“ከእያንዳንዱ ግጭት ዕድል ማውጣት ነው የሚጠበቅብን” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 

ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ያሉ “መናጦች” እና “መታወኮችን” ባትፈልግም፤ ከእያንዳንዱ ግጭት “ዕድል  ፈልቅቃ ማውጣት” እንደሚጠበቅባት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ዓለም ባልተናጠችበት ወቅት “ጥቅም አግኝተን፣ ስትናጥ እንደምንጎዳ [በማሰብ] ከእነሱ በላይ መጨነቅ የለብንም” ሲሉም ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት “የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” በተሰኘ ኮንፍረንስ ላይ ከታደሙ ተሳታፊዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ነው። ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጥር 7፤ 2018 የተካሄደው ይህ ኮንፍረንስ፤ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው “የኢኮኖሚ ማሻሻያ” “የተገመገመበት” እና “የመጪው ጊዜ ምልከታ” የቀረበበት መድረክ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

በኮንፍረሱ ቁልፍ የመንግሥት የፋይናንስ እና የዘርፉ ሌሎች ተቋማትን የሚመሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች ገለጻ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በበኩላቸው የኮንፍረንሱ አካል ሆኖ በተሰናዳው “የእሳት ዳር ወግ” ክፍለ ጊዜ፤ ከአወያዩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢሳያስ ካሳ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህንን ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥያቄ ካቀረቡ ተሳታፊዎች መካከል የሲቢኢ የካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ይገኙበታል። በዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት አማካሪነታቸው ይበልጥኑ የሚታወቁት የአቶ ዘመዴነህ ጥያቄ፤ ተነባቢው የአሜሪካው “ኒውዮርክ ታይምስ” ጋዜጣ ከቀናት በፊት በአስተያየት አምዱ ላይ ባወጣው ጹሁፍ ላይ የተንተራሰ ነበር።

ጋዜጣው በቬንዙዌላ እና በኢራን የተከሰቱ ወቅታዊ ጉዳዮችን ሩሲያ በቅርቡ ወደ ዩክሬን ካስወነጨፈችው ሚሳኤል ጋር በማዳመር “ዓለም በትርምስ ውስጥ ናት። በቀጣይ የሚመጣው ምንድነው?” በሚል ጥያቄ የአምስት ጸሀፊያን አስተያየት አስተናግዷል። ከጸሀፊያኑ አንዱ የሆኑት ብራዚላዊው ማቲያስ ስፔክቶር፤ የደቡባዊ ዓለም ሀገራት አንድ ቡድን ፈጥረው አሁን ያለውን ትርምስ እንደሚገዳደሩ ተንብየዋል።

የደቡባዊ ዓለም የሚባለው በዋነኝነት በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ እና በእስያ የሚገኙ፤ በማደግ ላይ እና በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ያሉ ሀገራትን ለመግለጽ የሚውል መጠሪያ ነው። የደቡባዊ ዓለም ሀገራትን ጉዳይ ያነሱት አቶ ዘመዴነህ፤ ኢትዮጵያ ወደ አንድ አቅጣጫ የመወገን አካሄድ ባትከትልም ከአሜሪካ በኩል ግፊት እንዳለ አመልክተዋል።

“ኢትዮጵያ ከምዕራባውያንም፣ ከምስራቁም ከሁሉም ጋር ወዳጅነት አላት። ግን ‘አንዱን ወገን ምረጡ’ የሚል አቋም እየተወሰደ ነው። በተለይ ከዋሽንግተን የሚመጣው። ከማን ጋር የንግድ ልውውጥ እንደምናደርግ፣ ከማን ጋር ኢንቬስት እንደምናደርግ እየተነገረን ነው። መሀል እንድንቀመጥ የሚፈቅድሉን አልመሰለኝም” ሲሉ አቶ ዘመዴነህ የጥያቄያቸውን መንደርደሪያ አሰምተዋል።

“ትልቅ ሀገር ነን። ግን እነሱ ደግሞ ልዕለ ኃያል (superpower) ናቸው። እና side ውሰዱ እያሉን ስለሆነ እንዴት ያዩታል?” ሲሉ ኢትዮ-አሜሪካዊው የኢንቨስትመንት አማካሪ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል። የአቶ ዘመዴነህን ጥያቄ “ወሳኝ” ሲሉ የጠሩት አብይ፤ “አንተም እንደምትገምተው ሙሉውን ዘርዝሬ አልመልሰውም” ሲሉ ምላሻቸው ቁጥብ እንደሚሆን አስቀድመው ጥቆማ ሰጥተዋል።

