ለሁለት ሳምንት “በኢ-መደበኛ ማቆያዎች” ተይዞ የቆየው የ“አዲስ ስታንዳርድ” ማኔጂንግ ኤዲተር ከእስር ተለቀቀ    

የ“አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነ፤ ከሁለት ሳምንት እስር በኋላ ትላንት ማክሰኞ ሚያዝያ 20፤ 2018 ከሰዓት በኋላ ተፈትቶ ወደ ቤቱ መመለሱን አሳታሚ ድርጅቱ አስታወቀ። ጋዜጠኛው ታስሮ የቆየው በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ኢ-መደበኛ የማቆያ ስፍራዎች እንደሆነ የመገናኛ ብዙሃኑ ዋና አዘጋጅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ላለፉት አራት ዓመታት በ“አዲስ ስታንዳርድ” ሲሰራ የቆየው ሚሊዮን፤ በአዲስ አበባ ሲኤምሲ ሚካኤል አካባቢ ከሚገኘው የመገናኛ ብዙሃኑ ቢሮ “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች“ የተወሰደው ረቡዕ ሚያዝያ 7፤ 2018 ረፋድ ላይ ነበር። ሲቪል የለበሱት ግለሰቦች ጋዜጠኛውን የወሰዱት “ለጥያቄ እንፈልግሃለን“ በሚል እንደነበር የመገናኛ ብዙሃኑ አሳታሚ ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሚሊዮንን ስለወሰዱት ግለሰቦች ማንነት ተቋሙ ለአዲስ አበባ እና ለፌደራል ፖሊስ የሲቪል ክትትል ኃላፊዎች በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ ቢያቀርብም፤ “የእኛ አባላቶቻችን አይደሉም”፣ “አናውቃቸውም” የሚል ምላሽ እንዳገኘም ድርጅቱ በዚሁ መግለጫው አመልክቶ ነበር። ጋዜጠኛው የደረሰበት ሳይታወቅ ለአንድ ሳምንት ያህል ከቆየ በኋላ መገናኛ ብዙሃኑ ባወጣው መረጃ፤ ሚሊዮን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ “በግልጽ ባልታወቀ ስውር ቦታ እንደሚገኝ” አሳታሚ ድርጅቱ እና የተቋሙ የህግ ቡድን ማረጋገጣቸውን ገልጿል።

ሆኖም ጋዜጠኛውን ቤተሰቡ፣ የስራ ባልደረቦቹ እንዲሁም የህግ አማካሪዎች “ሊጠይቁትም ሆነ ሊያነጋግሩት እንዳልቻሉ” በዚሁ መረጃ ላይ ሰፍሯል። የ“አዲስ ስታንዳርድ” ዋና አዘጋጅ አቶ ዮናስ ከድር “ለሁለት ሳምንት አካባቢ እኛም ቤተሰቡም [አላገኘነውም]።  በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ አዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ኢ-መደበኛ የማቆያ ስፍራ ነው እንዲቆይ የተደረገው” ሲሉ ጋዜጠኛ ሚሊዮን ስለነበረበት ሁኔታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አቶ ዮናስ ጋዜጠኛውን በትላንትናው ዕለት ያስረከቡት “የመንግስት የደህንነት አካላት” መሆናቸውን ቢገልጹም፤ ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል። የሚሊዮንን የእስር ሁኔታ የተመለከቱ “ዝርዝር መረጃዎች”፤ የጋዜጠኛውን “ደህንነት በማይጎዳ መልኩ” ወደፊት ይፋ እንደሚደረጉ ጃኬን ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል። 

በጋዜጠኛው ላይ የደረሰውን “የመሰወር ድርጊት” እና “እንግልት” “በጽኑ እንደሚቃወም” የገለጸው አሳታሚ ድርጅቱ፤ ክስተቱ “የፕሬስ ነጻነትን ማክበር እንዲሁም ጋዜጠኞችን ከማስፈራሪያ፣ ከሕገ-ወጥ እስር እና ከማስገደድ ድርጊቶች መጠበቅ  አስፈላጊ መሆኑን  በድጋሚ ያረጋገጠ ነው” ሲል በዚሁ መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ድርጊቱ “በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ያልተገደበ ጫና እና የእገታ ስጋት የሚያሳይ ነው” ብሎ ነበር። 

ማህበሩ በዚሁ መግለጫው በጋዜጠኛ ሚሊዮን ላይ የተፈጸመው “እገታ”፤ በኢትዮጵያ “ህገ መንግስት እና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች የተረጋገጠውን የግል ነጻነት እና ደህንነት የመጠበቅ መብትን በግልጽ የጣሰ ነው” ሲልም ተችቷል። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ በበኩሉ የጋዜጠኛ ሚሊዮን “መሰወር”፤ ችግሮች ሲገጥሙት በቆየው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ የደረሰ “የሚረብሽ አዲስ ምዕራፍ ነው” ብሎ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)