በታራሚዎች ላይ “የአማራጭ ቅጣትን” ለመተግበር የሚያስችል የአዋጅ ረቂቅ በቅርቡ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው

የፍትሕ ሚኒስቴር በእስር የሚቆዩ ታራሚዎችን ቁጥር “ከፍተኛ በሆነ መንገድ” ለመቀነስ ያስችላል ያለውን “የአማራጭ ቅጣት ስርዓትን” ለመተግበር ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን አስታወቀ። የአዋጁ ረቂቅ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብም ሚኒስቴሩ ገልጿል። 

መስሪያ ቤቱ ይህን የገለጸው፤ የሚኒስቴሩን የ2018 በጀት ዓመት እቅድ እና የሩብ ዓመት ስራ አፈጻጸም በተገመገመበት መድረክ ላይ ነው። የፊት ለፊት የግምገማ መድረኩን ያዘጋጀው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። 

ትላንት ረቡዕ ጥቅምት 12፤ 2018 በተካሄደው በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ የቋሚ ኮሚቴው አባላት በርካታ ጥያቄዎችን አቅርበው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በቋሚ ኮሚቴ አባላት ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፤ ተጠሪነታቸው ለፍትሕ ሚኒስቴር የሆኑት የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን የተመለከቱት ይገኙበታል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በፓርላማ የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኢሳ ቦሩ፤ የፍትህ ሚኒስቴር ሰብዓዊ መብትን ማክበር እና ማስከበርን በተመለከተ በዘረዘረበት የእቅዱ ክፍል ላይ የታራሚዎችን አያያዝ ማካተቱን በጥሩነት ጠቅሰዋል። ቋሚ ኮሚቴው ባለፈው ዓመት በነበረው የቁጥጥር እና ክትትል ስራው “በክፍተትነት” ካያቸው ጉዳዮች፤ ከእናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤት የሚቆዩ ህጻናትን የሚመለከተው አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል።

“በማረሚያ ቤት ከእናታቸው ጋር ያሉ ህጻናትን በሚመለከት በጣም ከፍተኛ እጥረት ነው ያለው። በመንግስት ደረጃ በጀት አይመደብላቸውም። ግን ብዙ ህጻናቶች አሉ። የእነሱን መብታቸውን ለማስከበር ምንድነው የታሰበው?” ሲሉ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጠይቀዋል።

ለዚህ ጥያቄ ቅድሚያ የመመለስ ዕድል ያገኙት የፍትሕ ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኡመድ ኡጁሉ ናቸው። ከእናቶቻቸው ጋር ታስረው የሚገኙ ህጻናት ጉዳይ “በጣም ቴክኒካል” እንደሆነ የገለጹት አቶ ኡሙድ፤ በቋሚ ኮሚቴው የተነሳውን ሃሳብ “እንደ ቴክአዌይ” በመውሰድ “በሚመለከተው አካል” ማጣራት እንደሚደረግበት አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ግን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ተቋም በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ረገድ “ብዙ መሻሻሎች” ማድረጉን አማካሪው ጠቁመዋል። ይህን “የተሻሻለ ሁኔታ” መስሪያ ቤታቸው ተቋሙን በገመገመበት ወቅት መመልከቱን የጠቀሱት አቶ ኡመድ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) በማረሚያ ቤቶች ጉብኝት ካደረገ በኋላ ተመሳሳዩን ግብረ መልስ ለሚኒስቴሩ መስጠቱን አብራርተዋል። 

ኢሰመኮ ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ባወጣው ዓመታዊ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ፤ በ2017 በጀት ዓመት በአጠቃላይ በ66 ማረሚያ ቤቶች እና 473 ፖሊስ ጣቢያዎች እንዲሁም 9 መደበኛ ያልሆኑ ማቆያ ስፍራዎች ክትትል ማከናወኑን አስታውቆ ነበር። ኮሚሽኑ በክትትሉ የለያቸውን “መልካም እመርታዎች” በሪፖርቱ በዝርዝር አመላክቷል።

ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ በዚሁ ሪፖርቱ በማረሚያ ቤቶች ያሉ “አሳሳቢ” ጉዳዮችንም አካትቷል። የፍትሕ ሚኒስቴር አማካሪው አቶ ኡመድ በትላንቱ ማብራሪያቸው፤ በማረሚያ ቤቶች ከጥበቃ እና ከቀለብ ጋር ተያይዞ “ክፍተቶች” እንዳሉ አልሸሸጉም።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“ቀለብን በሚመለከት የፌደራል በጣም ዝቅተኛ ነው። እንደውም ክልሎች ከፌደራል ይሻላሉ። ይሄን ስንገመግም፤ ይሄ የቀለብ ጉዳይ አነስተኛ ስለሆነ የሚጨመርበት ወይም በጀት የሚፈቀድበት መንገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ለሚመለከተው አካል በደብዳቤ የጠየቀበት ሁኔታ ነው ያለው። መልሱ አልመጣም” ሲሉ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት አስረድተዋል።

ለማረሚያ ቤቶች የሚመደበው የቀለብ በጀት አነስተኛ መሆን በፓርላማ ስብሰባዎች ላይ ሲያነጋግር የትላንቱ የመጀመሪያው አይደለም። ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የፍትሕ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ ጥያቄው ቀርቦላቸው፤ በጀቱ የታራሚዎችን ቀለብ ለመሸፈን በቂ እንዳልሆነ አረጋግጠው ነበር።

