በተስፋለም ወልደየስ
ለጃዋር መሐመድ የሳተላይት መሳሪያ በመግጠም የተከሰሱት አቶ ሚሻ አደም ዛሬ በነበራቸው ችሎት ሳይቀረቡ ቀሩ። በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዋስትና ተፈቅዶላቸው የነበሩት አቶ ሚሻ ትላንት ከእስር መፈታታቸው ቢነገርም፤ ጠበቆቻቸው ግን በኦሮሚያ ፖሊስ በድጋሚ መታሰራቸውን መስማታቸውን ዛሬ ለችሎት ገልጸዋል።
የአቶ ሚሻን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 20ኛ ወንጀል ችሎት ጳጉሜ 4፤ 2012 ባስቻለው ችሎት ተከሳሹ የ20 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም የፌደራል ፖሊስ ከፍርድ ቤት የተሰጠ እግድ ሳይኖር ተከሳሹን ለቀናት በእስር ላይ ማቆየቱን የአቶ ሚሻ ጠበቃ አቶ ከዲር ቡሎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ካሳለፈ ከአምስት ቀናት በኋላ፤ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ “ዋስትናው ሊፈቀድ አይገባም” ሲል ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱን ጠበቃው አስታውሰዋል። ከትላንት በስቲያ ሰኞ መስከረም 4፤ 2013 በነበረ ችሎት ይግባኙን የተመለከተው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ማጽናቱንም ገልጸዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ፤ በትላንትናው ዕለት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ለአቶ ሚሻ የመፈቻ ትዕዛዝ ጽፎላቸው እንደነበር አንድ የቤተሰብ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። እኚሁ የቤተሰብ አባል የመፈቻ ትዕዛዙን ይዘው ተከሳሹ ወደ ታሰሩበት አዲስ አበባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቢያመሩም በጥበቃ ላይ በተሰማሩ ፖሊሶች መለቀቃቸው እንደተነገራቸው አብራርተዋል። ዘግይቶም አቶ ሚሻ ከእስር ከወጡ በኋላ በኦሮሚያ ፖሊስ እንደተወሰዱ መስማታቸውን አክለዋል። የተከሳሹ ጠበቆችም ተመሳሳይ መረጃ እንደደረሳቸው ዛሬ ለችሎት አቤት ብለዋል።
የአቶ ሚሻን የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ክስ የሚመለከተው 20ኛ ወንጀል፤ በአቶ ሚሻ ላይ የሚመሰክሩ ምስክሮች ማንነት እንዳይገለጽ አቃቤ ህግ ላቀረበው አቤቱታ፤ የተከሳሽ ጠበቆች የሚሰጡትን አስተያየት ለማድመጥ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ አቤቱታውን ቅድሚያ ሰጥቶ ተመልክቷል። ጉዳዩን በጽህፈት ቤት የተመለከተው ችሎቱ፤ “ተከሳሹ ተለቅቋል ተብሎ ቢገለጽም ለኦሮሚያ ፖሊስ ተላልፎ ተሰጥቷል” መባሉን ከግራ ቀኙ ክርክር መረዳቱን ገልጿል። በዚህም ላይ በመመስረት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ፖሊስ በፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳዩን እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ተከሳሹን በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለቅቀው መሆን አለመሆኑን እንዲያስረዱ ያዘዘው ችሎቱ፤ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ተላልፈው ተሰጥተውም ከሆን ምክንያቱን እንዲገልጹ አሳስቧል። ችሎቱ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ችሎቱ በጽህፈት ቤት ለቀረቡት አቃቤ ህግም ተከሳሹን በማፈላለግ እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
“ተከሳሹ በችሎት ቀርበው ክርክር ሊደረግ ይገባ ነበር” ያሉት የችሎቱ ዳኛ፤ የህግ የበላይነት የማስከበር ጉዳይ ከሆነ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊከበር ይገባ እንደነበር አሳስበዋል። በዋስትና ጉዳይ ላይ የቀረበው ይግባኝ መከልከሉን የጠቀሱት ዳኛው፤ ከዚያ በኋላ ተከሳሹ ታስረው መቆየታቸው አግባብ እንዳልሆነ ጠቁመዋል። ቀጣይ የችሎት ሂደቶችን ለማከናወን “መጀመሪያ ተከሳሹ የት እንዳለ መታወቅ አለበት” ያሉት ዳኛው፤ ከዚያ በኋላ “የሚሰጡ ትዕዛዞች ይኖራሉ” ብለዋል። ችሎቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ፖሊስን ምላሽ ለማድመጥ ለመጪው ሰኞ መስከረም 11፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ሚሻ የተከሰሱት የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅን በመተላለፍ ነው። የአቃቤ ህግ ተከሳሹ “ኢትዮ ቴሌኮም የዘረጋውን መሰረተ ልማት ወደ ጎን በመተው፤ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ከአሜሪካን ሀገር በማስመጣት በአቶ ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ዘርግተዋል” ሲል ይወነጅላል። ተከሳሹ ዘርግተዋቸዋል ከተባሉ መሳሪያዎች ውስጥ በግለሰብ ደረጃ መያዝ የማይፈቀደውን ሮኬት ፕሪዝም ጂን 2 ሲስተም፤ ዩቢኪውቲ ኤጅ ራውተር እንዲሁም ከሳተላይት የሚመጣውን ሲግናል ለመሰብሰብና ቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ቪሳት ዲሽ መሆኑ በክሳቸው ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)