ከ20 ዓመት በላይ በሥራ ላይ የቆየውን “የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት አዋጅ” የሚያሻሻል የአዋጅ ረቂቅ፤ ትላንት ሐሙስ ጥር 14፣ 2018 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ቀርቧል። የአዋጅ ረቂቁ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች የተመራው፤ ውይይት ሳይካሄድበት እና አስተያየትም ሆነ ጥያቄ ሳይቀርብበት ነው።
የህግ ረቂቁ በነባሩ አዋጅ ውስጥ ያልተካተቱ አዳዲስ ድንጋጌዎችን አካትቷል። አዲሱ አዋጅ በዋናነት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሥልጣን እና ተግባራት ላይ ማሻሻያዎችን አድርጓል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ተጨማሪ ሥልጣን እና ተግባር በማሻሻያ አዋጁ ተሰጥቷቸዋል። የአዋጅ ረቂቁ የአቪዬሽን ደህንነት አገልግሎት ክፍያ እና የመንገደኞች ፍተሻን በተመለከተም አዳዲስ ድንጋጌዎች አካትቷል። በአዲሱ አዋጅ የተሻሻሉትን እና አዲስ የተካተቱትን ድንጋጌዎችን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን በተመለከተ
በ1997 በወጣው አዋጅ የተጠቀሰው “የደህንነት፣ ኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን” መስሪያ ቤት ፈርሶ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ተተክቷል። በስራ ላይ ባለው አዋጅ የአቪዬሽን ደህንነት ሥራዎችን በበላይነት የማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠው ለቀድሞው “የደህንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን” ነበር።
የአዋጅ ማሻሻያው ይህንን ሥልጣን ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ሰጥቷል። የደህንነት መስሪያ ቤቱ ከቀድሞው ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ከተላለፉለት ሥልጣኖች ሌላ ስድስት አዳዲስ ተግባራት እና ኃላፊነቶች ተጨምረውለታል።
“ብሔራዊ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ጥራት ቁጥጥር” የተባለ የሥራ ክፍል እንዲያቋቋም በአዋጅ ማሻሻያው ኃላፊነት የተሰጠው መስሪያ ቤቱ፤ “ያለገደብ በማንኛውም ቦታ በመንቀሳቀስ” የአቪዬሽን ደህንነት ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞች እና መስፈርቶች አተገባበር ተገቢነት የማረጋገጥ ስልጣንም ተሰጥቶታል። በዚህ ረገድ ችግሮች ከተከሰቱም “የእርምት እርምጃ” “የመውሰድ” እና “የማስወሰድ” ኃላፊነትም ተጥሎበታል።

ብሔራዊ የደህንነት ተቋሙ “የአውሮፕላን እና በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ሕገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ከትከሻ የሚተኮስ የአየር መከላከያ መሣሪያ (MANPADS)፣ ስጋት ማድረስ የሚችል ማንኛውም ነገር ወይም የሰው አልባ አውሮፕላን (drone) ዝውውር ቁጥጥር” የማድረግ ሥልጣንም አግኝቷል። መስሪያ ቤቱ በዚህ መልክ “ሊቃጣ የሚችል አደጋን” ለመከላከል “ስርዓት የመዘርጋት” እና “እርምጃ የመውሰድ” ሥልጣንም በአዲሱ አዋጅ ተሰጥቶታል።
የአየር መንገድ ኦፕሬተሮች፣ የአየር ትራፊክ አገልግሎት ሰጪና የሌሎች ተቋማት የሴክዩሪቲ ፕሮግራም እና መመሪያ የመገምገም እና የማጽደቅ ተግባራት የሚከወናወኑትን በዚሁ ተቋም እንደሆነ የአዋጅ ማሻሻያው ያመለክታል። ወደ ኢትዮጵያ የሚበሩ ኦፕሬተሮች የበረራ ደህንነት ኦፊሰር ስምሪት ቁጥጥር እና ክትትል የሚያደርገው ይሄው ተቋም መሆኑን በአዋጁ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል ያስገንዝባል።
ለደህንነት መስሪያ ቤቱ የተሰጡት አዲስ ተግባራት መካከል “የመንገደኞች ምዝገባ እና የቅድመ-በረራ መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ትግበራን” “መምራት” እና “ማስተባበር” የሚለው ይገኝበታል። ተቋሙ ይህን ተግባር እንዲያከናውን የተሰጠው “የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት” ስላለበት እንደሆነ አዋጁን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ ያስረዳል።

