በጋምቤላ ከተማ ከነገ ጀምሮ “ላልተወሰነ ጊዜ” ሞተር ሳይክል ማሽከርከር ተከለከለ 

በጋምቤላ ከተማ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት፤ ከነገ አርብ ጥር 15፤ 2018 ጀምሮ የመንግስትም ሆነ የግል ሞተር ሳይክሎች “ላልተወሰነ ጊዜ” ማሽከርከር “በጥብቅ የተከለከለ” መሆኑን የከተማይቱ አስተዳደር አስታወቀ። በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች እና ግሮሰሪዎችም አገልግሎት መስጠት የሚችሉት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ብቻ መሆኑን አስተዳደሩ ገልጿል። 

አስተዳደሩ ይህን የገለጸው በጋምቤላ ከተማ ባለው “ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ” ላይ ከተወያየ በኋላ መሆኑን የከተማይቱ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ምሽቱን ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል። በጋምቤላ ከተማ ካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ በተከሰተ “የጸጥታ መደፍረስ” እና “ግጭት”፤ ቁጥራቸው እስካሁን በይፋ ያልተገለጸ ሰዎች መሞታቸውን እና መጉዳታቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ወር አጋማሽ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። 

የጋምቤላ ክልል መንግስት መቀመጫ በሆነችው የጋምቤላ ከተማ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ በሚደረግ የተሽከርካሪ እና የሰው እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት እላፊ የተጣለው ህዳር 30፤ 2018 ነበር። በከተማይቱ የተጣለው የሰዓት እላፊ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ባለፈው ታህሳስ 15 ውሳኔ ማሳለፉም አይዘነጋም።

የክልሉ መንግስት በጋምቤላ ከተማ እና “የጸጥታ ችግር ይስተዋልባቸዋል” በተባሉ አካባቢዎች “ላልተወሰነ ጊዜ” የጣለው የሰዓት እላፊ ስለመነሳቱ እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ዛሬ ካካሄደው ውይይት በኋላ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ግን ይህንኑ የሚያጠናክሩ ሆነው ታይተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ “ላልተወሰነ ጊዜ” የሞተር ሳይክል ማሽከርከር ከመከልከሉ በተጨማሪ በከተማው የሚገኙ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት ጊዜ ላይም ገደብ ጥሏል። በውሳኔው መሰረት በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ ባጃጆች አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽት 1 ሰዓት ብቻ ነው። 

በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችና ግሮሰሪዎች አግልግሎት መስጠት የሚችሉት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ብቻ መሆኑንም አስተዳደሩ ጨምሮ ገልጿል። እነዚህን ክልከላዎች እና ገደቦች ጥሶ በተገኘ “ማንኛውም ግለሰብ” ላይ “አስተዳደራዊ እርምጃ” የሚወሰድበት መሆኑንም የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር በዛሬ መግለጫው አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)