በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 2,672 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ስራ አለመጀመራቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

በ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለመመዝገብ ከታቀዱ ተማሪዎች መካከል 6.3 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት አለመመዝገባቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ለፓርላማ በላከው ሪፖርት አስታወቀ። በአማራ፣ በትግራይ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙትን ጨምሮ 2,672 ትምህርት ቤቶች ዘንድሮ የመማር ማስተማር ስራ አለመጀመራቸው፤ ተማሪዎቹ በትምህርት ገበታቸው ላይ ላለመገኘታቸው በሪፖርቱ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተላከው ባለ 108 ገጽ ሪፖርት፤ የትምህርት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም የዳሰሰ ነው። የትምህርት ተደራሽነትን ማሳደግ በሚያትተው የሪፖርቱ ክፍል፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 33.5 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እንደነበር ሰፍሯል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእቅድ ከያዘው የተመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት 19 በመቶውን ያህል ማሳካት እንዳልቻለ በሪፖርቱ ገልጿል። በዚህም መሰረት ዘንድሮ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ታቅዶ ከነበረው ውስጥ 6,380,932 ተማሪዎች መመዘገብ አለመቻላቸው ተጠቁሟል። 

ተማሪዎቹ በትምህርት ገበታቸው ላይ ላለመገኘታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሪፖርቱ በምክንያትነት የጠቀሰው፤ 2,672 በላይ ትምህርት ቤቶች በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ ምክንያት ስራ አለመጀመራቸውን ነው። ሆኖም ሪፖርቱ “ሰው ሰራሽ” እና “የተፈጥሮ” ያላቸውን ችግሮች አላብራራም። 

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ስራ ካልጀመሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 77.4 በመቶው የሚገኙት በአማራ ክልል መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል። ከትምህርት ቤቶቹ ውስጥ 11.8 በመቶው በትግራይ፣ 8.8 በመቶው ደግሞ በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ናቸው። የተቀሩት ሁለት በመቶ የሚሆኑት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

በበጀት አመቱ መማር ከነበረባቸው ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ተኛ ክፍል ካሉ ተማሪዎች ውስጥ የመማር እድል ያላገኙ ተማሪዎች 19 በመቶ ያህል መሆኑ፤ በፓርላማው የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ቀርቦበታል። ጥያቄው የቀረበው ቋሚ ኮሚቴው በትምህርት ሚኒስቴር የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ላይ ለመወያየት ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ሚያዝያ 7፤ 2018 በጠራው ስብሰባ ላይ ነበር። 

የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄዎች በንባብ ያቀረቡት አቶ ታደሰ ጌጡ፤ የመማር እድል ካላገኙ ተማሪዎች በተጨማሪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን በመጥቀስ ችግሩን ለመፍታት ምን እየተሰራ እንደሆነ ጠይቀዋል። ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ፤ ከባለፈው ዓመት ሲነጻጸር ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ካለፈው ዓመት የጨመረ ተማሪ ማስመዝገብ የተቻለው ዘንድሮው ዓመት የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ ሰፊ ንቅናቄ ተደርጎ በተሰራው ስራ መሆኑን አስረድተዋል። በ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በአጠቃላይ 27.1 ሚሊዮን ተማሪዎች መመዝገብ የተቻለው፤ ከክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በስፋት በተሰራው ስራ መሆኑን አስረድተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ካለፈው ዓመት የተሻለ የተማሪዎች ቁጥር መመዝገቡን በአጽንኦት ቢገልጹም፤ አሁንም ቢሆን የመማር ዕድል ያላገኙ ተማሪዎች እንዳሉ አምነዋል። “በሪፖርታችን እንዳስቀመጥነው በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ ምክንያት ያልመጡ መሆኑን ለመጠቆም ሞክረናል” ሲሉም ምክንያቱን አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት ከተመዘገቡ ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ከታቀደው አንጻር አነስተኛ መሆኑን በተመለከተም ወ/ሮ አየለች ምላሽ ሰጥተዋል። በ2018 የትምህርት ዘመን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመመዝገብ ታቅዶ የነበረው 4.3 ሚሊዮን ተማሪዎችን ነበር። ሆኖም ከእቅዱ አንጻር መፈጸም የተቻለው 61 በመቶውን ብቻ ነው። 

“[ተማሪዎች] ሁለተኛ ደረጃ ሲገቡ ያለውን ቁጥር ስናይ፤ በአንጻራዊነት ዝቅ ያለ መሆኑን አይተናል። ተማሪዎች ወደ ሁለተኛ ደረጃ ሲገቡ የኢኮኖሚ ገቢ ወደሚያስገኙ ስራዎች የማዘንበል ነገር እንዳለ በክትትላችን ያየነው ነው” ሲሉ ሚኒስቴር ዴኤታዋ የመስሪያ ቤታቸውን ግኝት ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገልጸዋል።

“ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ህጻናት ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን በዝርዝር እያስጠናን ነው ያለነው። በቅርቡ ይህንን ጥናት አጠናቅቀን ለቋሚ ኮሚቴው የምንልክ ይሆናል። አንድም ህጻን ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆን የለበትም መርህ ይዘን በዚሁ አግባብ እየሰራን እንገኛለን” ሲሉም ሚኒስቴር ዴኤታዋ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)