የዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የሄሞራጂክ ፊቨር (hemorrhagic fever) በሽታ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ46 ሚሊዮን ብር ገደማ አፋጣኝ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ። ድርጅቱ ሀገሪቱ በሽታውን ለመቆጣጠር ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ የሚሰጡ 11 አባላት ያሉበት ቡድን ማሰማራቱንም ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አካል የሆነው ተቋም ይህን የገለጸው፤ የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጂንካ ከተማ የሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ መከሰቱን ይፋ ባደረገ በማግስቱ ነው። በዚሁ በሽታ እስካሁን ስምንት ሰዎች መጠርጠራቸውን ያመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ የበሽታው “ምንነት” ገና “በመረጋገጥ ላይ ያለ” መሆኑን አስታውቆ ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት በዛሬው መግለጫው፤ የበሽታውን ትክክለኛ መንስኤ ለመለየት በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላብራቶሪ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁሟል። በኢትዮጵያ የተከሰተው በሽታ፤ እንደ ኢቦላ፣ ማርቡርግ፣ ክሪሚያን ኮንጎ ሄሞራጂክ ፊቨር እና ላሳ ፊቨር ያሉ ተላላፊዎች ምድብ ውስጥ የሚካተት እንደሆነ ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል።

የእዚህ አይነት በሽታዎች የመጀመሪያ ምልክቶች፤ ትኩሳት፣ ድካም፣ መፍዘዝ፣ የጡንቻ ህመም እና የጥንካሬ ማጣት መሆናቸውን ድርጅቱ ዘርዝሯል። የጤና ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ በአፍ፣ አፍንጫ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የመድማት፣ ትኩሳት፣ ማስቀመጥ እና ማስመለስ ምልክት ሲኖር ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ በወቅቱ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቦ ነበር።
ሚኒስቴሩ በዚሁ መግለጫው በጅንካ የተከሰተውን በሽታ መንስኤ ለማወቅ፣ ተጨማሪ ስርጭትን ለመግታት እና ለመቆጣጠር ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን ወደቦታው መላኩን ገልጿል። ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የተውጣጣው ይህ ቡድን፤ የማህበረሰብ ቅኝት፣ የንክኪ ልየታ፣ የቤት ለቤት ልየታ እንዲሁም የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን “እያጠናከረ” እንደሚገኝም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።
የዓለም ጤና ድርጅት ለዚህ ጥረት ድጋፍ የሚሰጡ እና ለተመሳሳይ ወረርሽኞች ምላሽ በመስጠት ልምድ ያላቸውን 11 ቴክኒካል ባለሙያዎችን ማሰማራቱን በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። ባለሙያዎቹ በበሽታ ቅኝት፣ በላብራቶሪ ምርምራ፣ በበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር፣ በወረረሽኝ ምላሽ ቅንጅት እና በማህበረሰብ ተሳትፎ ስራዎች ላይ እገዛ እንደሚያደርጉም አክሏል።

ድርጅቱ ባለሙያዎችን ከማሰማራት በተጨማሪ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ተገልለው የሚታከሙበት ድንኳን፣ ለጤና ሰራተኞች የሚሆኑ ራስን የመከላከያ ቁሳቁሶች እና የበሽታ መከላከያ አቅርቦቶች ማቅረቡን ገልጿል። የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ በሽታውን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ፤ ለመጠባበቂያ እና ለአስቸኳይ ጉዳዮች ከያዘው ፈንድ ውስጥ 46 ሚሊዮን ብር ገደማ (300 ሺህ ዶላር) ወጪ አድርጌያለሁ ብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































