በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከዚህ ቀደም የጸጥታ መደፍረስ ከነበረባቸው ከጋሞ እና ጋርዱላ ዞኖች የመከላከያ ሰራዊት ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ፤ በስፍራዎቹ አለመረጋጋት መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የመከላከያ ሰራዊት አካባቢዎቹን ባለፉት ሶስት ቀናት ለቅቆ መውጣቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡ አንድ የክልሉ ኃላፊ በበኩላቸው፤ በስፍራዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ገልጸዋል።
ከትላንት እሁድ የካቲት 8፤ 2018 ጀምሮ የጸጥታ መደፍረስ ካጋጠማቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢዎች መካከል የጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ እና የጋርዱላ ዞን ደራሼ ወረዳ እንደሚገኙበት ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ የጸጥታ አለመረጋጋት የተፈጠረው የዘይሴ ብሔረሰብ በሚገኝባቸው ቀበሌዎች መሆኑን አመልክተዋል።
ትላንት አመሻሽ አካባቢ በተለይ “ዘይሴ ወዘቃ” የተባለ ቀበሌ ላይ የተኩስ ድምጾች ይሰሙ እንደነበር እኚሁ ነዋሪ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደምም ራስን በራስ ከማስተዳደር ጥያቄ ጋር በተገናኘ በዘይሴ ብሔረሰብ መኖሪያ ቀበሌዎች ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች እንደነበሩ የሚናገሩት ነዋሪው፤ የትላንቱ ሁኔታም ከዚሁ ጋር የተገናኘ መሆኑን አስረድተዋል።

በአካባቢው በተፈጠረው አለመረጋጋት እና ተኩስ ምክንያት፤ ከአርባምንጭ – ጊዶሌ – ኮንሶ የሚወስደው አውራ ጎዳና በትላንትናው ዕለት ተዘግቶ እንደነበረ ነዋሪው ተናግረዋል። የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው ላይ ከደረሱ በኋላ ለጥቂት ሰዓታት ተዘግቶ የነበረው አውራ ጎዳና መከፈቱን ነዋሪው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አድማ ብተና እና የጋሞ ዞን ፖሊስ አባላት “በዛ ብለው” እንደሚታዩም ነዋሪው እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ግን በአካባቢው አለመኖራቸውን የወረዳው ነዋሪ ገልጸዋል።
በትላንትናው ዕለት ሌላው አለመረጋጋት እና ግጭት የተከሰተበት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የጋርዱላ ዞን ነው። በዚህ ዞን ውስጥ በደራሼ ወረዳ ስር የሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት መኖሩን ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ሆልቴ፣ ሀይበና እና ዋሌሳ የተሰኙት ሶስቱ ቀበሌዎች ከማንነት፣ ከእርሻ እና ከግጦሽ መሬት ጋር በተያያዘ ግጭቶች ሲከሰቱባቸው የቆዩ ናቸው። የመከላከያ ሰራዊት ትላንት እሁድ ከእነዚህ ቀበሌዎች ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ፤ በአካባቢው ዳግም ግጭት መቀስቀሱን ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል። ሆኖም የአካባቢው ነዋሪዎች “ስልካችን ሊጠለፍ ስለሚችል የደህንነት ስጋት አለብን” በሚል ምክንያት፤ በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት እና ስለተያያዥ ጉዳዮች ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከዚህ ቀደምም ግጭት እና አለመረጋጋት ከነበረባቸው ሁለት ዞኖች፤ የመከላከያ ሰራዊት ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ “ሂደት በሂደት” ለቅቆ መውጣቱን አንድ የክልሉ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ የሚሰሩት እኚሁ ኃላፊ፤ የመከላከያ ሰራዊቱ ከእነዚህ አካባቢዎች የወጣው “በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ” ጋር በተገናኘ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በአማራ ክልል እና በሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ ከዚህ ቀደም ሲቆጣጠሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች ለቅቀው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አቅጣጫ ሲጓዙ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ባለፉት ቀናት በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወሩ ታይተዋል። የፌደራል መንግስት የመከላከያ ሰራዊት እያካሄደው ያለውን ስምሪት በተመለከተ እስካሁን በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሁለት ዞኖች ለቅቀው መውጣታቸውን ተከትሎ፤ ነባር ግጭቶች ማገርሸታቸውን የክልሉ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እስከዛሬ ሰኞ ረፋድ ድረስ በነበራቸው መረጃ መሰረት በአካባቢዎቹ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ኃላፊው ገልጸዋል።
በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰተው የጸጥታ ችግር፤ ከመዋቅር ጥያቄ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ኃላፊው አመልክተዋል። በዘይሴ ብሔረሰብ ዘንድ የሚነሳውን ከጋሞ ዞን በመውጣት በልዩ ወረዳ የመደራጀት ጥያቄን መነሻ በማድረግ፤ በአካባቢው ተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበር የክልሉ ኃላፊ አስታውሰዋል።
እነዚህ ግጭቶች ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደነበሩ የገለጹት ኃላፊው፤ በግጭቶቹ ምክንያትም በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት ሰፍሮ የማረጋጋት ስራ ሲሰራ እንደቆየም አስረድተዋል። ሰራዊቱ ባለፉት ሶስት ቀናት ውስጥ ከአካባቢው ከወጣ በኋላ “መለስተኛ አለመረጋጋት” መፈጠሩን ያመኑት ኃላፊው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ክልሉ ወደ አካባቢው የአድማ ብተና ኃይል መላኩን ጠቁመዋል።