በፓርላማ በጸደቀው የ2018 በጀት፤ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን “የመሰረታዊ ፍላጎት አገልግሎት ለመስጠት” የተመደበለት የገንዘብ መጠን 831 ሚሊዮን ብር ነው። ኮሚሽኑ ለተመሳሳይ አገልግሎት በ2017 የፌደራል በጀት ተመድቦለት የነበረው 700.4 ሚሊዮን ብር ነበር። 

የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በትላንቱ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ፤ የማረሚያ ቤት ጉዳይ የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት (intervention) የሚፈልግ እንደሆነ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። “አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ በጣም በርካታ ታራሚ ነው ያለው። ይሄን ሁሉ ታራሚ ይዘን፣ ይሄን ሁሉ እየቀለብን፣ ህክምና እንዲህ እያልን መቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ አለ ብለን አናስብም” ሲሉ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ የማዘጋጀቱ ጉዳይ ለነገ የሚባል እንዳልሆነ አብራርተዋል። 

በዚህ ረገድ ሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው፤ “በርካታ ስራዎችን” ለማከናወን ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህ በማሳያነት በመጀመሪያ የጠቀሱት በጉዳዩ ላይ እየተከናወነ ያለውን ሀገር አቀፍ ጥናት ነው። ጥናቱ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጣ ኮሚቴ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል። 

ኮሚቴው በጥናቱ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል “በሀገር አቀፍ ደረጃ የማረም እና የማነጽ አገልግሎት (prison service standard)  ምን ይመስላል?” የሚለው አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል። በዚህ ጥናት አገልግሎቱ ብቻ ሳይሆን አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አደረጃጀታቸው እንደሚፈተሽም አክለዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“የማረም እና ማነጽ ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎች ከምልመላቸው ጀምሮ፣ ስልጠና፣ የስራ ስምሪታቸው በጣም ወጣ ገባ ነው። ትጥቃቸውን እንኳ ብናይ በጣም ወጣ ገባ ነው። አንዳንዱ የሚሊተሪ አይነት ባህሪ አለው። ትጥቅ ይታጠቃል። አንዳንዱ የመከላከያ [ሰራዊትን] ትጥቅ የሚመስል ይታጠቃል። ይሄ ሁሉ መልክ መያዝ አለበት” ብለዋል አቶ በላይሁን።

የማረሚያ ቤት ስልጠና እና አስተዳደርን ብቻ ሳይሆን “የታራሚዎችን ቁጥር ከፍተኛ በሆነ መንገድ ሊቀንስ የሚያስችል ስርዓት” እንደሚያስፈልግም የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታው በትላንቱ ማብራሪያቸው ላይ አንስተዋል። የፍትሕ ሚኒስቴር ለዚህ የሚረዳ አማራጭ ቅጣት ረቂቅ አዋጅን እያዘጋጀ መሆኑን እና በቅርቡም ወደ ፓርላማ ለማምጣት ማቀዱን ተናግረዋል።  

“በርካታ ሰዎች ወደ ማረሚያ ቤት ከሚሄዱ ይልቅ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡበትን ስርዓት የሚዘረጋ አዋጅ ነው። ይሄ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለን እናስባለን” ሲሉም አቶ በላይሁን አስረድተዋል።  ብዙ ሀገራት ከታራሚዎቻቸው ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑትን በዚህ ስርዓት የሚያስተናግዱ መሆኑንም አመልክተዋል።  

የአሜሪካዋ ኖርዝ ካሮላይና ግዛት ጥፋት ከሚፈጽሙ ወንጀለኞች መካከል 63 በመቶ ገደማ ያህል የሚሆኑት የማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረጉ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው አንድ ሰነድ ያመለክታል። የካናዳ የፍትሕ መስሪያ ቤት ከአምስት ዓመት በፊት ባጠናቀረው ስታትስቲክስ 75 በመቶ ወይም ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ ካናዳውያን፤ በሰው ላይ ጉዳት ያላደረሰ ወንጀል በፈጸሙ ጥፋተኞች ላይ ማህበረሰብን መሰረት ያደረገ ቅጣት ቢጣልባቸው እንደሚደግፉ ይፋ አድርጎ ነበር።

የፍትሕ ሚኒስቴር ዴኤታው በኢትዮጵያ “ታራሚዎች ታርመው፣ ታንጸው ከወጡ በኋላ ‘የት ነው የሚሄዱት?’ የሚለው የመልሶ የመቀላቀል ስርዓት (reintegration system) የለም” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። “ይሄም የፖሊሲ intervention የሚፈልግ ነው። እርሱም ላይ ረቂቅ አዋጆች ተዘጋጅተዋል” ሲሉ መስሪያ ቤታቸው ይህን በተመለከተ የህግ ማዕቀፍ ማርቀቁን አስታውቀዋል።   

“እነዚህን ተግባራዊ ስናደርግ፣ ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ችግሩን የምንቀርፍ ካልሆነ በስተቀረ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ሰው እየመደብን፣ በጀቱን ከፍ ዝቅ እያደረግን ቋሚ መፍትሔ አይሆንም። ለጊዜው መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል ግን ይሄ ቋሚ መፍትሔ ስለማይሆን [አዋጆቹ] እነዚህን ችግሮች በሙሉ ይፈታሉ ብለን የምናስበው” ሲሉም አቶ በላይሁን አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)