በቤርሳቤህ ገብረ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የዛሬ ሁለት ሳምንት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው ላይ ያጸደቀው የክልሉ ህገ መንግስት ማሻሻያ፤ “የኢፌዲሪን ህገ መንግስት የሚቃረን ነው” ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት “ተፈጻሚ እንዳይሆን” አቤቱታ አቀረቡ። የምክር ቤት አባላቱ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ለፌደራል የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ነው።
የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፤ በተለያዩ አካላት የሚቀርቡለትን ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን ያለው ነው። ጉባኤው በሚያደርገው ማጣራት መሰረት ህገ መንግስቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል። አጣሪ ጉባኤው፤ በተሻሻለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት ላይ ትርጓሜ የሚጠይቅ አቤቱታ እንደቀረበለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።
ይህን አቤቱታ በትላንትናው ዕለት ያቀረቡት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ተመራጭ የሆኑት አቶ አመንቴ ገሺ፣ አቶ ዮሐንስ ተሰማ እና ተስፋሁን ኪሉ ናቸው። ሶስቱ የቦዴፓ የክልል ምክር ቤት ተመራጮች የህገ መንግስት ትርጉም ከጠየቁባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ማደግን የተመለከተው ይገኝበታል።

በ1995 ዓ.ም የወጣው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት፤ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ100 እንደማይበልጥ ይደነግጋል። የምክር ቤቱ አባላት ቁጥርም፤ የህዝብ ብዛትን መሰረት ያደረገ እንደሚሆንም በህገ መንግስቱ ላይ ሰፍሯል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የህግ አውጪ አካል የሆነው የክልሉ ምክር ቤት የካቲት 11፤ 2017 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው፤ ይህንን የሚቀየር የህገ መንግስት ማሻሻያ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። አዲሱ የህገ መንግስት ማሻሻያ፤ የክልሉ ምክር ቤትን መቀመጫ አሁን ካለበት 99 ወደ 165 ከፍ አድርጓል።
ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታቸውን ያቀረቡ የምክር ቤት አባላት፤ ክልሎች የህገ መንግስት ማሻሻያ ስርአትን ተከትለው የምክር ቤቶቻቸውን የመቀመጫ ወንበር የመወሰን መብት እንዳላቸው ጠቅሷል። ይሁን እንጂ አሁን የተሻሻለው 165 የምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት፤ አሁን በስራ ላይ ለሚገኙ የምርጫ ክልሎች የተከፋፈለበት መንገድ “የህዝብ ብዛት ያማከለ አይደለም” ሲሉ ሶስቱ የምክር ቤት አባላት በአቤቱታቸው ላይ አስፍረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ነባር የምርጫ ክልሎችን የፈረሱበትን እና አዳዲስ የምርጫ ክልሎች የተቋቋሙበት ሂደት “ህገ መንግስቱን የጣሰ፣ ኢ-ፍትሃዊ፣ አድሎአዊና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ስልጣንና ተግባር የተጋፋ ነው” ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ተችተዋል። በ1987 ዓ.ም. በምርጫ ቦርድ እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አማካኝነት የተቋቋሙት የምርጫ ክልሎች ኦሶሳ ሆሃ፣ አሶሳ መገሌ እና መንጌ የሚባሉ እንደሆኑ በአቤቱታው ላይ ተጠቅሷል።
