በኦሮሚያ ክልል፣ ባሌ ዞን፣ ደሎ መና ወረዳ የሚገኘው የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት፤ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ጥቅምት 8፤ 2018 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መመረቁ ይፋ ተደርጓል። ይህ የመስኖ ፕሮጀክት ከታቀደለት ጊዜ በትንሹ ሁለት ዓመት ዘግይቶ እና ቀድሞ ከተያዘለት በተጨማሪ ቢያንስ ሶስት ቢሊዮን ብር ወጪ አስወጥቶ ለምረቃ የበቃ ነው።
ፕሮጀክቱ ከወጣበት ከፍተኛ ገንዘብ ሌላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለት ጊዜ መመረቁም ልዩ ያደርገዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተለያዩ ሰነዶችን እና ዘገባዎችን ፈትሻ፤ የዚህን ፕሮጀክት የኋላ ዳራ፣ አደናጋሪ መረጃዎቹን እና ከመነሻ በጀቱ በላይ የፈሰሰበትን ገንዘብ በተመለከተ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች።
ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያለው እና በወቅቱ “ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት” የሚል ስያሜ የነበረው መገናኛ ብዙሃን በጥር 26፤ 2012 ዓ.ም ያቀረበው ዜና ርዕስ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ ዐቢይ የወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክትን መረቁ” ይላል። ስያሜውን ወደ “ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን” የቀየረው ይኸው መገናኛ ብዙሃን፤ ስለዚሁ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመት በኋላ የሰራው ዜናም ተመሳሳዩን ርዕስ ይዟል።
የዛሬ አምስት ዓመት ከስምንት ወር ገደማ የተሰራው የፋና ዜና፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረቀው የወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት 400 ሄክታር የማልማት አቅም እንዳለው ገልጾ ነበር። ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መገንባቱ የተነገረለት ይህ ፕሮጀክት፤ 1,123 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል እንደሆነ ዜናው አመልክቷል። ዜናው በወጣበት ዕለት የተሰራጨው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃም እነዚሁኑ አሃዞች ይዟል።
ከትላንት በስቲያ የተሰራጨው የፋና የፕሮጀክት ምረቃ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚያኑ ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ያሰፈሩትን መልዕክት ዋቢ ያደረገ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው፤ ፕሮጀክቱ “በሙሉ አቅሙ” ወደ ተግባር በሚገባበት ወቅት፤ ለ9,687.45 ሄክታር የእርሻ መሬት አስተማማኝ የመስኖ አቅርቦት እንደሚኖረው እና በዚህም 20 ሺህ አርሶ አደሮች እንደሚገለገሉ ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርን የሚመሩት ዶ/ር አብርሃም በላይ፤ በትላንትናው ዕለት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ያጋሩት መረጃ ግን የወልመል መስኖ ፕሮጀክት የማልማት አቅሙ 12 ሺህ ሄክታር እንደሆነ ይገልጻል። ሚኒስትሩ ይህንኑ አሃዛዊ መረጃ፤ ፕሮጀክቱ በተመረቀበት ዕለት ባደረጉት ንግግር ላይም ተጠቅመውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትሩ ባገለጿቸው አሃዞች መካከል ያለው ልዩነት፤ የመስኖ ፕሮጀክቱን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜ በወጡ መረጃዎችም ላይ በጉልህ ይታያል። ዶ/ር አብርሃም በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ግንባታ የፈጀው አራት ዓመት ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት ለዚህ በማሳያነት የሚቀርብ ነው።
የእርሳቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስልጣን እና ተግባሩን የተረከበው የቀድሞው መስኖ ልማት ኮሚሽን የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክትን የጀመረው በመስከረም 2012 ዓ.ም እንደሆነ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ኮሚሽኑ በዚሁ ዓመት መገባደጃ ላይ ባዘጋጀው ቪዲዮ፤ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በ2012 በጀት ዓመት 13.88 በመቶ እንደነበር ገልጿል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የ2014 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትም፤ የወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የመስኖ ልማት ኮሚሽን በ2012 በጀት ዓመት ግንባታቸውን ካስጀመራቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ያትታል። በ2011 ዓ.ም የተቋቋመው ይህ ኮሚሽን ያስጀመራቸው፤ የወልመል፣ ጨልጨል፣ ጉደር- ላፍቶ እና የላይኛው ርብ የግድብ እና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው።
አራቱ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ዓመት በአጠቃላይ ያስወጣሉ ተብሎ የተቀመጠው የገንዘብ መጠን 11.374 ቢሊዮን ብር ነበር። የወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪ 2.95 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የመስኖ ልማት ኮሚሽን በ2012 ዓ.ም. አስታውቆ ነበር።
ኮሚሽኑ በ2014 ዓ.ም ሲፈርስ በስሩ የነበረውን የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የተረከበው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ነው። ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ባደረጉት ንግግር፤ የወልመል መስኖ ፕሮጀክት የተጠናቀቀው በ6 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ወጪ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የገንዘብ መጠን ፕሮጀክቱ ሲጀመር ከተያዘለት በሶስት ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያለው ነው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተቻቸው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር መረጃዎች፤ ለፕሮጀክቱ የተያዘው ወጪ በ2015 ዓ.ም. ወደ 3.6 ቢሊዮን ብር ከፍ መደረጉን ያሳያሉ። በዚህ የገንዘብ መጠን እና ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ “በአጠቃላይ ወጪ ተደርጎበታል” ተብሎ በተቀመጠው አሃዝ መካከል እንኳ የ2.4 ቢሊዮን ብር ልዩነት አለ።
በ2015 የፌደራል መንግስት በጀት ለፕሮጀክቱ የተያዘው ገንዘብ 660 ሚሊዮን ብር ነበር። በቀጣዩ በጀት ዓመት ይህ የገንዘብ መጠን ወደ 200 ሚሊዮን ብር ዝቅ ብሏል። ከ2017 የፌደራል በጀት ውስጥ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ የተመደበው 500 ሚሊዮን ብር ነበር። ፕሮጀክቱ በተመረቀበት በዘንድሮው የ2018 በጀት ዓመትም፤ 244 ሚሊዮን ብር በበጀት ዝርዝር ውስጥ ተይዞለታል።
የወልመል መስኖ ፕሮጀክት በተጨማሪነት ያስወጣው ሶስት ቢሊዮን ብር፤ በዘንድሮው የፌደራል በጀት የተያዙ 10 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ጥናት እና ዲዛይን እንደዚሁም የ10 ፕሮጀክቶችን ግንባታ የተያዘውን የገንዘብ መጠን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን ይችል ነበር። የ10 የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ጥናት እና ዲዛይን ለማከናወን በዘንድሮው የፌደራል በጀት የተያዘው የገንዘብ መጠን 418.8 ሚሊዮን ብር ነው።

