በመሬት መንቀጥቀጥ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፤ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ በተከሰተባቸው ስፍራዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችን፤ የአደጋ ስጋት ወደሌለባቸው ቦታዎች የማጓጓዝ ስራ ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 26፤ 2017 በስፋት ሲከናወን ውሏል። ከከሰም የስኳር ፋብሪካ አቅራቢያ በሚገኘው እና በተለምዶ “ቀበና” ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች፤ በዛሬው ዕለት አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። 

ዛሬ ረፋዱን በስፍራው የነበረ አንድ የዓይን እማኝ፤ የተወሰኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች በስድስት ወታደራዊ ካሚዮን ተጭነው ሲጓጓዙ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጥቂት ንብረቶቻቸውን ይዘው አካባቢውን የለቀቁ እነዚህ ነዋሪዎች፤ ለጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች የሚያውሉት ገንዘብ የሌላቸው ናቸው።

በተሻለ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ ጥቂት ነዋሪዎች፤ የጭነት መኪናዎችን በመከራየት ወደ አዋሽ አርባ፣ ወደ አዋሽ ሰባት እና ሌሎችም ከተሞች ንብረቶቻቸውን ሸክፈው ሲጓዙ በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። ነዋሪዎቹ እንደ “አይሱዙ” ያሉ የጭነት መኪናዎችን ለመከራየት ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር እንደሚጠየቁም ዘጋቢው ተረድቷል።

በዚህ መጠን አቅም የሌላቸው ነዋሪዎች፤ በሚኒባስ፣ በሶስት እግር ተሽከርካሪዎች እና በሞተር ሳይክል ጭምር ንብረቶቻቸውን ሲያጓጓዙ ታይተዋል። በመከላከያ ሰራዊት የትራንስፖርት እገዛ ከቀበና ከተማ እንዲወጡ ከተደረጉ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑቱ፤ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ በሚዘረጋው አውራ ጎዳና አጠገብ ካለ ገለጣ ስፍራ ለመስፈር መገደዳቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ታዝቧል። 

በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች ቤት ለመከራየት አቅም እንደሌላቸው የሚናገሩት እነዚህ ነዋሪዎች፤ በአካባቢው የሚያውቁት ዘመድ አዝማድ ባለመኖሩ ለጊዜው ይህን አማራጭ መከተላቸውን አስረድተዋል። ከሚጠጡት ውሃ ጀምሮ የዕለት ደራሽ እርዳታ በአስቸኳይ እንደሚያስፈልጋቸውም ተማጽዕኖ አቅርበዋል።

በአፋር ክልል፣ ዱለሳ ወረዳ ከሚገኘው ሳገንቶ ቀበሌ ብቻ ሶስት ሺህ ገደማ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ካሉአለ ከተባለ ስፍራ የመጡት እኚሁ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ርዕደ መሬት የሚገልጹት “አስፈሪ” በሚል ቃል ነው።

“መሬት መንቀጥቀጥ ነበር። እንደገና ደግሞ እሳት ወጣ። የአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ ራሱ የተለየ ነው። የቆመ ሰው ይወድቃል፤ ግመልም ይወድቃል፤ ከብትም ይወድቃል” ይላሉ ነዋሪው የሰሞኑን ሁኔታ ሲገልጹ። “ውሃ የወጣበት አካባቢ ከሶስት ኪሎ ሜትር [ዙሪያ] የሚሆንበት ቦታ ላይ መሬት ስለሚንቀጠቀጥ ሰው በጣም ይፈራል” ሲሉም ነዋሪው ያክላሉ። 

በአፋር ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተከሰቱት የመሬት መንቀጥቀጦች በሬክተር ስኬል ከ4 እስከ 5.8 የደረሱ እንደሆኑ በክስተቶቹ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት መረጃ ያመለክታል። በሬክተር ስኬል ከ5.5 እስከ 6.0 መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች ህንጻዎች እና በሌሎች ግንባታዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው።


ያለፉት ቀናት የመሬት መንቀጥቀጦች፤ በሳገንቶ ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኘው የከሰም የስኳር ፋብሪካ ላይ ከፍተኛ የንብረት ውድመት አድርሰዋል። የሳገንቶ ቀበሌ ነዋሪው በእርሳቸው የመኖሪያ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጡ ባስከተለው ፍንዳታ የፈለቀ፤ “ውሃ የመሰለ ፈሳሽ” ለቤቶች መቃጠል ምክንያት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

“ብዙ ቤቶች ተቃጥለዋል። ከግቢ ውስጥ በሚወጣ ውሃ፤ ቤት ይቃጠላል። ውሃ ይባላል እንጂ እሳት ነው” ሲሉ ነዋሪው የፈሳሹን ምንነት ያስረዳሉ። በእርሳቸው የመኖሪያ አካባቢ ርዕደ መሬቱ በሰው ላይ ጉዳት ባይደርስም፤ ከብቶች ግን መሞታቸውን ነዋሪው ተናግረዋል። በመሬት መንቀጥቀጡ የነዋሪዎች ንብረት መውደሙንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)