መስሪያ ቤቱ በሀገር ውስጥ ከሚያከናውናቸው “የመረጃ እና ደህንነት ተግባራት” በተጨማሪ ከሌሎች አቻ ተቋማት በመተባበር “አለም አቀፍ የወንጀል ሪከርድ ያላቸውን ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት መረጃ በመለዋወጥ ክትትል እና ቁጥጥር” የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት የማብራሪያ ሰነዱ አመልክቷል። በዚህ መሰረት ተቋሙ “ሽብርተኝነትና የተደራጁ ወንጀሎች በመከላከል ረገድ እንደ ሀገር ያለበትን ኃላፊነት መወጣት ያለበት በመሆኑ” ይህ ተግባር ለእርሱ መሰጠቱ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
የደህንነት መስሪያ ቤቱ “በራሱ ከሚያገኛቸው መረጃዎች እና ከሌሎች አቻ ተቋማት የሚላኩለትን መረጃዎች መሰረት በማድረግ” በአየር ማረፊያዎች ሊተላለፉ የሚችሉ ተጠርጣሪዎችን ለመከታተል እንዲያስችለው የመንገደኞችን ምዝገባ እና ቅድመ-በረራ መረጃ የመሰብሰብ እና የማሰራጨት ትግበራን የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት እንደተሰጠውም ሰነዱ ያብራራል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን በተመለከተ
አዲሱ ማሻሻያ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ስር የነበሩ ለሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተሰጡ ሥልጣን እና ተግባራት የያዙ ሁለት ድንጋጌዎችን ሰርዟል። ከተሰረዙት ድንጋጌዎች መካከል አንዱ፤ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በነባሩ አዋጅ መሰረት “ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን እየተከታተለ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በተቀመጠው መሰረት መሠራቱን ኦዲት ያደርጋል” ይላል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን “የአፈጻጸም ሪፖርቱን” ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያስተላልፍ እና በግኝቶቹ መሰረት የማስተካከያ እርምጃዎችን በወቅቱ መወሰዳቸውን የማረጋገጥ ስልጣንም በተሰረዘው ድንጋጌ ተሰጥቶት ነበር። በአዋጅ ማሻሻያው የተሰረዘው ሌላኛው ድንጋጌ፤ “በኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገቡ የአየር መንገድ ኦፕሬተሮችን እና የዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎችን የደህንነት መመሪያዎች [ከነባሩ] አዋጅ ጋር በተጣጣመ መልኩ መቀረጻቸውን የመገምገም” ስልጣንን ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ሰጥቶ የነበረው ነው።
በተሰረዘው ድንጋጌ፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ግምገማውን መሰረት በማድረግ ለቀድሞው ደህንነት፣ ኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን “አስተያየት” የመስጠት ኃላፊነት ተጥሎበት ነበር። ይሄ ኃላፊነት በአዲሱ አዋጅ በመጠኑ ተሻሽሎ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ተሰጥቷል።

መንገደኞች ከፍተሻ ነጻ ስለሚሆኑበት ሁኔታ
አዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ በኢትዮጵያ በኩል የሚጓዙ ተላላፊ መንገደኞች ከፍተሻ ነጻ የሚሆኑበትን ሁኔታ የተመለከተ ድንጋጌ አካትቷል። በኢትዮጵያ በኩል የሚጓዙ ተላላፊ መንገደኞች “ከመነሻ ሀገር የሚደረግላቸው” የደህንነት እርምጃ “አስተማማኝ መሆኑ ሲረጋገጥ”፤ መንገደኞች እና የጉዞ እቃዎቻቸው “ከፍተሻ ነጻ” ሊሆኑ እንደሚችሉ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል።
ሆኖም ማሻሻያው “አስተማማኝ የደህንነት እርምጃ” በሚል ለተገለጸው ሀረግ ትርጓሜ አልሰጠም። አዋጁን ለማብራራት ለፓርላማ አባላት የተሰራጨው ሰነድ፤ “የኤርፖርቱን የስራ እንቅስቃሴ በማፋጠን፣ የመንገደኞች የአገልግሎት እርካታን ለማምጣት የሚያስችል በመሆኑ” ይህ ድንጋጌ እንዲካተት መደረጉን ገልጿል።
የአቪዬሽን ደህንነት አገልግሎት ክፍያ
በአዋጅ ማሻሻያው፤ “ኦፕሬተሮች” እና በኤርፖርት ውስጥ የአቪዬሽን ደህንነት አገልግሎት የሚያገኙ ማናቸውም አካላት “የደህንነት አገልግሎት ክፍያ” ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የመፈጸም ግዴታ የሚጥል ድንጋጌ ተካትቷል። “ኦፕሬተር” ማለት “በአውሮፕላን አገልግሎት በመስጠት ወይም በአውሮፕላን አገልግሎት የሚሰጡትን በመርዳት ተግባር ላይ የተሰማራ ማንኛውም ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም ኢንተርፕራይዝ ነው” ሲል ነባሩ አዋጅ በትርጓሜ ክፍሉ አስቀምጧል።

በአዲሱ አዋጅ የተደነገገው “የደህንነት አገልግሎት ክፍያን”፤ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት “ተመራጭ ሐሳቦችን ተከትሎ” ከራሱ መንገደኞች፣ ከሌሎች ኦፕሬተሮች እና በኤርፖርት ውስጥ የአቪዬሽን ደህንነት አገልግሎት ከሚያገኙ ማናቸውም አካላት በመሰብሰብ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገቢ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ነው።
የክፍያ ተመኑ በየጊዜው እየተጠና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በጋራ እንደሚወሰን እና እንደሚሻሻል ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ ያመለክታል። ይህንኑ የክፍያ ተመን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ባለው ተቋማዊ አሰራር መሰረት ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያሳውቅ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































