የ“አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነ በትላንትናው ዕለት ረፋድ ላይ “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች” ከተወሰደ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ የደረሰበት እንዳልታወቀ ተቋሙ አስታወቀ። ጋዜጠኛው ስለሚገኝበት ቦታ እና ሁኔታ ለተቋሙም ሆነ ለቤተሰቦቹ ያስታወቀ አካል ባለመኖሩ “ከፍተኛ ስጋት” እንደፈጠረባቸው የመገናኛ ብዙሃኑ ዋና አዘጋጅ አቶ ዮናስ ከድር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በጋዜጠኝነት ከ20 ዓመት በላይ ልምድ ያለው ሚሊዮን “አዲስ ስታንዳርድን” የዛሬ አራት ዓመት ከመቀላቀሉ በፊት፤ በቀድሞው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ውስጥ በዚሁ ሙያ አገልግሏል። በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃኑ በተለያዩ የአርታኢነት ደረጃዎች ሲሰራ የቆየው ሚሊዮን፤ ሲኤምሲ ሚካኤል አካባቢ ከሚገኘው የተቋሙ ዋና ቢሮ ሲቪል በለበሱ ሰዎች የተወሰደው ትላንት ረቡዕ ሚያዝያ 7፤ 2018 ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ40 ገደማ ላይ እንደሆነ አቶ ዮናስ ገልጸዋል።
ማንነታቸው ያልታወቀው እነዚሁ ግለሰቦች ወደ ቢሮው በመግባት ጋዜጠኛውን “ለጥያቄ እንፈልግሃለን” በማለት ይዘውት ሲወጡ፤ በደህንነት ካሜራ (CCTV) መታየታቸውን ዋና አዘጋጁ ተናግረዋል። ግለሰቦቹ የጋዜጠኛውን “ስልክ ሲቀበሉ” እና “ላፕቶፕ በእጁ ይዞ ሲሄድ” በደህንነት ካሜራው መመልከታቸውንም አቶ ዮናስ አስረድተዋል።

የ“አዲስ ስታንዳርድ” አሳታሚ የሆነው ጃኬን አሳታሚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ ድርጊቱ ከመፈጸሙ በፊት ቢያንስ ሶስት ባርኔጣና ማስክ ያደረጉ እንዲሁም ሌላ አንድ ግለሰብ የመገናኛ ብዙሃኑ ቢሮ በሚገኝበት ደረጃ አካባቢ “ሲንቀሳቀሱ” እና “ተግባራቸውን ሲያቀናጁ” መታየታቸውን ገልጾ ነበር። ግለሰቦቹ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የነበረው “በታቀደ እና በተደራጀ መልኩ” እንደነበርም ድርጅቱ አክሏል።
እነዚህ ግለሰቦች ጋዜጠኛ ሚሊዮንን ከያዙ በኋላ “አንደኛው እየመራ ሌሎቹ ደግሞ ተከታትለውት” የ“አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮ ከሚገኝበት ህንጻው በጋራ መውጣታቸውን ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል። ከድርጊቱ በኋላ የድርጅቱ አመራሮች እና የህግ ቡድን ጋዜጠኛው ያለበትን ቦታ ለማወቅ ቀኑን ሙሉ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስታውቋል።
ሚሊዮን ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ የ“አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮ ባለበት መሪ አካባቢ የሚገኙ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎችን እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስን መጠየቃቸውን አቶ ዮናስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ የሲቪል ክትትል ኃላፊዎች ጋዜጠኛውን ስለወሰዱት ግለሰቦች በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ ቢቀርብላቸውም፤ “የእኛ አባላቶች አይደሉም”፣ “አናውቃቸውም” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ዋና አዘጋጁ አስረድተዋል።