የክልሉ አድማ ብተና ኃይል በአካባቢው ላይ ከደረሰ በኋላ “አንጻራዊ መረጋጋት መስፈኑን” የገለጹት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ፤ ትላንት አመሻሽ ላይ ተዘግቶ የነበረው አውራ ጎዳናም በአጭር ሰዓታት ውስጥ እንደተከፈተ አመልክተዋል። በጋርዱላ ዞን ባሉት ቀበሌዎች የነበረው ግጭት እና አለመረጋጋት ግን በአርባ ምንጭ ዙሪያ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር “ጠንከር ያለ” እንደሆነ እኚሁ ኃላፊ ተናግረዋል።
በአካባቢው ያለው ግጭት ሁለት መልክ እንዳለው የሚጠቅሱት ምንጩ፤ አንዱ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ቀበሌዎች በእርሻ እና በግጦሽ መሬት ምክንያት የሚያደርጉት “የእርስ በእርስ ግጭት” እንደሆነ አስገንዝበዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የጋርዱላ ዞን ከሌሎች የክልሉ ዞኖች ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ባሉ አራት ቀበሌዎች፤ ከመዋቅር ጥያቄ ጋር የተያያዘ ግጭት እና አለመረጋጋት እንዳለ ኃላፊው ገልጸዋል።
በአራቱ ቀበሌዎች ውስጥ ያለው የመዋቅር ጥያቄ፤ በጋራ በመደራጀት “ራስን በራስ ማስተዳደር” የሚል መሆኑንም ምንጩ አስረድተዋል። የመዋቅር ጥያቄው የቆየ ጉዳይ ቢሆንም እና በአካባቢው ሰፍሮ የነበረው መከላከያ ሰራዊት መውጣቱን ተከትሎ ትላንት እንደ አዲስ ማገርሸቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው አክለዋል።

በጋርዱላ ዞን እና በአዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው አለመረጋጋት፤ የመዋቅር ጥያቄ የሚያነሱ አካላት “የመንግስት ደጋፊ ናቸው” ያሏቸውን ነዋሪዎች ቤት እና ንብረት ማቃጠላቸውን ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በዚህ ድርጊት “በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን” ከአካባቢው የደረሳቸውን መረጃ ጠቅሰው ኃላፊው ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአድማ ብተና ኃይሎች ከጋርዱላ ዞን ፖሊስ አባላት ጋር በመቀናጀት በአካባቢው “አንጻራዊ መረጋጋት” እንዲሰፍን ማድረጋቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። ከአርባምንጭ ወደ ጊዶሌ፣ ኮንሶ እና ጂንካ የሚወስደው የፌዴራል አውራ ጎዳናም ለተሽከርካሪዎች መከፈቱንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