አዲሱ ማሻሻያ እነዚህን በማፍረስ፤ አብራሞ፣ ኡራ፣ ኡንዱሉ፣ አሶሳ ከተማ ወረዳ አንድ እና አሶሳ ከተማ ወረዳ ሁለት የተባሉ አምስት የምርጫ ክልሎችን ማቋቋሙንም የክልሉ ምክር ቤት አባላት በአቤቱታቸው አንስተዋል። “ለአስተዳደር ተብለው የተቋቋሙትን እነዚህ አምስት ወረዳዎች፤ እንደ ምርጫ ክልል ተቆጥረው 31 የክልል ምክር ቤት መቀመጫ ተሰጥቷቸዋል” የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ ሂደት የኢፌዲሪን ህገ መንግስት እና ሌሎች የፌደራል አዋጆችን “የሚጻረር” እንደሆነ አመልክተዋል።
ለክልሎች የተሰጠው ስልጣን “የክልል ምክር ቤትን የመቀመጫ ጥቅል ብዛት መወሰን እና የአካባቢ ምርጫን የሚመለከት ነው” ሲሉ በአቤቱታቸው ያሰፈሩት ሶስቱ ተመራጮች፤ ክልሎች የምርጫ አከላለልን በተመለከተ “ስልጣን የላቸውም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ይህንን ህገ መንግስታዊ መርህ ጥሷል” ሲሉም ከስሰዋል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የምርጫ ክልሎችን ማካለል እንደ ሀገር “የህገ መንግስት ማሻሻያ የሚፈልግ በመሆኑ” በመጪው ሀገራዊ ምክክር በአጀንዳነት ውስጥ መያዙን በመጥቀስም ትችታቸውን ሰንዝረዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ወደ ህገ መንግስት ማሻሻያ ፈጥኖ መግባቱ የሀገራዊ ምክክሩን አላማ የሚጋፋ ጭምር ነው” ሲሉ የክልል ምክር ቤት አባላቱ ነቅፈዋል።
ሶስቱ ተመራጮች ህገ መንግስታዊ ትርጉም የጠየቁበት ሌላው ጉዳይ፤ አዲሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት ቁጥር “የህዝብ ብዛትን መሰረትን ያላደረገ ነው” በሚል መነሻነት ነው። አቤቱታ አቅራቢዎቹ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎቹን “በህዝብ ቁጥር ሳይሆን በወረዳ ብዛት አከፋፍሏል” ባይ ናቸው።
“የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሳይደረግ እያንዳንዱ ወረዳ ያለውን የህዝብ ብዛት ወደ ወንበር መቀየር ሲገባ፣ አንስተኛ ቁጥር ላለው ወረዳ በርካታ መቀመጫ፣ በርካታ የህዝብ ቁጥር ላላቸው ወረዳዎች ደግሞ አነስተኛ መቀመጫ ተሰጥቷል” ሲሉ የምክር ቤት አባላቱ በአቤቱታቸው ላይ አመልክተዋል። ይህ አካሄድ ዜጎች “በወኪሎቻቸው እና በራሳቸው ሉዓላዊነታቸውን የሚገልጹበትን ዴሞክራሲያዊ መብት የሚጻረር” እንዲሁም በኢፌዲሪ ህገ መንግስት የተቀመጠውን “የዜጎችን እኩልና ፍትሃዊ የፖለቲካ ተሳትፎ መብት የሚጋፋ ነው” ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ነቅፈዋል።

ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታቸውን ያቀረቡት የምክር ቤት አባላት ሌላው ያነሱት ጉዳይ፤ የህገ መንግስት ማሻሻያው እንዲጸድቅ የደገፉት የወረዳ ምክር ቤቶች የስልጣን ጊዜ ያበቃ መሆኑን ነው። የክልሉ ህገ መንግስት የወረዳ ምክር ቤቶች የስልጣን ዘመን አምስት ዓመት እንደሆነ መደንገጉን የጠቀሱት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ በ2005 ዓ.ም በተካሄደ የአካባቢ ምርጫ የተመረጡ ሁሉም የወረዳ ምክር ቤቶች “የስልጣን ጊዜ አብቅቷል” ሲሉ ይሟገታሉ።
