ኢትዮጵያ “ከሶማሌ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ” በባህር ላይ የሚያጋጥሙ ሽብሮችን የሚያስቀር፣ ቴክኖሎጂ የታጠቀ እና “ውጊያ የሚያሳጥር” ልዩ ኃይል (ኤሊት ፎርስ) እና ተቋም መገንባቷን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱትን የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚመሩት ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ በበኩላቸው፤ የጦር ክፍሉ መንግስት ለሚሰጠው “ማንኛውም ግዳጅ” ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢፌዲሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት አብይ ይህን ያሉት በሀዋሳ ስቴድየም ዛሬ እሁድ የካቲት 15፤ 2018 በተካሄደው፤ የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፤ መደበኛው ጦር “ሊወጣቸው የማይችላቸውን” “ውስብስብ እና አስቸጋሪ” ግዳጆችን የሚፈጽሙ፣ የኮማንዶ፣ የአየር ወለድ እና የጸረ ሽብር ልዩ ኃይል አባላትን በውስጡ የያዘ ነው።
በሺህዎች የሚቆጠሩ የዕዙ አባላት፤ የበዓሉ የክብር እንግዳ እና የኢፌዲሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፊት የሰልፍ እና ወታደራዊ ትርኢት አሳይተዋል። የጸረ ሽብር ልዩ ኃይል አባላትም፤ ከሄሌኮፕተር በአየር ላይ በተዘረጋ ገመድ ላይ ተንጠላጥለው “ታጋቾችን ለማስለቀቅ” እንዴት “ግዳጅ እንደሚወጡ” የሚያሳይ ትርኢት ለታዳሚያን አቅርበዋል።

“በአንድ አካባቢ ላይ የሉዓላዊነት ስጋት ሲፈጠር” “በሰዓታት ውስጥ” በቦታው ተገኝተው “ግጭቶችን የሚቆጣጠሩ” እንደሆኑ የተነገረላቸው የልዩ ኃይል አባላትን፤ “የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎች” ሲሉ ሌተናል ጄነራል ሹማ አወድሰዋቸዋል። ሌተናል ጄነራል ሹማ በዛሬው ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግርም፤ የዕዙ የምስረታ በዓል እንዲከበር ከተደረገባቸው ምክንያቶች አንዱ “ጠላቶቻችን አርፈው የማይቀመጡ ከሆነ ውጊያ ጨራሽ መሆናችንን ለማሳየት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከቀድሞ የበለጠ “የተደራጀ” እና “የሰለጠነ” መሆኑን የገለጹት የዕዙ አዛዥ፤ “በባህርም፣ በየብስም፣ በየትኛውም አየር ጸባይ እና የመሬት ገጽ” የውጊያ ሁኔታ መቀየር የሚችሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። “መንግስታችን፣ ተቋማችን እና ህዝባችን ለሚሰጡን ማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ መሆናችንን በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ሌተናል ጄነራል ሹማ ለክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች ባሰሙት ንግግር አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግርም፤ የኢትዮጵያ ልዩ ኃይል በባህር ላይ የሚደረጉ ግዳጆችን መፈጸም የሚችል መሆኑን አስተጋብተዋል። የሀገሪቱ ልዩ ኃይል “ከሱማሌ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ” በባህር የሚያጋጥሙ ሽብሮችን ማስቀረት የሚችል መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ጭምር “በቂ” እንደሆነ አስታውቀዋል።

ልዩ ኃይሉ “ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም፣ በድሮን ቅኝት የሚያደርግ” መሆኑን የገለጹት አብይ፤ አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች (ካማካዚ) በመጠቀም “ምሽግ የሚያፈርስ” መሆኑንም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ልዩ ኃይል፤ በምሽግ ብቻ ሳይሆን “በስትራቴጂክ ቦታዎች” እና “በሰላም ወረዳዎች” “ውጊያን የሚያጧጡፍ እና የሚያሳጥር ተቋም” እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
