የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስምንት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 384 ቦታዎችን ለሊዝ ጨረታ አቀረበ። አስተዳደሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት የመሬት ሊዝ ጨረታ ሲያወጣ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
በ2011 ዓ.ም. የከተማ መሬትን በሊዝ ለመያዝ የወጣው አዋጅ፤ የከተማ ቦታ በሊዝ የሚያዘው፤ በጨረታ ወይም በምደባ ስልት እንደሆነ ይደነግጋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቋርጦት የነበረውን የመሬት ሊዝ ጨረታ እንደገና ከጀመረበት ከግንቦት 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ስድስት ዙር ጨረታዎች አከናውኗል።
ለሰባተኛ ጊዜ ለሚከናወነው በአሁኑ የሊዝ ጨረታ የተካተቱ መሬቶች፤ በቦሌ፣ ለሚ ኩራ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ኮልፌ ቀራንዮ፣ አዲስ ከተማ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ናቸው። “ለተለያዩ አገልግሎቶች የተዘጋጁ ናቸው” የተባሉት እነዚህ ቦታዎች፤ ባለፈው ዙር ከቀረቡት በ252 ያህል ብልጫ አላቸው።

በአሁኑ ዙር መጫረት የሚፈልጉ ግለሰቦች የጨረታ ሰነዱን እስከ ጥቅምት 14፤ 2018 ድረስ መግዛት እንደሚችሉ የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል። ተጫራቾች መሬቶቹ የሚገኙበት ቦታ ድረስ በመሄድ እና አጠቃላይ የቦታዎቹን ሁኔታ በማየት ዋጋ ማቅረብ እንዳለባቸው ቢሮው ከትላንት በስቲያ ሰኞ ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ ላይ አመልክቷል።
ባለፈው ነሐሴ ወር በተከናወነው ስድስተኛው ዙር የሊዝ ጨረታ፤ ከፍተኛ ዋጋ ተሰጥቶ የነበረው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነበር። በዚህ ክፍለ ከተማ ለሚገኝ ቦታ የቀረበው ከፍተኛ ዋጋ በካሬ ሜትር 91,330 ብር እንደነበር “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የጨረታ አሸናፊዎች ዝርዝር ያሳያል።
በዚሁ ዙር ዝቅተኛ ዋጋ የተመዘገበው በየካ ክፍለ ከተማ ለሚገኝ መሬት የቀረበው ሲሆን፤ ለቦታው በካሬ ሜትር የተሰጠው ዋጋ 12,550 እንደሆነ በአሸናፊዎቹ ዝርዝር ላይ ሰፍሯል። የአሁኑ ዙር የሊዝ ጨረታ፤ ከጥቅምት 17፤ 2018 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አምስት ቀናት በቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አዳራሽ የሚከፈት መሆኑን የከተማይቱ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ገልጿል።

ቢሮው በ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ባካሄደው ስድስተኛው የመሬት ሊዝ ጨረታ፤ 1.176 ቢሊየን ብር መገኘቱን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስታውቆ ነበር። ከጨረታ አሸናፊዎች ጋር “ውል የማሰሩ ስራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ”፤ በአጠቃላይ 1.8 ቢሊየን ብር ለማግኘት ማቀዱንም መስሪያ ቤቱ አመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

































