በትግራይ ክልል ስር የነበሩ አምስት የምርጫ ክልሎች “በቀጥታ” ምርጫ እንዲካሄድባቸው ተወሰነ  

በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል “አከራካሪ ሆነው” የቆዩ የተባሉ አምስት የምርጫ ክልሎች፤ “የይገባኛል ጥያቄው እስከሚፈታ” ድረስ ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው ለፓርላማ “በቀጥታ” ምርጫ እንዲደረግባቸው ውሳኔ ተላለፈ። ውሳኔ የተላለፈባቸው የምርጫ ክልሎች፤ ሁመራ፣ አዲ ረመጽ፣ ጠለምት፣ ኮረም ኦፍላ እና ራያ አላማጣ ናቸው።

እነዚህ ምርጫ ክልሎች ከሁለቱ ክልሎች ውጭ ሆነው ምርጫ እንዲካሄድባቸው ውሳኔ ያሳለፈው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። ለምክር ቤቱ ውሳኔ መንስኤ የሆነው፤ ጥር 22፤ 2018 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ የተደረገው የምርጫ ክልሎች እና ምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ነው።

በዚህ ዝርዝር ላይ በሁመራ ምርጫ ክልል የሚገኙ ጣቢያዎች፤ በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን፣ በሰቲት ሁመራ ወረዳ የሚገኝ እንደሆነ ተጠቅሶ ነበር። በአዲ ረመጽ የምርጫ ክልል የሚገኙ ጣቢያዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በትግራይ ክልል፣ ምዕራባዊ ዞን፣ በወልቃይት እና ፀገዴ ወረዳዎች ውስጥ ያሉ መሆናቸው በዝርዝሩ ላይ ሰፍሯል።

በዚሁ ክልል፣ በተመሳሳይ ዞን ውስጥ እንደሚገኝ በምርጫ ቦርድ ዝርዝር ተጠቅሶ የነበረው የፀለምቲ ምርጫ ክልል፣ በፀለምቲ ወረዳ የሚገኝ መሆኑ በሰነዱ ተመልክቷል። በትግራይ ክልል፣ ደቡብ ዞን ስር ያሉ የምርጫ ክልሎች ሆነው የተጠቀሱት ደግሞ ኦፍላ ኮረም እና አላማጣ ናቸው።

ሁለቱ ምርጫ ክልሎች በኦፍላ እና በአላማጣ ወረዳዎች እንደሚገኙ በምርጫ ቦርድ ሰነድ ላይ ተቀምጧል።  ይህ ዝርዝር ይፋ መደረጉን ተከትሎ፤ ምርጫ ቦርድ “አከራካሪ ቦታዎች ለትግራይ ክልል ሰጥቷል” በሚል በማህበራዊ ትስስር ገጾች ትችት ቀርቦበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ከአንድ ሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ አሁን ያለው የምርጫ ክልል እና የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት ቦርዱ “በስድስተኛውም፣ በአምስተኛውም ሀገራዊ ምርጫ ሲጠቀምባቸው የነበሩ” እንደሆኑ ገልጸው ነበር። የመጪው ሰባተኛ ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ክልል እና ጣቢያዎች ይፋ የተደረጉት በዚህ መነሻ እንደሆነም በወቅቱ አስረድተዋል።

እርሳቸው ይህን ቢሉም ቦርዱ የምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢያዎችን ዝርዝር ለህዝብ ይፋ ካደረገ ከሶስት ቀናት በኋላ፤ ይህንኑ በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለተቋሙ ደብዳቤ ጽፏል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዚሁ ደብዳቤው፤ አምስት ምርጫ ክልሎች “በትግራይ እና በአማራ ክልላዊ መንግስታት መካከል አከራካሪ ሆነው መቆየታቸውን” መጥቀሱ ተገልጿል።

በእነዚህ የምርጫ ክልሎች “የይገባኛል ጥያቄው እስከሚፈታ፤ ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ውጪ ሆነው ለብቻቸው በቀጥታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ” መወሰኑንም ምክር ቤቱ ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል። በአምስቱ የምርጫ ክልሎች የሚደረገው የክልል ምክር ቤት ምርጫም “አመቺ ጊዜ ተመርጦ ወደፊት እንዲካሄድ” ውሳኔ ማስተላለፉም በምክር ቤቱ ደብዳቤ ላይ ተገልጿል ተብሏል።

“በአከራካሪዎቹ” ቦታዎች ላይ የክልል ምክር ቤት ምርጫ የሚካሄደው፤ “በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ መንግስት ውሳኔ ሲፈታ” እንደሆነም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤው ማሳወቁን ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በግንቦት ወር መጨረሻ የሚደረገውን ጠቅላላ ምርጫ በአምስቱ የምርጫ ክልሎች የሚያስፈጽመው፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት መሆኑን ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]