“የህግ አካል ቢይዝ ለፖሊስ ያስረክባል፤ የተለመደው እንደዚያ ነው። ከዚያ ለቤተሰብ ይደወላል፤ ‘ልብስ፣ ምግብ’ ይባላል በተለምዶው አሰራር። ነገር ግን ያም የለም። የት እንዳለ ማወቅ አልቻልንም” ሲሉ አቶ ዮናስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጋዜጠኛ ሚሊዮን ስለሚገኝበት ቦታ ለቤተሰቦቹም ሆነ ለሚሰራበት ድርጅት ያስታወቀ አካል እስካሁን አለመኖሩ “ከፍተኛ ስጋት” እንደፈጠረባቸውም አመልክተዋል።
በጋዜጠኛው ላይ የተፈጸመውን ድርጊት “የሰብዓዊ መብት ጥሰት” መሆኑን የገለጹት ዋና አዘጋጁ፤ ይህንኑ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትላንትናው ዕለት ማስታወቃቸውን ጠቁመዋል። ጉዳዩ የደረሰበት ደረጃን ለማወቅ በዛሬው ዕለት የኮሚሽኑን ሰራተኞች ማነጋገራቸውን እና ሁኔታውን “እየተከታተሉት” እንደሆነ ምላሽ ማግኘታቸውንም አክለዋል።
የትላንቱን ድርጊት “እገታ” ሲል የጠራው የ“አዲስ ስታንዳርድ” አሳታሚ ድርጅት፤ ክስተቱ የተፈጸመው በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃኑ የዜና ክፍል እና ስራዎች ላይ “ተደጋጋሚ” እና “እየበረታ የመጣ” “የጸጥታ እና የአስተዳደራዊ ጫናዎች” ባሉበት ወቅት እንደሆነ በትላንቱ መግለጫው ጠቅሷል። ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አጋማሽ፤ የመገናኛ ብዙሃኑ ሶስት ሰራተኞች ለአንድ ቀን ታስረው መለቀቃቸውን ድርጅቱ አስታውቆ ነበር።


በዚያን ወቅት ፖሊስ በ“አዲስ ስታንዳርድ” ቢሮ ባደረገው ብርበራ፤ የድርጅቱ እና የሰራተኞች በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች እንደተወሰዱበት መግለጹም ይታወሳል። በፖሊስ የተወሰዱት ላፕቶፖች፣ ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ የሞባይል ስልኮች፣ ፍላሽ ዲስኮች እና ሲፒዩዎች ከቀናት በኋላ መመለሳቸውንም ድርጅቱ በወቅቱ ገልጿል።
ሆኖም የድርጅቱ የአይቲ ባለሙያዎች በንብረቶቹ ላይ ባደረጉት “ሙያዊ ፍተሻ” “የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌሮች (malware) መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ” ማግኘታቸውን ድርጅቱ በወቅቱ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም። “በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የደረሰው ጥቃት ቀድሞውንም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚገኘው የፕሬስ ነጻነት ላይም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል መብቶችና የግላዊ መረጃዎች ደህንነት የወደፊት ሰፊ ዕጣ ፈንታ ላይ የተቃጣ የጥቃት ሙከራ ነው” ሲልም መገናኛ ብዙሃኑ በወቅቱ ድርጊቱን ኮንኖ ነበር።
በየካቲት 2003 ዓ.ም የተመሰረተው “አዲስ ስታንዳርድ” መገናኛ ብዙሃን፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እገዳ ተጥሎበት እንደነበር አይዘነጋም። ባለስልጣኑ በሰኔ 2013 ዓ.ም. መገናኛ ብዙሃኑን አግዶት የነበረው፤ በትግራይ ክልል ጦርነት ወቅት “የሽብርተኛ ቡድን አጀንዳዎችን ያራምዳል” የሚል ውንጀላ በማቅረብ ነው።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፈው የካቲት ወር ባወጣው መግለጫ፤ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃኑን የምዝገባ ምስክር ወረቀት መሰረዙን አስታውቋል። የ“አዲስ ስታንዳርድ” የምዝገባ ወረቀት የተሰረዘው “የሚዲያ ስነ-ምግባርን፣ የኢትዮጵያን ህጎች እና የሀገርንና የህዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ አሰራጭቷል” በሚል ምክንያት ነው።
“አዲስ ስታንዳርድ” ውሳኔውን በመቃወም የአቤቱታ ደብዳቤ ለባለስልጣኑ ቦርድ አስገብቶ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ዋና አዘጋጅ አቶ ዮናስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ በሂደት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። “የእነሱ ውሳኔ ህገ ወጥ [ነው]። ስለዚህ ለህገ ወጥ ውሳኔ እኛ እውቅና አንሰጥም። አሁንም ምንም የሚያቆመን የህግ አግባብ ስለሌለ ስራችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ዋና አዘጋጁ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