“የአካባቢ ምርጫ ተካሄዶ የወረዳው ምክር ቤት [አባላት] ስላልተመረጡ፤ አሁን ያሉት ህገ መንግስታዊ አይደሉም። የክልሉ ህገ መንግስትም እንዲሻሻል ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም። ውሳኔ ቢያሳልፉም እንኳ የስልጣን ጊዜያቸው ያበቃ በመሆኑ እና ህገ መንግስታዊ ስልጣን በሌለው አካል የተላለፈ ውሳኔ በመሆኑ፤ ኢ-ህገ መንግስታዊ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ የክልል ምክር ቤት አባላቱ አቤት ብለዋል።
በ1995 ዓ.ም የወጣው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት፤ የክልሉ ህገ መንግስት የሚሻሻለው በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የወረዳ ምክር ቤቶች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በአብላጫ ድምጽ ሲያጸድቁት እንደሆነ ይደነግጋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የካቲት 11፤ 2017 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ላይ አፈ ጉባኤ አስካል አልቦሮ፤ የህገ መንግስት ማሻሻያው ሂደት “ህጋዊ ስርአቱን ተከትሎ” መካሄዱን ገልጸው ነበር።

በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የወረዳ ምክር ቤቶች ቀደም ብለው ባካሄዷቸው ስብሰባዎች፤ በህገ መንግስት ማሻሻያው ላይ መወያየታቸው በዚሁ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተነስቷል። የወረዳ ምክር ቤቶቹ ከውይይታቸው በኋላ ማሻሻያውን ከሁለት ሶስተኛ በላይ በሆነ ድምጽ ማጽደቃቸውም ተብራርቶ ነበር።
በወረዳ ምክር ቤቶች የጸደቀ የህገ መንግስት ማሻሻያ፤ በክልሉ ምክር ቤት አባላት በአራት ሶስተኛ ድምጽ መጽደቅ እንዳለበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት ላይ ተደነግጓል። ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታቸውን ካቀረቡ የምክር ቤት አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ተሰማ፤ እርሳቸውን ጨምሮ ሶስቱም የቦዴፓ ተመራጮች የህገ መንግስት ማሻሻያው በአብላጫ ድምጽ ሲጸድቅ እንደተቃወሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የህገ መንግስት ማሻሻያው አዋጅ ለምክር ቤት አባላት የተሰጣቸው መደበኛ ጉባኤው በተጀመረ በሶስተኛው ቀን እንደነበር የገለጹት፤ የማሻሻያ ሂደቱ “ድብቅ ነበር” ሲሉ ተችተዋል። “ ‘ለምንድን ነው በግልጽ ተወያይተን፣ ተሳትፈን፣ ሀሳብ አስተያየት ሰጥተን የማይመጣው?’ ብለን ስንጠይቅ መልስ የለም። እነሱ 88 ናቸው እኛ ሶስት ነን” ሲሉ በእነርሱ እና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ የክልል ምክር ቤት ተመራጮች መካከል ባለው ልዩነት ምክንያት ውሳኔውን በድምጽ የመቀየር እድላቸው ዝቅተኛ እንደነበር አብራርተዋል።
“ ‘ለምንድን ነው በግልጽ ተወያይተን፣ ተሳትፈን፣ ሀሳብ አስተያየት ሰጥተን የማይመጣው?’ ብለን ስንጠይቅ መልስ የለም። እነሱ 88 ናቸው እኛ ሶስት ነን”
– አቶ ዮሐንስ ተሰማ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የቦዴፓ ተመራጭ
አቶ ዮሐንስ እና ሁለቱ የቦዴፓ ተመራጮች ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባስገቡት አቤቱታ ማጠቃለያ ላይ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ምክር ቤት ያጸደቀውን ህገ መንግስት ማሻሻያ “ኢ-ህገ መንግስታዊ፣ ያልነበረ እና ያልተደነገገ” እንዲባል እና እንዲቆጠር ጠይቀዋል። የህገ መንግስት ማሻሻያው “ተፈጻሚ እንዳይሆን ተብሎ እንዲወሰንም” ለአጣሪ ጉባኤው በተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)