“ከውጭ የሚመጣን ሀብት ለመጠቀም እስከ መጨረሻው ማድረግ ያለብን ነገር ካለ እናደርጋለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢንቨስትመንትን በሚመለከት ደቡባዊ እና ምዕራባዊ የሚባል ክፍፍል “ያለ አይመስለኝም” ሲሉ አስተያየታቸውን አጋርተዋል። “አንድ የሚባል south እና west ብቻ ሳይሆን፤ አንድ x የሚባል ሀገር ያለ አይመስለኝም። በዚያ ሀገር ውስጥ ከፍተኛ የፖሊሲ፣ የአመለካከት ክፍፍሎች አሉ” ሲሉም አብራርተዋል። 

“በእነዚያ ሁሉ ክፍልፋዮች ውስጥ የእኔ እና የአንተ ስራ እየገቡ opportunities መውሰድ ነው። የሚጣሉ ካሉ ‘እባካችሁ አትጣሉ፣ ጥል አይስፈልግም። ከተጣላችሁም ለቀይ ባህር መሆን አለበት። እንደዚሁ በባዶ አታድርጉት’ ብለን እንመክራለን። ‘ወንድ ልጅ መጣላቱ ካልቀረ፣ ሀገር መጣላቱ ካልቀረ’ ብለን እንመክራለን” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። 

“አንዳንዱ ነዳጅ ያጣላዋል። አንዳንዱ ክብር ያጣላዋል። አንዳንዱ ነገ ማን ይቀድመኛል ያጣላዋል። አንዳንዱ ቀይ ባህር ያጣላዋል። እና እንዳግባቡ መጠቀም ጥሩ ነው ለማለት ነው”

“አንዳንዱ ነዳጅ ያጣላዋል። አንዳንዱ ክብር ያጣላዋል። አንዳንዱ ነገ ማን ይቀድመኛል ያጣላዋል። አንዳንዱ ቀይ ባህር ያጣላዋል። እና እንዳግባቡ መጠቀም ጥሩ ነው ለማለት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዓለም ስትከትለው የቆየችውን “እውነታ” በማጠየቅ የእርሳቸው መንግስት እየተገበረ ነው ያሉትን “ሀገር በቀል እሳቤ” አድንቀዋል።    

“ ‘አንደኛው የዓለም ጦርነት’ ይላል ዓለም። ‘ሁለተኛው የዓለም ጦርነት’ ይላል። ዓለም ማነው?። እኛ እና ጅቡቲ አልተዋጋንም። የእነሱ ጦርነት የዓለም ጦርነት፣ የእነሱ ረሃብ የዓለም ረሃብ፣ የእነሱ እድገት የዓለም እድገት፣ የእነሱ ምቾት የዓለም ምቾት፣ እነርሱ ጋር ያልሆነው ነገር ግን secondary፤ ይሄ ነው የዓለም እውነታ። ለዚህ ነው ሀገር በቀል በሆነ እሳቤ ተያይዘን እንውጣ እያልን ያለነው” ሲሉ አብይ የምዕራቡን እና የደቡቡን ዓለም ምሳሌ በመጥቀስ አነጻጽረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌላ የኮንፍረንሱ ተሳታፊ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም፤ “እግረ መንገድ”፣ “በጨረፍታ ለማሰብ እንዲሆናችሁ” በማለት ከሰሞኑ የዓለም ሁኔታ ጋር የተያያዘ ጉዳይ አንስተዋል። “ሰሞኑን እንደምትሰሙት ዓለም በትልቁም፣ በትንሹም ከባቢ ትናጣለች። ሁሉ ጋር መናጥ አለ” ያሉት አብይ፤ አንድ “የጨነቀው” ወዳጃቸው ከእዚህ ጋር በተያያዘ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ጠቅሰዋል።