“ተቋም የምንገነባው፣ ኤሊት ፎርስ የምንገነባው፤ በቀጠናችን፣ በከባቢያችን ውጊያ፤ በቀጣናችን፣ በከባቢያችን ሽብር እንዳይፈጠር ነው። ሲፈጠርም በአጠረ ጊዜ ለመቋጨት ነው” ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ፤ ኢትዮጵያ ይህን አይነት ተቋም በመገንባቷ “የምስራቅ አፍሪካ” እና “ድፍን የአፍሪካ” ሀገራትን “እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“የእኛ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላም ለማረጋገጥ፤ በድፍን አፍሪካ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፤ በቀጠናችን ላሉ ሀገራት አለኝታ፣ መከታ፣ ጋሻ ለመሆን ነው” ሲሉም አብይ ተናግረዋል። በመከላከያ ሰራዊት የተገነባው ልዩ ኃይል ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ዓለም አቀፍ ስምሪቶች “ስመጥር ተግባራት ሲፈጽም እንደኖረው ሁሉ”፤ “ዛሬም እንደ ትላንቱ የኢትዮጵያን ነጻነት፣ የአፍሪካን ሰላም የሚያስከብር አስተማማኝ ኃይል መሆኑን ለመላው ህዝባችን ለማብሰር እፈልጋለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዛሬውን ንግግር ያደረጉት፤ “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ጦርነት ይቀሰቀሳል” የሚል ከፍተኛ ስጋት ባለበት በአሁኑ ወቅት ነው። አብይ በዛሬው ንግግራቸው የኤርትራን ጉዳይ በቀጥታ አልጠቀሱም። ሆኖም በስቴድየሙ በትርኢት መልክ የቀረቡ መፈክሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀደሙ ንግሮቻቸው በተደጋጋሚ የሚያነሱትን የባህር በር እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይን በጉልህ ያሳዩ ሆነዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፎቶ የተካተተበት አንደኛው መፈክር “ተወደደም ተጠላም ተዘግቶብን አንኖርም” የሚል ኃይለ ቃል ይዟል። ሌላኛው መፈክር ደግሞ “የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና ክብር ለማስጠበቅ ተኝተን አናድርም” ይላል።
በዛሬው ክብረ በዓል ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በ65 ዓመት ታሪኩ የፈጸማቸውን ገድሎች ሲዘረዝሩ ኤርትራን አንስተዋል። የዕዙ ገድሎች በደርግ ዘመን እና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ እንደሆኑም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት “ደርዘን ክፍለ ጦሮች” በስሩ እንደያዘ የተነገረለት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ፤ የተመሰረተው በ1953 ዓ.ም “የአየር ወለድ ጦር” ሲቋቋም እንደሆነ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል። በ1970 ዓ.ም የፈረሰው ዕዙ፤ ከሶስት ዓመት በኋላ “አምስተኛ አየር ወለድ ብርጌድ” በሚል ስያሜ በድጋሚ መመስረቱን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ አመልክተዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ክፍል በ1977 ዓ.ም. ወደ “102ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር” ያደገ ቢሆንም፤ የደርግ መንግስት ከስድስት ዓመት በኋላ ሲወድቅ በድጋሚ መፍረሱን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አስታውሰዋል። ኢህአዴግ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በትጥቅ ትግል ወቅት የነበሩ አራት ኮማንዶ ሻለቃዎችን ከተበተነው “102ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር” ከተገኙ አባላት ጋር በማጣመር “አጋአዚ” የተባለ ክፍለ ጦር መመስረቱንም ገልጸዋል።
“አጋአዚ ክፍለ ጦር ለውጡን ተከትሎ በብሔር እና በፖለቲካዊ ውግንና ምክንያት ለውጡን ያልተቀበሉ መኮንኖች፣ ባለሌላ ማዕረግተኞች እና ወታደሮች በብዛት በመክዳታቸው፤ ክፍለ ጦሩ ተዳክሞ ከነበረበት በማንሳት የመከላከያ አመራር እና የልዩ ዘመቻ ዕዝ አመራሮች በውጊያ ውስጥ ደርዘን ክፍለ ጦሮችን በመፍጠር፤ ለዕዝ እና ለቁጥጥር አመቺ ይሆን ዘንድ ‘የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ’ ተብሎ የተመሰረተ ነው” ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አመሰራረቱን በዝርዝር አስረድተዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ኃይሉን ለማብዛት “በብዙ ሺህዎች” ለሚቆጠሩ ወታደሮች የመሰረታዊ ኮማንዶ ስልጠናን እየሰጠ እንደሚገኝ የዕዙ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሹማ ተናግረዋል። ዕዙ በዛሬው ዕለትም በ44ኛ ዙር የሰለጠኑ ኮማንዶዎችን በይፋ አስመርቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]































