የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ የሚገኙ ተቋማት ለድጋፍ የሚሰበስቡትን ገንዘብ፤ ለዚሁ ተግባር በተከፈተ የባንክ ሒሳብ ውስጥ በ24 ሰዓት ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ አዲስ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጀ። ከህዝብ፣ ከመንግስት እና ከበጎ አድራጎት ለጋሾች የሚሰበሰበው ይህን መሰሉ ሀብት መመዝገብ ያለበት፤ የከተማ አስተዳደሩ በሚከተለው የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት መሠረት እንደሆነም መመሪያው ያዝዛል።
“የድጋፍ ሀብት አሰባበሰብ እና አስተዳደር አፈጻጸም” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ረቂቅ መመሪያ የተዘጋጀው ባለፈው ጥር ወር ነው። በሶስት ክፍሎች እና 15 አንቀጾች የተከፋፈለው መመሪያው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ በድጋፍ ሀብት ምንጭ አሰባሰብ ላይ ያለውን ስልጣን፣ የአስተዳደር ሥርዓት እና የድጋፍ ሀብት የሚሰበሰብባቸውን ምንጮች የዘረዘረ ነው።
አዲሱ መመሪያ ከዚህ በተጨማሪም ድጋፍ የሚሰበስቡ ተቋማት ያላቸውን ኃላፊነት የተመለከቱ እና ሌሎችንም ድንጋጌዎችን በውስጡ አካትቷል። መመሪያው የተዘጋጀው በከተማይቱ የሚገኙ ነዋሪዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የድጋፍ ሀብት ማሰባሰብ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተገልጿል።

ሌላው የመመሪያው ዓላማ፤ የሀብት አሰባሰብ ሂደት ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን፣ ወጥነትን በማስፈን፤ “ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ” ከተለያዩ አካላት የሚሰበሰበውን ድጋፍ “በአንድ ቋት” ማስቀመጥ መሆኑም በረቂቅ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። “የሀብት አሰባሰብ” ማለት “ለተለያዩ ማህበራዊ ድጋፎች እንዲውል ከተለያዩ ግለሰቦች እና ተቋማት በቋሚነት ወይም በዘመቻ መልክ፣ በገንዘብ ወይም በዓይነት ሀብት የማሰባሰብ ተግባር” እንደሆነ የመመሪያው የትርጓሜ ክፍል ያስረዳል።
በመመሪያው መሰረት “የድጋፍ ሀብት ምንጮች” ተብለው የተዘረዘሩት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ የንግዱ ማህበረሰብ ናቸው። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኝ የበጀት ድጋፍ እንዲሁም ከሌሎች ህጋዊ ምንጮች የሚገኝ ድጋፍም፤ በሀብት ምንጭ ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።
የድጋፍ ሀብት የሚያሰባስቡ ተቋማት፤ ለድጋፍ ሀብት አሰባሰብ አስፈላጊ የሆኑ በቂ የሰው ኃይል፣ ኮምፒውተር፣ ኢንተርኔት፣ የባንክ ሒሳብ መመልከቻ እና ሌሎች ሁኔታዎችን የማሟላት ኃላፊነት እንዳለባቸው በመመሪያው ላይ ሰፍሯል። ተቋማቱ የሰበሰቡትን የድጋፍ ገንዘብ፤ ለዚሁ ጉዳይ ተብሎ በተከፈተው አካውንት በ24 ሰዓት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርባቸውም ረቂቁ ደንግጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ የቻናል አንድ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ አቶ አብይ ቢተው፤ ተቋማት እስካሁን የድጋፍ ሀብቶችን ሲሰበስቡ የቆዩት “በተበጣጠሰ መንገድ” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የተወሰኑ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ይህን በተመለከተ የየራሳቸው መመሪያ እንዳላቸው አቶ አብይ ገልጸዋል።