“‘ጂኦ ፖለቲክሱ ያስፈራል። ዓለም እየተናጠች ነው። እንደው ይሄ መናጥ ምን ያመጣብን ይሆናል?”’ ብሎ በስጋት ጠየቀኝ…የዓለምን መናጥ እኛ አንፈልግም። የዓለምን መታወክ እኛ አንፈልግም። ዓለም ሰላም በነበረችበት ሰዓት ግን ምን አደረገችልን? ነው መልሱ። ምን አደረገችልን? ሳትናጥ ስትቀር ጥቅም አግኝተን፤ በመናጧ እንደምንጎዳ ከእነሱ በላይ መጨነቅ የለብንም” ሲሉ አብይ ከኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ሳቅ ያስከተለ ምላሽ ሰጥተዋል።

“ከእያንዳንዱ ግጭት opportunity ፈልቅቀን ማውጣት ነው የሚጠበቅብን እንጂ የመጣን ነገር በመፍራት አይሆንም። ሰላም ሲሆኑም ለእነሱ ነው ትርፉ፣ ሲጋጩም ጉዳት ለእነሱ ነው። ሽማግሌ ከፈለጉ እናስታርቃለን። እኛ ግን መስራታችን ብሔራዊ ጥቅም (national interest) ነው” ሲሉም አክለዋል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋም ከኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተለግሶታል።

አብይ በትላንት በስቲያው መድረክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ግጭቶች “መጨነቅ” እና “መፍራት” እንደማያስፈልግ ቢናገሩም፤ ከየመን የሚተኮሱ ሚሳኤሎች እንዴት ኢትዮጵያን እንደሚያስጨንቅ ከሁለት ዓመት በፊት በፓርላማ በቀረቡበት ወቅት አስረድተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያየ ወቅት ባደረጓቸው ንግግሮችም፤ “የመጪው ዓለም ሥርዓትና አሰላለፍ” እንዲሁም “የዓለምን አጠቃላይ እንቅስቃሴ” መገንዘብ እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዳር 2016 መጀመሪያ በፓርላማ ባቀረቡት ማብራሪያ “ትላልቆቹ አገራት አንዳንዴ ሲጨቃጨቁ በሚዲያ ሲጣሉ እኛ እንደነግጣለን። ኬንያ እንደኛ ላትደነግጥ ትችላለች። ታንዛኒያ ላትደነግጥ ትችላለች። ደቡብ አፍሪካ ላትደነግጥ ትችላለች። እኛን የሚያስደነግጠን ምንድን ነው? አንድ ወደብ ነው ያለን” ሲሉ ከየመን ሚሳኤል መተኮስም ሆነ በጅቡቲ የጦር ሰፈር ያላቸው ሀገራት እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ስጋት የሚደቅን እንደሆነ ተናግረው ነበር።

አብይ በዚሁ ማብራሪያቸው “የጅቡቲ ሕዝብና መንግሥት ወንድማችን ነው ችግር የለም። ግን ትላልቆቹ ቢጣሉ፣ ጅቡቲ ላይ ካምፕ ስላላቸው ድንገት ቢታኮሱ፣ የእኛ ቦቴዎች ነዳጅ ሊያመጡ አይችሉም። የጅቡቲ መንግሥት እየፈቀደ፣ የጅቡቲ ሕዝብ እየፈቀደ፣ እኛም ፍላጎት እያለን፣ በሌሎች ግጭት ምክንያት ለአንድ ሣምንት ነዳጅ ባይኖር አስቡት። ማዳበሪያ ካልገባ አስቡት” ሲሉ ለፓርላማ አባላት “ጭንቀታቸውን” አጋርተዋል። 

“[በየመን] ያሉ ኃይሎች ወደ ጅቡቲ ካምፖች [ነገር] ፍለጋ ቢተኩሱ፤ እኛ ወደብ አክሰስ ማድረግ አንችልም። ይሄ የጅቡቲ መንግሥት ሕዝብ የሚያደርግብን ጫና ሳይሆን የጂኦ ፖለቲክሱ መሳከርና አንዳንድ ኃይሎች በርቀት መተኮስ፣ በርቀት መግደል አቅም ስለፈጠሩ [ነው]። እኛ ያ ነገር ቢያጋጥም መቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ ምን እናደርገዋለን ነው ጭንቀታችን። ምርጫ የለንም፣ ያለን አማራጭ አንድ ነው። ይሄንን ቸል ማለት ጥሩ አይደለም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሁኑ አቋማቸው የተቃረነ ማብራሪያ በወቅቱ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)