ብሔራዊ ባንክ “በህገ ወጥ” ገንዘብ አስተላላፊዎች ላይ “የማያዳግም” “ሰፊ እርምጃ” ለመውሰድ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “ህገ ወጥ ስራዎችን” ያከናውናሉ ባላቸው የሃዋላ አስተላላፊዎች ላይ “የማያዳግም” “ሰፊ እርምጃ” ለመውሰድ መዘጋጀቱን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ተናገሩ። ባንኩ የሚወስደው እርምጃ “የኢትዮጵያን እና የዓለም አቀፍ ህግን የጠበቀ” እንደሚሆን የገለጹት የብሔራዊ ባንክ ገዢው፤ በዚህ ተግባር የተሰማሩ ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እና “አስፈላጊውን ጥንቃቄ” እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ዶ/ር እዮብ “የመጨረሻ” ያሉትን ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት፤ በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ የሃዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው። የብሔራዊ ባንክ ገዢው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያቀኑት፤ የዓለም ባንክ ግሩፕ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባዎችን ለመካፈል ነው። 

በዋሽንግተን ዲሲው የሃዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች ውይይት፤ የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር አመራሮች ተገኝተዋል። የውይይቱ ትኩረት “በህጋዊ በሆነ መንገድ መስራት እየፈለጉ ተገቢውን ድጋፍ ያላገኙ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን እንዴት እንደግፍ?” የሚል እንደነበር ዶ/ር እዮብ ተናግረዋል። 

በእነዚህ ድርጅቶች በችግርነት ለተነሱ ጉዳዮች፤ ብሔራዊ ባንክ እና የባንክ አመራሮች “አስፈላጊውን ድጋፍ” ለማድረግ ማረጋገጫ መስጠታቸውን ገዢው ጠቁመዋል። የብሔራዊ ባንክ ትኩረት “በርካታ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ህጋዊ በሆነ መንገድ ሰርተው ዘላቂነት ያለው ቢዝነስ ውስጥ እንዲቆዩ ነው” ያሉት ዶ/ር እዮብ፤ ሆኖም የተወሰኑ ድርጅቶች “የአጭር ጊዜ ትርፍ” ለማግኘት “በህገ ወጥ ስራ” ላይ ከመሰማራት እንዳልተቆጠቡ አስረድተዋል። 

“የterrorism financing ወይም money laundering የምንለው ላይ የተሰማሩ፤ የተወሰኑ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት እንዳሉ ደርሰንበታል። እዚህ ላይ በጣም የተናበበ፣ የተቀናጀ ሰፊ እርምጃ ለመውሰድ ነው ያሰብነው። ይሄንን አስቀድመን በግልጽ ነግረናቸዋል” ብለዋል የብሔራዊ ባንክ ገዢው።

ብሔራዊ ባንክ በህገ ወጥ ተግባራት የተሰማሩ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን በምርመራ እንደደረሰባቸው ሲያስታውቅ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ባንኩ በሐምሌ 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉ አራት የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት ሰጪዎች “በወንጀል የተገኘ ንብረትን ህጋዊ የማስመሰል እና ህገ ወጥ ተግባራትን ፋይናንስ በማድረግ ተግባር ተሳትፈዋል” በሚል ወንጅሎ ነበር።

ባንኩ በእነዚህ ድርጅቶች ላይ እያከናወነ ያለውን ምርመራ እንደሚቀጥል እና “ተገቢ እርምጃዎችን” እንዳስፈላጊነቱ በቀጣይ እንደሚወስድም በወቅቱ አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ የገዢው የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት ባለፈው ነሐሴ ወር ካደረገው ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ “በውጭና በሀገር ውስጥ” ባለው የውጭ ምንዛሬ እንቅስቃሴ ላይ “የኢኮኖሚ አሻጥር” እንደሚደረግ መግለጹ አይዘነጋም።

ፓርቲው የውጭ ምንዛሬ እንቅስቃሴውን “በሀገር ፍቅር ስሜት እንዲንቀሳቀስ በማድረግ”፤ “የኢኮኖሚ አሻጥር” ይሰራሉ ያላቸውን “የውጭ እና የውስጥ ጠላቶችን” ለመታገል ከውሳኔ ላይ መድረሱን በወቅቱ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል። ባለፈው መስከረም ወር የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር እዮብ፤ መስሪያ ቤታቸው በህገ ወጥ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ “ሰፊ ዝግጅት” ማድረጉን ተናግረዋል።

“የብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ማንኛውንም እርምጃ ከመውሰድ የሚቆጠብ አይሆንም። አካውንት ብቻ በመዝጋት የሚመለስ ነገር እንዳልሆነም በግልጽ ማንሳት እፈልጋለሁ። ተቀባዮቹንም ያካተተ፣ ላኪዎቹንም ያካተተ ሰፊ የማጥራት ስራ ሰርተናል። ወደ ተቀናጀ እርምጃ እየገባን ነው” ሲሉ የባንኩ ገዢ ዛሬ በተሰራጨ ማብራሪያቸው ላይ አመልክተዋል። 

ባንኩ የሚወስደው እርምጃ “የማያዳግም” እንደሚሆን የገለጹት ዶ/ር እዮብ፤ በህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሃዋላ አስተላላፊዎች “የመጨረሻ ማሳሰቢያ መሆኑን አውቀው” ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አበክረው አሳስበዋል። በእነዚህ ተቋማት በኩል ገንዘብ የሚልኩ ዜጎች እና ከድርጅቶቹ ጋር የሚሰሩ በተለያየ የንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ አስመጪ እና ላኪዎችም፤ ከድርጊቶቻቸው እንዲቆጠቡ መክረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)