ምንም ዓይነት መመሪያ ሳይኖራቸው ሁነቶችን ብቻ መሠረት በማድረግ ድጋፍ የሚሰበስቡ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት እንዳሉ ያነሱት የክፍል ኃላፊው፤ አሰራሩ “ቁጥጥር የሌለበት” እንደሆነ አስረድተዋል። “አብዛኞቹ ደረሰኝ ቢቆርጡም የትኞቹ ተቋማት እንደሚቆርጡና እንደማይቆርጡ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ነበር። ቁጥጥርም አልነበረም” ሲሉም አቶ አብይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
በዚህም ምክንያት የተሰበሰበው ሀብት በአግባቡ ለተጠቃሚው ስለመድረሱ “ምንም ዓይነት ማረጋገጫ” እንዳልነበረ የክፍል ኃላፊው አክለዋል። የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት በተደጋጋሚ ድጋፍ በመጠየቅ ህብረተሰቡን “የሚያማርሩበት” ሁኔታ እንደነበርም ተናግረዋል።
የሚሰበሰበው ሀብት የባንክ ሒሳብ አያያዝ ላይ “ወጥነት እንደሌለው” የገለጹት አቶ አብይ፤ አንዳንዶቹ ተቋማት ለድጋፍ የሚሆን የተለየ ሒሳብ ሲከፍቱ ሌሎቹ ግን “ከመደበኛው የባንክ ሒሳብ ጋር ቀላቅለው” እንደሚሰበስቡ አመልክተዋል። አዲሱ መመሪያ ከተዘጋጀባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ በገንዘብም ሆነ በዓይነት የሚገኙ የድጋፍ ሀብቶች የሚሰበሰቡበት ሥርዓት “ወጥ እና ለቁጥጥር አመቺ” ለማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል።

ረቂቅ መመሪያው ከህዝብ፣ ከመንግሥት እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚሰበሰበው የገቢ እና የወጪ ሒሳብ አመዘጋገብ፤ የከተማ አስተዳደሩ በሚከተለው የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት መሠረት እንዲከናወን ይደነግጋል። መመሪያው ለአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ ከሰጠው ስልጣን መካከል፤ ተቋማት የድጋፍ ሀብት የሚሰበስቡባቸውን የባንክ ሒሳቦች “መክፈት”፣ “መዝጋት” እና “እንደ አስፈላጊነቱ እንዳይንቀሳቀሱ ማገድ” የሚሉ ይገኙበታል።
ድጋፍ በሚሰበስበው የከተማ አስተዳደሩ ተቋም ዝግ የባንክ ሒሳብ ውስጥ “በስህተት ወይም በብልጫ” የገባ ገንዘብ ሲኖር፤ የሚቀርበውን “የተመላሽ ጥያቄ ትክክለኛነት መርምሮ” ለከፋዩ “እንዲመለስ የማድረግ” ስልጣንም ለቢሮው ተሰጥቷል። ለሀብት አሰባሰብ የሚያገለግሉ የገቢ እና የወጪ ደረሰኞችን የማሳተም፣ ለተቋማት የማከፋፈል እና ተቋማት በራሳቸው እንዲያሳትሙ ሲጠይቁም “መርምሮ የመፍቀድ” ተግባር የቢሮው እንደሚሆን በመመሪያው ተመልክቷል።
ረቂቅ መመሪያው “የሀብት ስርጭት ሥርዓትን” የተመለከተ ድንጋጌም በውስጡ ይዟል። በዚህም መሰረት ማንኛውም የተሰበሰበ ድጋፍ “በገንዘብም ሆነ በዓይነት ሊከፋፈል የሚችለው” ለተሰበሰበበት ዓላማ ብቻ መሆኑ “ሲረጋገጥ” እና በተቋሙ የበላይ ኃላፊ “ሲፈቀድ ብቻ” እንደሆነ በመመሪያው ተደንግጓል።

የሀብት ስርጭቱ “ፍትሐዊነትን፣ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን” የተከተለ መሆኑን ለማረጋገጥ፤ ተጠቃሚዎችን የመለየት ሥራ “እንደ የተቋሙ መስፈርት” መከናወን እንዳለበትም በመመሪያው ላይ ሰፍሯል። ለማህበራዊ አገልግሎት ወይም ለፕሮጀክቶች የሚውሉ ንብረቶች ስርጭትን በተመለከተ፤ የፍላጎት ጥያቄው “በጽሁፍ ቀርቦ፣ በባለሙያ ተረጋግጦ እና በኃላፊ መጽደቅ” እንዳለበት መመሪያው ያስገድዳል።
በገንዘብ ድጋፍ ስርጭት ወቅት ገንዘቡ ወደ ተጠቃሚው የባንክ ሒሳብ እንዲተላለፍ የሚጠበቅ ሲሆን ይህ በማይቻልበት ሁኔታ በአካል ክፍያ ሲፈጸም ግን “የከፋዩ ባለሙያ፣ የክፍያ ምስክር እና ተከፋዩ የፈረሙበት ሰነድ” በፋይናንስ መመሪያ መያዝ እንዳለበት መመሪያው ያዝዟል።
ማንኛውም የሀብት ስርጭት ከተከናወነ በኋላ ድጋፉ ለታለመለት አካል መድረሱን የሚያረጋግጥ የአፈጻጸም ሪፖርት በ15 የስራ ቀናት ውስጥ ተዘጋጅቶ ለተቋሙ ኃላፊ እና ለሚመለከተው አካል መቅረብ እንዳለበት በረቂቁ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























