የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የክልሉን ህገ መንግስታዊ ወሰን “አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ሲል አወገዘ

በትግራይ ክልል ስር የነበሩ አምስት የምርጫ ክልሎች “በቀጥታ” ምርጫ እንዲካሄድባቸው የተላለፈውን ውሳኔ፤ “በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘውን የትግራይ ህገ መንግስታዊ ወሰን አደጋ ላይ የሚጥል ነው” ሲል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አወገዘ። ውሳኔውን “አደገኛ” ሲል የጠራው አስተዳደሩ፤ የሚያስከትለውን “መዘዝ” ከግምት ውስጥ በማስገባት “በድጋሚ እንዲጤን” እና “እንዲታረም” በጥብቅ አሳስቧል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ሰኞ የካቲት 16፤ 2018 ዕለት ላወጣው መግለጫ በሰጠው ምላሽ ነው። ምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁመራ፣ አዲ ረመጽ፣ ጠለምት፣ ኮረም ኦፍላ እና ራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች የሚደረገው ምርጫ “ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ውጭ” እንዲደረግ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቆ ነበር።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የትግራይ ህዝብ ድምጽ ባልተወከለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ “ህገ መንግስቱን እና የፕሪቶሪያን ስምምነት በግልጽ የሚጥስ ነው” ሲል ነቅፏል። የቀድሞው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ “የሃገራችንን ሰላም የበለጠ ከማወክ ውጭ ሌላ ትርጉም አላቸው ብዬ አላምንም” ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ተችተዋል።

አቶ ጌታቸው በፕሬዝዳትነት የሚመሩት ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምርጫ ክልሎች ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ “የሀገሪቱን ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት የሚንድ” ሲል ተቃውሟል። ውሳኔው “ተቋማዊ ነጻትን የሚደፈጥጥ” እና “ሕገ- መንግሥታዊ ሥርዓት አልበኝነትን የሚያውጅ ነው” ያለው ፓርቲው፤ የማስተካከያ እርምጃ ካልተወሰደ “በምርጫ የማይሳተፍ መሆኑን” አስታውቋል።

ፓርቲው ይህን ያለው፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ የካቲት 16፤ 2018 በጻፈው ደብዳቤ ነው። የአቶ ጌታቸው ፊርማ ያረፈበት ደብዳቤው፤  የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እና እርሱን የተከተለው የምርጫ ቦርድ ድርጊት “ግልጽ የስልጣን አላግባብ መጠቀም” (abuse of Power)  ማረጋገጫ እንደሆነ አመልክቷል።

በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 62 ስር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠው ስልጣን እና ተግባር “ከህገ-መንግስት ትርጉም እና የክልሎች ወሰን ክርክርን ከመፍታት አይዘሉም” ብሏል ፓርቲው። ምክር ቤቱ “የምርጫ ክልሎችን የማዋቀርም” ሆነ ክልሎችን “ከነባር አስተዳደራዊ መዋቅራቸው ውጭ” በፌዴራል መንግስት ስር እንዲሆኑ የመወሰን “ምንም አይነት ህገ-መንግስታዊ ውክልና” እንደሌለው ስምረት በደብዳቤው አስገንዝቧል።

ማንኛውም የክልል ወሰን መፍትሄ ሊያገኝ የሚገባው በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 48 መሰረት መሆኑን ያመለከተው ፓርቲው፤ ይህ ሂደት ሳይጠናቀቅ እና በህዝበ-ውሳኔ ይፋዊ ለውጥ ሳይደረግ “ምርጫው በፌዴራል መንግስት ይፈጸም” መባሉ “የክልል አስተዳደርን በጉልበት የመንጠቅ ሙከራ ነው” ሲል አውግዟል። የኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 48 የክልሎች “የአከላል ለውጦችን” የሚመለከት ነው።

“የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ፤ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የህዝብ አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወስናል” ሲል ይደነግጋል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት የቀረበ ጉዳይ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴሬሽን ምክር ቤት “የመጨረሻ ውሳኔ” እንደሚሰጥበትም በህገ መንግስቱ ላይ ሰፍሯል።

 እንደ ስምረት ሁሉ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲም፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት በ “ቀጥታ የሚጥስ” ሲል ኮንኖታል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ ውሳኔው “በኃይል የተያዙ ነገር ግን በህገ መንግሥቱ የተረጋገጡትን የምዕራብ፣ የጸለምቲ እና የደቡብ ትግራይ ክፍሎች ግዛቶችን ከህጋዊው የትግራይ አስተዳደር ውጭ የሚያደርግ” እንደሆነ አስታውቋል።

ዛሬ ለህዝብ ይፋ የሆነው ውሳኔ፤ “አሳሳቢ” እና “ሆን ተብሎ ሁኔታዎችን ማባባስን” የሚያመለክት እንደሆነ ገልጿል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ “ገለልተኛ” የአስተዳደር እርምጃ ሳይሆን፤ ይልቁንም በሁለቱ ክልል ተወላጆች መካከል “ግጭት ለመፍጠር የተነደፈ” የተሰላ የፖለቲካ እንቅስቃሴ” እንደሆነ በመጥቀስ ፓርቲው ተችቷል። ውሳኔውን “ህገወጥ እና ግጭት አቀጣጣይ” ሲልም ጠርቶታል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የዲፕሎማሲ አካላት ለዚህ ጉዳይ “አስቸኳይ እና በአዲስ መልክ ትኩረት እንዲሰጡ” ጥሪ ያቀረበው ፓርቲው፤ እንደ አፍሪካ ህብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች የቀጠናው እና አለም አቀፍ ተዋናዮች ያሉ ባለድርሻ አካላት፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ትግራይን እና ቀጠናውን ወደ ሌላ አስከፊ የግጭት እና አለመረጋጋት ውስጥ ሊከት ከሚችል ድርጊት እንዲቆጠብ ግፊት እንዲያደርጉ” ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]