ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ከህግ ውጭ ታስረው የነበሩ 1,336 ሰዎች እንዲፈቱ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 17፤ 2018 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ ከህግ ውጭ የሚፈጸም የዘፈቀደ እስር “መሻሻል ማሳየቱን” ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከክልሎች ጋር ባደረገው ምክክር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ተፈቱ ካሏቸው “ከህግ ውጪ” ታስረው የነበሩ ሰዎች መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው የኦሮሚያ ክልል መሆኑን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል 915 ሰዎች ሲፈቱ፣ በአማራ 186፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 46፣ በጋምቤላ 66 እንዲሁም በሶማሌ ክልል 123 ሰዎች ከህግ ውጪ ታስረው የነበሩ ሰዎች ከእስር መለቀቃቸውን ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ዘርዝረዋል። አቶ ብርሃኑ ይህን እርምጃ “በመልካም ጎን እንመለከተዋለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