ጥናት እና ዲዛይን በዚህ ዓመት ይደረግላቸዋል ተብለው በበጀት ሰነዱ የተያዙት፤ በታችኛው በለስ፣ አንገረብ፣ ወይጦ፣ ራሚስ፣ ዜንቲ፣ ሎኮ አባያ፣ ኪሎ፣ መጫላ፣ ተላ እና ሽንፋ የሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ናቸው። ለፈንታሌ፣ ለአንገር፣ ለላይኛው ርብ፣ ለኬጦ፣ ለወይቦ፣ ለሽንሌ እና ለጎዴ የመስኖ ልማቶች ግንባታ በዘንድሮው የፌደራል በጀት የተያዘው የገንዘብ መጠንም፤ የወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክት ባስወጣው ተጨማሪ ወጪ መሸፈን ይችል ነበር።
ተጨማሪው የሶስት ቢሊዮን ብር ወጪ፤ ከላይ ከተጠቀሱት ፕሮጀክቶች ሌላ ለአደአ በቾ የከርሰ ምድር ውሃ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ እና ለከሰም መስኖ ልማት ማጠናቀቂያ የተመደበውን የገንዘብ መጠን መሸፈን ይችላል። በ2018 የፌደራል በጀት ለሶስት የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የተመደበው የ“ሪቴኔሽን” ክፍያም፤ የወልመል ፕሮጀክት ባስወጣው ተጨማሪ ወጪ የመሸፈን ዕድል ነበረው።
እንደ ወልመል ወንዝ ፕሮጀክት ያሉ ግዙፍ ግንባታዎች ዘግይቶ መጠናቀቅ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስትም ሆነ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ በተደጋጋሚ ከሚያስተጋቡት ትርክት ጋር የተቃረነ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ባደረጓቸው ንግግሮች፤ መንግስታቸው ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ የመጨረስ “ብቃት” እንዳለው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

እርሳቸው በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲም፤ “የገባውን ቃል የሚፈጽም” እና ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ጀምሮ የመጨረስ ልምምድን ባህል ወደ ማድረግ እየተሸጋገረ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። በወልመል ወንዝ የመስኖ ፕሮጀክት ለታየው የዓመታት መዘግየት፤ ግንባታውን በሚያሰሩት፣ በሚቆጣጠሩት እና በሚያከናውኑት አካላት የተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው ሲነሱ ቆይተዋል።
ለግንባታው መጓተት ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ፕሮጀክቱን የተረከቡት ኮንትራክተሮች አቅም ውሱንነት፣ የጸጥታ ችግር፣ የወሰን ማስከበር፣ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ የሲሚንቶ እና የነዳጅ እጥረቶች ይገኙበታል። በሁለት ክፍሎች የተከፈለውን የወልመል ወንዝ የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ሲያከናውኑ የቆዩት፤ አለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ እና የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ናቸው።
ሁለቱ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች 50 ሜትር ስፋት ያለው የውሃ መቀልበሻ ውቅር፣ 144 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ቦይ (ካናል)፣ 60 ኪሎ ሜትር መጋቢ የመንገድ ስራ፣ 45 ውሃ ማጠራቀሚያ ኩሬ (ፖንድ) እንደዚሁም 50 ብሎኮች የያዘ የግድብ አስተዳደር ማዕከል እና መኖሪያ ግንባታን አከናውነዋል። ድርጅቶቹ ግንባታዎቹን በመጀመሪያ በታቀደለት ሶስት ዓመት እንደሚያጠናቅቁ በተደጋጋሚ ቢገልጹም፤ በተጨማሪነት ከተሰጣቸው ጊዜ ጋር ተደምሮ በትንሹ ሁለት ዓመት ዘግይተዋል።

የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት በብዙዎቹ የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሚታየው መጓተትን ቢያስተናግድም፤ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ግን ግንባታው “በስኬት” መጠናቀቁን በምረቃ ንግግራቸው ላይ አብስረዋል። ሚኒስትሩ ለዚህ “ስኬት” “ቁርጠኛ እና በሳል አመራር” ሰጥተዋል ያሏቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን “የላቀ አክብሮት እና ምስጋናቸውን” አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)