ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት ሶስት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ካገኘችው 2.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ወርቅ፣ ቡና እና አበባ መሆናቸውን የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱ ከወርቅ ሽያጭ ብቻ ያገኘችው ገቢ 1.2 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
ዶ/ር ፍጹም ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ጥቅምት 12፤ 2018 በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመቶ ቀናት እቅድ ግምገማ ላይ ባቀረቡት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርት ነው። የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ መንግስት ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ውጪ ከሚላኩ ሸቀጦች ለማግኘት አቅዶ ከነበረው ገቢ “ከመቶ ፐርሰንት በላይ” ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከዚህ ዘርፍ ለማግኘት አቅዳ የነበረው የገንዘብ መጠን 2.1 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ከእቅድ በላይ 117 በመቶ ስኬት የተመዘገበበት እንደሆነ በተገለጸው የወጪ ንግድ ዘርፍ ከፍተኛውን የገቢ ድርሻ የያዙት ወርቅ እና ቡና ናቸው።

ባለፉት ወራት በዓለም ገበያ ያለው የሁለቱ ሸቀጦች የመሸጫ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶበታል። ኢትዮጵያ የምታመርተው “አረቢካ” ተብሎ የሚጠራው የቡና ዝርያ ዋጋ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን “ብሉምበርግ” የተሰኘው የዜና አውታር ዘግቧል።
በተመሳሳይ መልኩ በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆቹ 2025 ዓመት የወርቅ ዋጋ በ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጎልድማን ሳክስ የተባለው የኢንቨስትመንት ባንክ ባለፈው መስከረም ወር ያወጣው መረጃ ያሳያል። ባንኩ የወርቅ ዋጋ በመጪው የፈረንጆቹ 2026 ዓመት በስድስት በመቶ ከፍ እንደሚልም ትንበያውን አስቀምጧል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት ከወርቅ ያገኘችው የገቢ መጠን 1.2 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ለፌደራል መንግስት ካቢኔ አባላት ተናግረዋል። ይህ የገቢ መጠን መንግስት በእቅድ ከያዘው 135.7 በመቶውን ያሳካ እንደሆነም በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
ከወርቅ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 116 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑንም ዶ/ር ፍጹም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ባለፉት 100 ቀናት የተመረተው 11.47 ቶን ወርቅ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 66 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
በ2017 የመጀመሪያ ሶስት ወራት 6.39 ቶን የተመረተ ሲሆን፤ በዘንድሮው ተመሳሳይ ወቅት 8.37 ቶን ወርቅ ይመረታል የሚል ዕቅድ በፌደራል መንግስት ተቀምጦ ነበር። በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ እና በአሁኑ ወቅት “በሙከራ ስራ ላይ” እንደሆነ የተገለጸው የኩምሩክ ጎልድ ማይኒንግ፤ በዓመት ከአምስት እስከ ሰባት ቶን የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል።
ከወርቅ ቀጥሎ ባለፉት ሶስት ወራት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ገቢ ያስገኘው፤ ለረጅም ዓመታት የሀገሪቱ “የኢኮኖሚ ዋልታ” በሚል ቅጥያ ሲጠራ የቆየው ቡና ነው። ኢትዮጵያ በዘንድሮው በጀት ዓመት ሶስት ወራት ከቡና ሽያጭ ያገኘችው 763 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ዶ/ር ፍጹም አስታውቀዋል።

ይህ የገቢ መጠን ከእቅድ አኳያ “115 በመቶ” አፈጻጸም ያለው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፍጹም፤ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር “በእጅጉ ከፍ ያለ ነው” ብለዋል። የባለፉት ሶስት ወራት የቡና ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 47 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑም አክለዋል።
ከወርቅ እና ቡና ቀጥሎ በወጪ ንግድ ዘርፍ ከፍተኛውን ገቢ ያስገቡት አበባ፣ ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርበው የኤሌክትሪክ አግልግሎት እና የቁም እንስሳት ሽያጭ ናቸው። ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ቀናት ከአበባ ያገኘችው ገቢ 111 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
የአበባ የወጪ ንግድ ከእቅድ አኳያ “ጥሩ አፈጻጸም” ያለው መሆኑም ዶ/ር ፍጹም ተናግረዋል። መንግስት ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ውጭ ሀገራት ከሚላከው አበባ ለማግኘት ካቀደው ገቢ ያሳካው 81 በመቶውን ነው። የሶስት ወራቱ ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር “የተሻለ አፈጻጸም” እንዳለው በሚኒስትሯ ቢጠቀስም፤ ጭማሪ ያሳየው 7.4 በመቶ ብቻ እንደሆነ በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ከምታቀርበው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘችው ገቢ 115 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ዶ/ር ፍጹም ሪፖርት አድርገዋል። ይህ ከእቅድ አኳያ ከ100 ፐርሰንት በላይ አፈጻጸም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከኤሌክትሪክ ሽያጭ የተገኘው ገቢ 91 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።
ሀገሪቱ እየተገበረች ባለችው የኢኮኖሚ ሪፎርም “የተሻለ አፈጻጸም እያሳየ ያለ” እንደሆነ በሚኒስትሯ ከተጠቀሰው የቁም እንስሳት ንዑስ ዘርፍ ባለፉት ሶስት ወራት የተገኘው ገቢ 12 ሚሊዮን ዶላር ነው። መንግስት ከያዘው እቅድ 137 በመቶውን ማሳካቱን ዶ/ር ፍጹም ቢገልጹም፤ በመጠን “አሁንም ብዙ መስራት አለብን” ሲሉ ከንዑስ ዘርፉ ከፍ ያለ ገቢ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

























