወሰደበት እርምጃ “በማንኛውም መመዘኛ ትክክል ነው” ብሎ እንደማያምን ገለጸ። መገናኛ ብዙሃኑ ከባለስልጣኑ የተሰጠውን “ፍቃድ” የመለሰው፤ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ከመስሪያ ቤቱ በደረሰው ትዕዛዝ መሰረት መሆኑን አስታውቋል።

“ዋዜማ ሬድዮ” በሚል ስያሜ በስደት ላይ በነበሩ ሶስት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በሰኔ 2006 ዓ.ም የተቋቋመው መገናኛ ብዙሃኑ፤ “በኢትዮጵያ ያለውን የስራ ፍቃድ” ተመላሽ ያደረገው ዛሬ ቅዳሜ ጥር 16፤ 2018 ነው። የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውቅና የሰጠው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ በመጋቢት 2013 ዓ.ም ከጸደቀ ከሁለት ወራት በኋላ “የምዝገባ ምስክር ወረቀት” ከተሰጣቸው 17 መገናኛ ብዙሃን መካከል ዋዜማ ሬድዮ አንዱ ነበር።    

መገናኛ ብዙሃኑ በዚህ መልክ የተሰጠውን “የስራ ፈቃድ እውቅናውን” የመለሰው፤ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስት፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን፣ መመሪያዎችን እና የሙያ ስነምግባርን “አክብሮ ለመስራት” “ፈቃደኛ ባለመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ወንጅሏል። የመገናኛ ብዙሃኑ ዘገባዎች የኢትዮጵያን “ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ”፣ “ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው” እና “የሙያ ስነምግባርን የጣሱ” “የአንድ ወገን ዘገባ ብቻ” የተንጸባረቁባቸው ሆነው መገኘታቸውንም ባለስልጣኑ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የ“ዋዜማ ሬድዮ” ዘገባዎች፤ የፌዴራልና የክልል መንግስታት “አስተያየት እና ምላሽ ያልተካተተባቸው” እና “ሁከት ቀስቃሽ” መሆናቸውን በመግለጽም ባለስልጣኑ ከስሷል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው ራሱ “ባደረገው ክትትል” እና “ከዜጎችም በተሰጠው አስተያየትና ጥቆማ መሰረት” እንደሆነ በመግለጫው ላይ አመልክቷል። 

የዋዜማ መገናኛ ብዙሃን አመራር ምሽቱን ባወጣው መግለጫ፤ ባለስልጣኑ ያቀረባቸውን “ክሶች” “የኢትዮጵያን ሚዲያ ለሚከታተሉ ተደራሲዎች፣ ታዛቢዎች እና ባለሞያዎች የሕሊና ፍርድ እንተዋለን” ሲል ምላሽ ሰጥቷል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በበኩሉ የመገናኛ ብዙሃኑን ዘገባዎች በተመለከተ “ዋዜማ ሚዲያ ተደጋጋሚ የእርምት ግብረመልስ ሲሰጠው የቆየ” መሆኑን በመግለጫው ላይ አመልክቷል። 

ሆኖም መገናኛ ብዙሃኑ “የተሰጠውን አስተያያት እና “የማስተካከያ እርምጃ መቀበል ባለመፍቀዱ የስራ ፈቃዱን ተመላሽ እንዲያደርግ ተወስኖ” ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህንኑ ተግባራዊ ማድረጉን በመግለጫው አስታውቋል። ዋዜማ ሬድዮ “ተደጋጋሚ ጥሰቶችን” መፈጸሙን በመግለጫው የጠቀሰው ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ፤ “ለጥፋቱ” ከሁለት ወር በፊት “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ” ተሰጥቶት እንደነበር ገልጿል። 

ከዚህ በኋላም ቢሆን መገናኛ ብዙሃኑ “የማስተካከያ እርምጃ” ባለመውሰዱ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን “ሲያከናውንለት የነበረውን ድጋፍ” ከዚህ በኋላ “ለማቋረጥ” መገደዱን በመግለጫው ይፋ አድርጓል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውሳኔ “ማዘናቸውን” የገለጸው የዋዜማ መገናኛ ብዙሃን አመራር፤ “እርምጃው በማንኛውም መመዘኛ ትክክል ነው ብለን አናምንም” ሲል ተቃውሟል። 

የእርምጃውን ዝርዝር “በሚገባ አጢኖ”፣ “አስፈላጊ እና ጠቃሚ ከሆነ” ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚሰጥ ያመለከተው የመገናኛ ብዙሃኑ አመራር፤ “ሌሎች ሕጋዊ አማራጮችን” ለመከተል ማቀዱን አስታውቋል። ዋዜማ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ዜናዎችን እና ትንታኔዎችን፤ በድረ ገጹ እና በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ላለፉት 12 ዓመታት ሲያቀርብ ቆይቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)